ሪፖርት | ሸገር ደርቢ ያለ ግብ ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ተከናነውኖ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

የኢፌዲሪ ሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጀምሮ በርካታ የመንግሥት ኃላፊዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የበላይ አመራሮች በተገኙበት በዚሁ ጨዋታ ከጨዋታው መጀመር በፊት በርካታ ኹነቶች ተካሂደዋል ፤ ከነዚህም መካከል ከሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተወከሉ 21 እናቶች ፊት የሁለቱ ክለብ የበላይ አመራር የሆኑት አቶ አብነት ገብረመስቀልና መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እርቀ ሰላም አውርደው በአንድ ላይ ተቃቅፈው የታዩበት ክስተት ትኩረት የሚስብ ነበር፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል በያዝነው ሳምንት አጋማሽ ጅማ አባጅፋርን 2-0 ከረታው የቡድን ስብስብ ምንም ቅያሪ ሳያደርጉ ተመሳሳይ የቡድን ስብስብ ይዘው ሲቀርቡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በሳምንቱ አጋማሽ ወልዋሎን1-0 ከረታው ቡድን ውስጥ አጥቂው ሱሌይማን ሎክዋን አስወጥተው ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱን አስገብተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከወትሮው በተለየ የቅዱስ ጊዮርጊሶችን 3-5-2 አደራደር ሊሰጣቸው የሚችለውን ጥቅም ለመጋራት በማሰብ በሶስት የመሀል ተከላዮች በመጠቀም ወደ 3-6-1 የቀረበ የሜዳ ላይ ቅርጽን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

ሁለቱም ቡድኖች ተቀራራቢነት ያላቸው የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች ቁጥር እንደመያዛቸውና ወደ መሀል እያጠበቡ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ከመብዛታቸው ጋር ተዳምሮ መሀል ሜዳው ላይ አላስፈላጊ የተጫዋቾች ክምችት ተፈጥሮ ኳሶች በሁለቱም ቡድኖች በኩል በፍጥነት ሲቆራረጡ ተስተውሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱም በኩል ከጨዋታው ክብደት የተነሳ በርካታ ግላዊ ስህተቶች እንዲሁም የኃይል አጨዋወቶች ይስተዋሉ ነበር። በዚህም አማኑኤል ዮሐንስ ባጋጠመው ጉዳት በ23ኛው ደቂቃ ላይ በዳንኤል ደምሴ ተቀይሮ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል፡፡

ይህ ነው የሚባል ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ባልታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኢትዮጵያ በሁለት አጋጣሚዎች ማለትም በ19ኛው እንዲሁም በ39ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ወደ ቀኝ አድልቶና መሐል ለመሐል የተገኙ የቆሙ ኳሶችን በጥሩ ሁኔታ ቢያሻማም በሁለቱም አጋጣሚዎች ቶማስ ስምረቱ የነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ኳሶችን ቢያገኝም በሁለቱም አጋጣሚ ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል፡፡ በአንጻሩ ወደ ግራ የመስመር ተመላላሹ ሔኖክ አዱኛ ባደላ መልኩ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲሞክሩ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ41ኛው ደቂቃ ሰልሀዲን ሰኢድ ራሱ ያሸነፈውን የመጀመሪያ ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ የላካትና ኢላማውን ሳትጠብቅ ከቀረችው ኳስ ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በዚሁ አጋማሽ ካሉሻ አልሀሰንና ሔኖክ አዱኛ በግላቸው ተጫዋቾችን እየቀነሱ ለማለፍ ያደርጉት የነበረው ጥረት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ሆኖ አልፏል፡፡ ከመሐል ሜዳው መጨናቀቅ ጋር ተዳሞሮ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 25 ደቂቃዎች ላይ በርከት ያሉ ረጃጅም ኳሶች የተስተዋሉ ሲሆን እምብዘም ሳቢ ያልነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ያለግብ ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ ሁለት ቡድኖች በጠሩ የግብ እድሎች ባይታጀብም የተሻለ ፉክክር ማሳየት ችለዋል፡፡ በ54ኛው ደቂቃ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኙትን የማዕዘን ምት አቤል ያለው አሻምቶ በኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ሲመለስ ካሉሻ አልሀሰን ያገኘውንና በረጅም ወደ ተቃራኒ የላከውን ኳስ አቡበከር ናስር ሊደርስበት ሲል ከግብ ክልሉ በፍጥነት የወጣው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ በአቡበከር ላይ በሰራው ግልፅ ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። በዚህም የተነሳ አማካዩ አቡበከር ሳኒን በመተካት ለዓለም ብርሃኑ ወደ ሜዳ ገብቶ ቀሪውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጨርሷል፡፡

ይህ ቀይ ካርድ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ላይ መጠነኛ የጨዋታ አቀራረብ ለውጥ እንዲያደርጉ ያስገደደ ነበር። የነበረው የተጫዋች ጉድለትን እንደ ቡድን በመንቀሳቀስ ለመሙላት ከመጣር ይልቅ በአመዛኙ በመጀመሪያ አጋማሽ የማጥቃት ነፃነት የነበራቸው ሁለቱ የመስመር ተመላላሾች አብዱልከሪም መሐመድ እና ሔኖክ አዱኛን እንቅስቃሴ በመገደብ በረጃጅሙ በሚላኩ ኳሶች ፈጣኑ አቤል እና ኳስ ይዞ የቡድን አጋሮችን ወደ ጨዋታ በማስገባት የተካነው ሰልሀዲን ሰዒድን ከተከላካይና ግብ ጠባቂ በቀጥታ በሚጣሉ ኳሶች ለማግኘትና ግቦችን ለማስቆጠር ሙከራ አድርገዋል፡፡

በአንጻሩ በጊዮርጊስ በኩል ተጫዋች በቀይ መውጣቱን የተመከቱት የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ተከላካዮን ቶማስ ስምረቱን አስወጥተው አጥቂው ሱሌይማን ሉክዋን በማስገባት ቅርጻቸውን ወደ 4-3-3 በመቀየርና በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም የመስመር ተመላላሾቹን ግልጋሎት አጥቶ የነበረው ቡና ከሎክዋ መግባት በኃላ የሜዳውን ስፋት በመጠቀም በኩል የተሻሉ ነበሩ፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ሱሊይማን ሉክዋ አልሀሰን ካሉሻ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ አክርሮ የመታውና ተቀይሮ የገባው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብጠባቂ ለዓለም ብርሃኑ የያዘበት ሙከራ የመጀመሪያ የጨዋታው ኢላማ የጠበቀ ሙከራ ነበር፡፡ በጊዮርጊሶች በኩል በ71ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው ከግራ መስመር ያሻገለትን ኳስ ሳልሀዲን ሰዒድ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣበት ኳስ አስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በ83ኛው ደቂቃ ላይ በጉዳት ከመጀመሪያው ሳምንት በኋላ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መሰለፍ ያልቻለው ጌታነህ ከበደ በክረምቱ አብሮት ከደደቢት ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለውን አቤል ያለውን ተክቶ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ላይ ክሪዚስቶም ንታምቢ በ87ኛው ደቂቃ ላይ በቀጥታ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የላካትና ወደ ውጪ ከወጣበት ኳስ ውጪ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳንመለከት ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ያለግብ ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡