ሪፖርት | ከጉዞ የተመለሱት ሀዋሳዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ነጥብ ወስደዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ትላንት አዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ ፕሮግራም ተይዞለት የነበረውና ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሊጉ መሪ ሀዋሳ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ከመጀመሩ 20 ደቂቃዎች በፊት በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ጨዋታው ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወሳል፡፡

ከትላትናው የደጋፊዎች ግጭት በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የስታዲየሙን ጸጥታ ሁኔታ ከሚያስጠብቀው አካል ጨዋታው መቀጠልና መካሄድ የሚያስችል ማረጋገጫ ስለተሰጠን ጨዋታው መካሄድ አለበት ቢሉም በአንጻሩ ሀዋሳ ከተማዎች በተወሰኑ ደጋፊዎቻችን እንዲሁም በቡድን አባላቶቻችን ላይ ጉዳት ስለደረሰ ጨዋታውን አናካሂድም የሚል አቋም በመያዛቸው ጨዋታው ትላንት መካሄድ ሳይችል ቀርቷል። በዛሬው እለትም ሀዋሳ ከተማዎች በአቋማቸው ፀንተው ወደ ሀዋሳ ጉዞ ከጀመሩ በኃላ ከባቱ (ዝዋይ) ከተማ ዳግም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ጨዋታውን አድርገዋል፡፡መካሄድ ከነበረበት ጊዜ በ23 ሰዓት ዘግይቶ ዛሬ በከፍተኛ የጸጥታ ኃይል ቁጥጥር ታጅቦ በዝግ ስታዲየም የተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጥት ነው የተጠናቀቀው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሲዳማ ቡና ከተረታው ቡድን ውስጥ ምንተስኖት አዳነ እና አሜ መሐመድን አስወጥተው በሰልሀዲን በርጌቾና በኃይሉ አሰፋ ሲተኩ በአንጻሩ ሀዋሳ ከተማዎች በሜዳቸው አዳማ ከተማን ከረታው ቡድን በገብረመስቀል ዱባለ ምትክ አክሊሉ ተፈራን ብቻ በመቀየር ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡ ለ10 ዓመታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገለገለውና ባሳለፍነው ክረምት ከክለቡ ተለያይቶ አሳዳጊ ክለቡ ሀዋሳ ከተማን የተቀላቀለው አዳነ ግርማ በቅጣት ምክንያት የቀድሞ ክለቡን መግጠም ባይችልም በስታዲየም ተገኝቶ ጨዋታውን ተከታትሏል፡፡

በ4-2-3-1 የሚመስል መነሻ አሰላለፍ ጨዋታውን የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች ሁለት ተፈጥሮአዊ የሆኑ የመስመር ተከላካዮችን በ10 ቁጥር ሚና ከተሰለፈው ታፈሰ ሰለሞን ግራና ቀኝ ዳንኤል ደርቤ እና ደስታ ዮሀንስን መጠቀማቸው አግራሞትን የጫረ ነበር። ይህም የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ የሆኑትን ሁለቱ የመስመር ተከላካዮቹ አብዱልከሪም መሐመድ እና ኄኖክ አዱኛን እንቅስቃሴ በመገደቡ ረገድ የተዋጣለት ውሳኔ ሆኖ አልፏል፡፡

ሁለቱም ቡድኖች ቀጥተኛ አጨዋወትን ምርጫቸው በሚያደረጉ ሁለት ቡድኖች መካከል እንደመከናወኑ ጨዋታው እምብዛም ማራኪ የሚባል እንቅስቃሴ አልታየበትም፡፡ ቶሎ ቶሎ በሚደረጉ የረጃጅም ኳሶች ልውውጦች ታጅቦ የተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ከፍተኛ የሆነ የኃይል አጨዋወት፣ አካላዊ ንኪኪዎችና ጉሽሚያዎች የበዙበት ነበር፡፡

ሀዋሳ ከተማዎች በተሻለ የመልሶ ማጥቃት ቁመና ላይ ባይገኙም ኳስ ሲያጡ ከእስራኤል እሸቱ በስተቀር ከኳስ ኃላ በጣም ጠቅጠቅ ብለው ሲከላከሉ ተስውሏል ፤ ነገርግን ኳስ በቁጥጥራቸው ስር ስትገባ ደግሞ በተለይም በዳንኤል ደርቤ በኩል ከሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በአንጻሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው አጋማሽ ከሁለቱ ቡድኖች በተሻለ ምንም እንኳን ኳሶቹ ከጨዋታ ውጪ ቢባሉም በ20ኛውና በ27ኛው ደቂቃ ላይ ከአብዱልከሪም መሀመድና ከሄኖክ አዱኛ በቀጥታ የተሻገሩትን ረጃጅም ኳሶች ተጠቅሞ አቤል ያለው የሞከራቸውን ኳሶች አንዱን ተክለማርያም ሲያድንበት ሌላኛው ደግሞ ግብ ብትቆጠርም ዳኛው ሳያፀድቋት ቀርተዋል፡፡

 

ከነዚህ ሙከራዎች ውጭ በተለይ በ14ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ አሰፋ ወደ ቀኝ ያደላውን የቅጣት ምት አሻምቶ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ ፍሪምፓንግ ሜንሱ ተንሸራቶ ሳይደርስባት የቀረው ኳስ አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች ምንም አይነት የግብ ማግባት አጋጣሚን መፍጠር ባልቻሉበት በዚሁ በመጀመሪያ አጋማሽ ከተከላካይ እንዲሁም አማካይ ስፍራ ተጫዋቾች በቀጥታ የሚጣሉ ኳሶችን ከሶስቱ የጊዮርጊስ ተጫዋቾች በማሸነፍ የግብ እድል ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ እንቅስቃሴ እንደመጀመሪያው ሁሉ አሰልቺ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ላይ አምና በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ከዩጋንዳው ኬሲሲኤ ጨዋታ ወዲህ ከሜዳ ርቆ የነበረው ሰልሀዲን ሰዒድ በኃይሉ አሰፋን ተክቶ በመግባት የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረግ የቻለውም በዚሁ አጋማሽ ነበር፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መሀል ሜዳ ላይ ከሶስቱ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ፊት ላይ ተቆርጠው ከመቅረት ጋር ተዳምሮ የተወሰደባቸውን የመሐል ሜዳ የቁጥር ብልጫ ለመቅረፍ ከአንድ የሀዋሳ ከተማ አጥቂ ጋር በትይዩ ሲቆሙ ከነበሩት ሶስት የመሀል ተከላካዮች ውስጥ በተወሰነ መልኩ በሁለተኛው አጋማሽ አስቻለው ታመነ ተነጥሎ ወደ መሀል ሜዳ እየገባ ለመጫወት ነፃነት ተሰጥቶት ተስተውሏል። በ69ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ዘለቀ ከሀዋሳዎች ሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት ኳስ ከግቡ አግዳሚ በላይ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት ኳስ በጨዋታው የታየችው የተሻለችው ሙከራ ነበረች፡፡

በጨዋታው በግሉ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ወጣቱ አጥቂ እስራኤል እሸቱ በቀጥታ ከተከላካዮች የሚላኩለትን ኳሶች ለመጠቀም ከጊዮርጊስ ተከላካዮች ጋር ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነበር። በዚህ መልኩ ያገኛትን ኳስ በ64ኛው ደቂቃ ወደ ግብ የላካትና ፓትሪክ ማታሲ ያዳነበት ኳስ ጥረቱን ማሳያ ነበረች፡፡

ጨዋታው 0ለ0 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን ወደ 11 በማሳደግ በመሪነቱ ቀጥሏል፡፡