ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | በአዲስ አበባ ስታድየም ውሎ ንግድ ባንክ እና መከላከያ አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን በዛሬው ዕለት አራት የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች የተካሄዱ ሲሆን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተደረጉት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መከላከያ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

8:00 ላይ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው መከላከያ 1-0 በማሸነፍ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል። ጨዋታው እጅግ የተቀዛቀዘ መልክ የነበረው ሲሆን የግብ ሙከራዎችን ለማስተናገድ 17 ደቂቃ መጠበቅ ግድ ሆኗል። ትሁን አየለ ያሻገረችውን ኳስ ሰርካለም ካሣ በአግባቡ ተቆጣጥራ የመታችውና ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ ያዳነችባት በአርባምንጭ በኩል የመጀመርያ ሙከራ ሲሆን በ23ኛ ደቂቃም አርባምንጮች ትሁን አየለ ከርቀት መትታ ኢላማውን በሳተ ኳስ ሌላ የጎል እድል መፍጠር ችለዋል። ከወትሮው እንቅስቃሴያቸው ተቀዛቅዘው የቀረቡት መከላከያዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ በመግባት ተጭነው መጫወት ችለዋል። በ30ኛው ደቂቃ የምስራች ላቀው ከርቀት የመታውና ግብ ጠባቂዋ ተስፋነሽ ተገኔ ያዳነችባት፣ በ34ኛው ደቂቃ ሲሳይ ገብረዋህድ ከቀኝ መስመር አክርራ መትታ የግቡን አግዳሚ የገጨባት እንዲሁም በ41ኛው ደቂቃ ብሩክታዊት አየለ የቀኝ ቋሚውን ታኮ የወጣባት ሙከራዎች ጦሩን መሪ ሊያደርጉ የተቃረቡ ሙከራዎች ናቸው።

ከእረፍት መልስ ሙሉ ለሙሉ የጨዋታውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር የቻሉት መከላከያዎች በአርባምንጭ የግብ ክልል አመዝነው ተጭነው በመጫወት በርካታ እድሎችን መፍጠር ሲችሉ አርባምንጮች በተቃራኒው ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት አፈግፍገው መጫወትን መርጠዋል። በተለይም በ70ኛው ደቂቃ የምስራች ላቀው የመታችውና የግቡን አግዳሚ ለተማ የተመለሰው ኳስ አስቆጪ ነበረች። የመከላከያዎች ጫና ፍሬ ያስገኘው በ84ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ሔለን እሸቱ በግምት ከ25 ሜትር ላይ አክራራ የመታችው ኳስ የግቡን ብረት ለትማ ከመረብ አርፋለች። ጨዋታውም በመከላከያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


በ10:00 ሰዓት ላይ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፈው ኢትዮጽያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ ጋር 1-0 አሸንፏል። ጨዋታውን በጥሩ እንቅስቃሴ የጀመሩት ድሬዳዋዎች ቢሆኑም ብዙም ሳይቅይ ንግድ ባንኮች ጨዋታውን በመቆጣጠር ፍፁም ብልጫ ማሳየት ችለዋል።

ንግድ ባንኮች የእንቅስቃሴ እና የጎል ሙከራ ብልጫ ቢኖራቸውም ኳስና መረብ ማገናኘት የቻሉት የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ የዳኛዋ ፊሽካ ሲጠበቅ ነው። ብዙነሽ ሲሳይ በቀኝ መስመር በኩል ይዛ የገባችውን ኳስ አክርራ በመምታት የኢትዮጽያ ንግድ ባንክን ብቸኛ ጎል አስቆጥራለች።

ከዕረፍት መልስ ተጨማሪ ጎል ባይቆጠርም በሁለቱም በኩል ያለቀላቸው የግብ ሙከራዎች ተስተናግደዋል። ንግድ ባንክ በረሂማ ዘርጋው እና ብርቱካን ገብረክርስቶስ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ የመጨረሻዎቹን በሳራ ይርዳው አማካኝነት ያደረጉት ለጎል የቀረበ ሙከራ አስቆጪ ነበር።

ካስፈለገዎ: አዳማ እና ባህር ዳር ላይ የተደረጉ ጨዋታዎችን ሪፖርት ሊንኩን ተጭነው ያገኛሉ | LINK


4ኛ ሳምንት
ቅዳሜ ታኅሳስ 6 ቀን 2011
መከላከያ 1-0 አርባምንጭ ከተማ
ጥረት ኮርፖሬት 0-1 ጌዴኦ ዲላ
አዳማ ከተማ 2-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ኢትዮ ንግድ ባንክ 1-0 ድሬዳዋ ከተማ
እሁድ ታኅሳስ 7 ቀን 2011
ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 09:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሀዋሳ ከተማ 09:00 አዲስ አበባ ከተማ