ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ድል አስመዝግቧል

ከሦስተኛው ሳምንት የተላለፈው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የጅማ አባ ጅፋር ተስተካካይ ጨዋታ በጊዮርጊስ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች መቐለ ላይ ያለግብ በተጠናቀቀው ጨዋታ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አሌክስ ኦሮትማልን አሳርፈው ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ቆይቶ በቅርቡ ተቀይሮ ሲገባ ይታይ የነበረው ሳላዲን ሰዒድን አስገብተዋል። በጅማ አባ ጅፋር የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ደግሞ ከአል አህሊው የመልስ ጨዋታ ፊት መስመር ላይ ሁለት ለውጦች ተደርገዋል። በዚህም መሰረት ኤርሚያስ ኃይሉ እና ማማዱ ሲዲቤ በአስቻለው ግርማ እና ቢስማርክ አፒያን ምትክ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታው ከእረፍት በፊት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የታየበትን ፍጥነት ይዞ መቀጠል ያልቻለ ነበር። በጥሩ መነቃቃት የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻለ ጉልበት ያለው አጨዋወት ይዘው በመግባት ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ አጋማሽ ገፍተው በመጫወት በሦስት አጋጣሚዎች የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በአመዛኙ ኄኖክ አዱኛ በተሰለፈበት የቡድኑ የግራ ክፍል ከተነሱት እነዚሁ ሙከራዎች ውስጥ ሳላዲን ሰዒድ በ3ኛው እና 13ኛው ደቂቃዎች አክርሮ የሞከራቸው ኳሶች ሲጠቀሱ ሁለቱም ዳንኤል አጄዬን እምብዛም አላስቸገሩትም። ከቡድኑ ሁለት አጥቂዎች ጀርባ በመሆን ከኄኖክ ጋር ጥሩ የቅብብል ጥምረት ሲፈጥር የታየው አቡበከር ሳኒም 7ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ገብቶ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ከግቡ ቋሚ ቅርብ ርቀት ወጥቷል።

ምንም እንኳን ወደ ኋላ ማፈግፈግን ምርጫቸው ያደረጉ የማይመስሉት ጅማ አባ ጅፋሮች እነዚህ ሙከራዎች በተሰነዘሩባቸው ወቅቶች በራሳቸው ሜዳ ለመቅረት ቢገደዱም የማጥቃት ሙከራዎችን ማድረጋቸው ግን አልቀረም። ሆኖም በመጀመሪያው አጋማሽ ለግብ የቀረበ ንፁህ የሚባል የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። የጊዮርጊሶቹ ናትናኤል እና የሙሉዓለም ጥምረት መሐል ለመሐል ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ያገዳቸው የሚመስሉት አባ ጅፋሮች በመስመር አጥቂዎቻቸው ዲዲዬ ለብሪ እና ኤርሚያስ ኃይሉ አማካኝነት ነበር ወደ ጊዮርጊስ ሳጥን ለመግባት የሚሞክሩት። ያም ቢሆን ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር በሁለቱ የተጋጣሚያቸው መስመር ተመላላሾች ፈጣን የመከላከል ሽግግር ምክንያት ውጤታማ ሆኖ አልታየም።


በተመሳሳይ በባለሜዳዎቹም በኩል የተደረጉት ሙከራዎች ከ13ኛው ደቂቃ በኋላ መቀጠል አልቻሉም። የአባ ጅፋር የግራ እና ቀኝ መስመሮች መከላከል መጠናከር እና ክፍተቶችን ሲፈጥር የነበረው አቡበከር መቀዛቀዝ ደግሞ ለዚህ ምክንያቶች ነበሩ። በመሆኑም አልፎ አልፎ በድንግተኛ ጥቃቶች የቡድኖቹ አጥቂዎች ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክልል ሲገቡ ከሚታዩባቸው አጋጣሚዎች ውጪ ከባባድ ሙከራዎች ያላስተናገደው የመጀመሪያ አጋማሽ ያለግብ ተጠናቋል።


ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ቢስማርክ አፒያን በኤርሚያስ ቀይረው ያስገቡት ጅማዎች የተሻለ ተነቃቅተው ወደ ግብ ሲደርሱ ታይተዋል። ሆኖም የቡድኑ የማጥቃት መንፈስ ከመከላከል ወረዳው በጥቂቱ ከፍ ያለ አቋቋም የነበረው የኋላ መስመሩን አጋልጦታል። የዚህ ምልክት የታየውም 53ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው ከኋላ የተጣለለትን ረጅም ኳስ ከከድር ኸይረዲን ኋላ ተነስቶ በመግባት ባደረገው ሙከራ ነበር። ከዚህ ሙከራ በኋላ ይበልጥ ጫናቸውን ያበረቱት ጊዮርጊሶች በስምንት ደቂቃዎች ልዩነት ውስጥ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል። የመጀመሪያው ፈጣኑ አቤል ያለው ከአብዱልከሪም የደረሰውን ኳስ ይዞ በመግባት ከአጄዬ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያስቆጠረው ነበር። በመቀጠልም 62ኛው ደቂቃ ላይ ጊዮርጊሶች ከአባ ጅፋር ተከላካዮች ካስጣሉት ኳስ አቤል ያለው ለሳላዲን ሰዒድ አቀብሎት ከአጃዬ ቀድሞ ኳሷ ጋር የደረሰው ሳላዲን ከመረብ ያገናኛት ነበረች።


ከግቦቹ መቆጠር በኋላ በተቀሩት ደቂቃዎች የነበረው እንቅስቃሴ ለተመጣጣኝነት የቀረበ ነበር። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ግን አፒያ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሞክሮት ኢላማውን ሳይጠብቅ ከቀረው ኳስ ውጪ ሌላ ሙከራ አልተስተናገደም። በአንፃሩ ለተጋጣሚያቸው ክፍተት ባለመስጠት እስከመጨረሸሻው የዘለቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሳላዲን ሰዒድ እና አቡበከር ሳኒ ከረጅም ርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎችን አድርገዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎሎች ሳይቆጠሩበት በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ከሦስት ጨዋታ በኋላ ማሸነፍ የቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ5 ጨዋታ ነጥቡን ስምንት አድርሶ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በውድድር ዓመቱ ሦስት ጨዋታዎች ብቻ ያደረገው ጅማ አባ ጅፋር በ4 ነጥቦች 13ኛ ላይ ይገኛል።