ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ነገ ከሚደረጉ የሰባተኛ ሳምንት መርሐ ግብሮች መካከል ሐረር ላይ ድሬዳዋ ፋሲልን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በዛሬው ቅድመ ዳሰሳችን የምንመለከተው የመጀመሪያ ጨዋታ ይሆናል። 

ምናልባትም ድሬዳዋ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ ሐረር ላይ ያደርገዋል ተብሎ በሚጠበቀው ጨዋታ እስካሁን ሽንፈት አድርሶበት የማያውቀው ፋሲል ከነማን ያስተናግዳል። ከጅማ አባ ጅፋር በመቀጠል ከመከላከያ ዕኩል ጥቂት ጨዋታዎችን ያደረጉት ድሬዎች በኢትዮጵያ ቡና ተሸንፈው ሊጉን ቢጀምሩም ከደደቢት እና ወልዋሎ ጨዋታዎች ያገኟቸው አራት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጡ አስችሏቸዋል። ሳምንት በሜዳው ከመከላከያ ጋር ነጥብ የተጋራው ፋሲል ከነማ ደግሞ አምስት ጨዋታዎችን አድርጎ በስምንት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ፋሲልም እንደ ነገ ተጋጣሚው ሁሉ ዓመቱን በሽንፈት ቢጀምርም በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ሁለት አሸንፎ እና ሁለት አቻ ተለያይቶ ነው ወደ ሐረር የሚያቀናው።

በድሬዳዋ ከተማ የጉዳት ዝርዝር ውስጥ ተካተው ከነበሩት በረከት ሳሙኤል፣ ዳኛቸው በቀለ ፣ ምንተስኖት የግሌ ፣ አማረ በቀለ ፣ ራምኬል ሎክ ፣ ኃይሌ እሸቱ እና ሀብታሙ ወልዴ መካከል አብዛኞቹ እንዳገገሙ የተሰማ ሲሆን አማረ እና ዳኛቸው ግን አሁንም ጉዳት ላይ ይገኛሉ። በፋሲል ከነማም በኩል የረጅም ጊዜ ጉዳት ከገጠመው አጥቂው ፋሲል አስማማው ውጪ ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡

የተለያየ የጨዋታ አቀራረብ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ነገም በተመሳሳይ አኳኋን ወደ ጨዋታው እንደሚገቡ ይጠበቃል። ኳስን ተቆጣጥረው መጫወትን ምርጫቸው የሚያደርጉት ፋሲሎች በነገው ጨዋታ የመሐል ሜዳ የበላይነቱን መያዝ የሚከብዳቸው ባይመስልም የድሬዳዋን የተከላካይ መስመር ለማለፍ ሊቸገሩ እንደሚችሉ ይታሰባል። በዚህም የአፄዎቹ የማጥቃት ባህሪን የተላበሱ አማካዮች እና ሦስቱ አጥቂዎች በድሬ የተከላካይ እና አማካይ ክፍል መሀል የሚኖረው ቦታ ላይ ክፍተሮችን ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት በጨዋታው ተጠባቂ ይሆናል። ጨዋታው በሌላ በኩል ባለሜዳዎቹ ድሬዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ሊይዝ ከሚችለው ተጋጣሚያቸው ጀርባ ለመግባት በቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶች የፊት አጥቂዎቻቸውን ፍጥነት ሊጠቀሙ የሚችሉበትም ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ከግብ መስመሩ ገፋ ያለ አቋቋም ሊኖረው የሚችለው የፋሲል የኋላ መስመር ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም ይገመታል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው ድሬዳዋ አንዱን ሲያሸንፍ በሦስቱ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ድሬዳዋ  ሁለት ፣ ፋሲል አንድ ጎሎች አስቆጥረዋል።

– ድሬዳዋ ባለሜዳ ሆኖ በተደረጉ ጨዋታዎች ባለሜዳዎቹ በ2009 ከፋሲል ጋር የተገናኙበትን የመጀመሪያ ጨዋታ 1-0 ሲያሸንፉ አምና ደግሞ ያለግብ ተለያይተዋል።

– በእስካሁኑ የቡድኖቹ ግንኙነት ፋሲል ከነማ ድል አልቀናውም።

– ድሬዳዋ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገዱ ሲሆን ከመረብ ያገናኟቸው ሦስት ግቦች የተገኙት ደግሞ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ነበር።

– ፋሲል ከተማ እስካሁን ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ግብ ሳይስቆጥር የወጣው በአንዱ ላይ ብቻ ነው። በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ መረቡን ሳያስደፍር ከሜዳ ወጥቷል።

ዳኛ

– ከከፍተኛ ሊግ አድጎ በአራተኛው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስሑል ያደረጉት ጨዋታ ላይ የተመደበው እና ምንም ካርድ ሳይመዝ የጨረሰው ብርሀኑ መኩሪያ ይህን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ
ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ዘነበ ከበደ – አንተነህ ተስፋዬ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሀንስ

ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ –  ሲላ አብዱላሂ – ራምኬል ሎክ

ኢታሙና ኬይሙኒ – ገናናው ረጋሳ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ – ሙጂብ ቃሲም – አምሳሉ ጥላሁን

ኤፍሬም ዓለሙ – ሐብታሙ ተከስተ – በዛብህ መለዮ

ሽመክት ጉግሳ – ኢዙ አዙካ – ሱራፌል ዳኛቸው