ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት የዛሬ ብቸኛ መርሐ-ግብር የነበረው የመቐለ 70 እንደርታ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ከወትሮው ለየት ባለ የደጋፊዎች ድባብ በጀመረው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ከባለፈው ሳምንት ጨዋታ ስብስባቸው ያሬድ ሀሰን፤ ሥዩም ተስፋዬ እና ያሬድ ከበደን አስወጥተው በአንተነህ ገ\ክርስቶስ ፣ አማኑኤል ገ\ሚካኤል እና አቼምፖንግ አሞስ ተክተዋል። በአንፃሩ እንግዶቹ ጊዮርጊሶች ከባለፈሰው ሰኞ ጨዋታ አሰላለፋቸው በበኃይሉ አሰፋን ምትክ አሌክስ አርቶማል ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የተከላካይ ክፍላቸው ወደ መሃል ሜዳ አስጠግተው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለማግኘት ሲራኮቱ ቢታይም በተጨናነቀው ቀጠና ምክንያት አንዳቸውም በጥሩ ፍሰት ወደ ተጋጣሚ ክልል መግባት አልቻሉም። በዚ መሃል እንግዶቹ ጊዮርጊሶች መጀመርያ ከነበረው 3-4-3 አጨዋወታቸው ወደ 3-4-2-1 በመቀየር የአጥቂዎቹ የተለጠጠ ቦታ አያያዝ በማስቀረት የተሻለ ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል። በተለይም ከዋናው አጥቂ በቅርብ ርቀት እንዲጫወቱ የተደረጉት አሌክስ አርቶማል እና አቡበከር ሳኒ ከማጥቃቱ ባሻገር መቐለዎች ኳስ በሚመሰርቱበት ወቅት ዋነኛ ሚና የሚወጡትን ሚካኤል ደስታ እና ጀብሪል መሃመድን በመሸፈን የመቐለን የኳስ አመሰራረት ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲፈጥሮ ብሎም ተጋጣሚ ቡድን በተደጋጋሚ ኳስ ከራሱ ክልል እንዳይመሰርት አድርገዋል። ሆኖም በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ የተንቀሳቀሱት ጊዮርጊሶች ሙሉዓለም መስፍን ካደረገው ሙከራ ውጭ ሌላ የግብ አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም።

ቀስ በቀሰ ወደ ጨዋታው የገቡት መቐለዎች በ18ኛው ደቂቃ ላይ ኦሴይ ማዋሊ ካደረጋት ጥሩ ሙከራ በኋላ የተሻለ ተንቀሳቅሰው የጎል እድሎችም ፈጥረዋል። በተለይም አማኑኤል ገ/ሚካኤል በጥሩ ሁኔታ ተጫዋቾች አልፎ ገብቶ ያመከናት እና ከቅጣት ምት ያደረጋት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ከዚች ሙከራ ውጭ ሳሙኤል ሳሊሶ ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ አሞስ መትቶ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡት ኳስም ይጠቀሳል። በጨዋታው ከተከላካዮች ጀርባ የሚፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ረጃጅም ኳሶችን ሲጥሉ የነበሩት ጊዮርጊሶች ጫና ፈጥረው መንቀሳቀስ ቢችሉም አቤል ያለው በግሉ ከሚፈጥራቸው እድሎች ውጭ ንፁህ የግብ እድል መፍጠር ተስኗቸው ታይተዋል።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ሲታይ የመቐለ ብልጫ በታየበት ጨዋታ በሁለቱም በኩል በርካታ ንፁህ የግብ እድሎች የመከኑበት ነበር። አማኑኤል በጥሩ ሁኔታ የሰጠው ኳስ ተጠቅሞ ማውሊ መትቶ ሰልሃዲን በርጊቾ ተደርቦ ባወጣው ሙከራ የተጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ መቐለዎች ጫና ፈጥረው በተቀሳቀሱባቸው ደቂቃዎች በርካታ እድሎች ፈጥረዋል። በተለይም አማኑኤል ከማውሊ የተቀበላትን የግንባር ኳስ መትቶ ማታሲ በሚያስደንቅ ብቃት ያዳናት ባለሜዳዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ሲታይ ተዳክመው የታዩት ጊዮርጊሶችም ሰልሃዲን ሰዒድ ተቀይሮ ከገባ በኋላ የተሻሉ የጎል ሙከራዎች አድርገዋል። ሰልሃዲን ከአቤል የተሻማለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ኦቮኖ ያዳነበት እና በተመሳሳይ አቤል ያሻማውን በግሩም ሁኔታ መትቶ ኦቮኖ በሚያስደንቅ ብቃት ያዳነው እንግዶቸ ከፈጠሯቸው እድሎች መካከል ይጠቀሳሉ።

ያሬድ ከበደ እና ዮናስ ገረመውን ቀይረው በማስገባት አጥቅተው ለመጫወት የሞከሩት መቐለዎች የጊዮርጊስ ተጫዋች ከጨዋታ ውጭ ነው ብለው በተዘናጉበት ወቅት አማኑኤል ሾልኮ ከርቀት ባደረጋት ሙከራ የጎል እድል ሲፈጥሩ በጨዋታው መጠናቀቅያ ሰዓት ጊዮርጊሶች ያደረጓት ሙከራም በመጨረሻ ሰዓት ጨዋታውን አሸንፈው ለመውጣት ያቃረበቻቸው ነበረች። ሙሉዓለም መስፍን ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ የመታት ኳስ ከጎሉ ቅርብ ርቀት የነበረው አሌክስ ተሰማን ነክታ ወደ ውጭ ወጣች እንጂ።

ጨዋታው ያለ ጎል መጠናቀቁን ተከትሎ ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በተገናኙባቸው ሦስቱም ጨዋታዎች ሳይሸናነፉ ነጥብ መጋራት ችለዋል።