ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደደቢት ከ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ

ደደቢት እና ወልዋሎ መቐለ ላይ የሚገናኙበትን የ7ኛ ሳምንት ጨዋታ አስመልክቶ የሚነሱ ነጥቦችን እንደሚከተለው እናስቃኛችኋለን።

ነገ ትግራይ ስታድየም ላይ ደደቢት የመጀመሪያ የሊግ ነጥቡን እና የመጀመሪያ ጎሉንም ጭምር ለማግኘት በሚያልምበት ጨዋታ ወልዋሎ ዓ/ዩን ያስተናግዳል። የመጨረሻ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ደደቢት የዘንድሮው ጉዞውን ከባድ የሚያደርጉበት አራት ሽንፈቶች ከገጠሙት በኋላ በስድስተኛው ሳምንት ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ሊያደርግ የነበረው ጨዋታ ተላልፎ ነው በድሬዳው ከተረታበት የሐረሩ ጨዋታ መልስ ወልዋሎን የሚገጥነው። በተመሳሳይ መልኩ አስከፊ ጅማሮን አድርጎ የነበረው ወልዋሎ ዓ/ዩ ከተጋጣሚው በተለየ ሁኔታ ባለፉት ሳምንታት መሻሻሎችን አሳይቷል። ቡድኑ ምንም እንኳን በሜዳው ያደረገውን ጨዋታ ያለግብ ቢጨርስም ደቡብ ፖሊስ እና መከላከያን መርታት መቻሉ ከነጉው ጨዋታ አስቀድሞ ከተከታታይ ሽንፈቶቹ አገግሞ በሊጉ ወገብ ላይ እንዲቀመጥ አስችሎታል።

በጨዋታው ደደቢቶች ያለምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና ከሙሉ ስብስባቸው ጋር ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ሲጠበቅ በወልዋሌ በኩል ግን የተሰሙ የጉዳት ዜናዎች አሉ። በዚህም የቢጫ ለባሾቹ  ተጫዋቾች ዳንኤል አድሀኖም፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ኤፍሬም ኃ/ማርያም የማይሰለፉ ሲሆን ዳዊት ፍቃዱ እና አስራት መገርሳ ግን አገግመው ከአርባ ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ ጨዋታ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።

በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የተሻለውን የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ለመውሰድ የሚደረገው ፍልሚያ ዋነኛ ተጠባቂ ጉዳይ ነው። ተጋጣሚዎቹ በአጭር ቅብብል ላይ የተመሰረተው አቀራረባቸው በተመሳሳይ መንገድ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንዲሞክሩ የሚያደርጋቸው ነው። በመሆኑም የአማካይ መስመር ተሰላፊዎቻቸው ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ለፊት አጥቂዎቻቸው ለማድረስ የሚጥሩባቸው እና የፊት አጥቂዎቻቸውም ወደ ኋላ ተስበው ኳሶችን ለመቀበል በሚያደርጓቸው ጥረቶች ውስጥ ጨዋታው ከመስመር እንቅስቃሴዎች ይልቅ መሀል ላይ በሚኖረው ፍልሚያ የመወሰን ዕድሉን ከፍ ያደርጉታል። በቦታው የቁጥር ብልጫ ሊኖራቸው ከሚችሉት እና ይህኛው ዕቅድ ብቻ ላይ ይበልጥ ትኩረት ከሚሰጡት ደደቢቶች በተለየ ሁኔታ ግን መሀል ላይ የሚቋረጡ ኳሶችን በድንገተኛ ጥቃት ኳስ ይዘው ለመግባት የሚሞክሩት ወልዋሎዎች ተደጋጋሚ የግብ ዕድል የመፍጠር አጋጣሚው ሊኖራቸው ይችላል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወልዋሎ ወደ ሊጉ በመጣበት የአምናው የውድድር ዓመት ቡድኖቹ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል።

– በጨዋታዎቹ በተመዘገቡት ውጤቶች በመጀመሪያው ዙር  አዲስ አበባ ላይ ደደቢት 3-1 ሲያሸንፍ ዓዲግራት ላይ ደግሞ ወልዋሎ የ1-0 ድል አስመዝግቦ ነበር።

– ደደቢት እስካሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያላስቆጠረ ሲሆን ሰባት ግቦችን አስተናግዷል።

– ወልዋሎ ዓ/ዩ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግብ አልተቆጠረበትም። ቡድኑ እስካሁን ያገባቸው ሁለት ግቦች የተገኙት ደግሞ መከላከያን እና ደቡብ ፖሊስን በተመሳሳይ የ1-0 ውጤት ሲያሸንፍ ነው።

ዳኛ

– ከመጀመሪያው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ደቡብ ፖሊስ እና መከላከያ ያደረጉትን ጨዋታ በመዳኘት አምስት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን የመዘዘው ሣህሉ ይርጋ ይህን ጨዋታ ለመምራት ተመድቧል። ሣህሉ በቡና እና ድሬዳዋ ጨዋታም ላይም በአራተኛ ዳኝነት አገልግሏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደደቢት (4-3-3) 

ረሺድ ማታውሲ

መድሀኔ ብርሀኔ – ኤፍሬም ጌታቸው – ክዌኪ አንዶህ – ኄኖክ መርሹ

አብርሀም ታምራት – የአብስራ ተስፋዬ

እንዳለ ከበደ – ዓለምአንተ ካሳ – አቤል እንዳለ

አኩዌር ቻሞ

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-3-3)

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን –  ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

አማኑኤል ጎበና – አስራት መገርሳ – አፈወርቅ ኃይሉ

አብዱርሀማን ፉሴይኒ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ኤፍሬም አሻሞ