የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-0 ደቡብ ፖሊስ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት አዳማ ከተማ ደቡብ ፖሊስን ስተናግዶ 1-0 ከረታበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡

” ከሊጉ ፉክክር እየራቅን ስለነበር የዛሬው ድል ደረጃችንን ከፍ ለማድረግ አጥቅተን ተጫውተናል” ሲሳይ አብርሃ – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው

“ዛሬ ቡድናችን በጣም ጥሩ ነበር ፤ የአሰላለፍ ለውጥ አድርገን በዛሬው ጨዋታ 4-4-2 በመጠቀም ያሉንን አራት አጥቂዎች በሙሉ ለመጠቀም ሞክረናል፡፡ በእንቅቃሴ ረገድ በሁለቱም አጋማሾች ጥሩ ነበርን። በመጀመሪያው አጋማሽ ሶስት የማግባት አጋጣሚዎችን አምክነናል ፤ በሁለተኛው አጋማሽም ይበልጥ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ስለነበረብን አጥቅተን ተጫውተናል፡፡ ከሊጉ ፉክክር እየራቅን ስለነበር በዛሬው ድል ደረጃችንን ከፍ ለማድረግ አጥቅተን ተጫውተናል፡፡ በአጠቃላይ ደጋፊውን እንዲሁም የቡድን አባላትን ለማመስገን እወዳለሁ። እስካሁን ድረስ በትዕግስት አብረውኝ ስለነበሩ፤ በቀጣይም ድጋፋቸው እንደማይለየን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡”

በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን ለማስጠበቅ ስለተከተሉት መንገድ

“የእኛ ቡድን በሊጉ ከሚገኙ ቡድኖች በተሻለ ሰዓት የማያባክን ቡድን ነው፡፡ ምክንያቱም በእኔ እምነት ሜዳ ውስጥ አንድ ኳስ እስካለ ድረስ ኳሱን ከያዝን ብዙ አማራጮች አሉን፤ ዋናው ጎል ስታስቆጥር እንደምታሸንፍ ካመንክ ተጨማሪ ጎሎችን ለማስቆጠር መንቀሳቀስ ትችላለህ፡፡”

ስላደረጉት የአሰላለፍ ለውጥና ምክንያቱ

“የከነዓን ማርክነህ በዛሬው ጨዋታ ላይ አለመኖር አንዱ ምክንያት ነው። ከዚህ ቀደም ይህን ቡድን (ደቡብ ፖሊስን) ሀዋሳ ላይ ሲጫወት ተመልክተነዋል። የመከላከል ባህሪን የተላበሰ ቡድን ነው። ረጃጅም ኳሶችን እየላክን በሁለት አጥቂዎች እንዲሁም በረከትና ቡልቻ በመስመር በኩል እገዛ እያደረጉ የቁጥር ብልጫ ወስደን ለመጫወት ሞክረናል፡፡”

 

” በግሌ ፍፁም ቅጣት ምቱ የተሰጠበት መንገድ አላሳመነኝም ” ያለው ተመስገን – ደቡብ ፖሊስ (ምክትል አሰልጣኝ)

ስለ ጨዋታው

“እንደአጠቃላይ ጨዋታ በፈለገነው መልኩ እየሄደ ነበር። በቅድሚያ ለማሸነፍ፤ ያ ካልሆነ ግን አቻ ለመውጣት ስትራቴጂ ነድፈን ነበር የመጣነው። በአጠቃላይ ሜዳ ላይ ይህንን እቅድ ለመተግበር የቸገረን ነገር አልነበረም፡፡ በስተመጨረሻ ላይ የተፈጠሩ ነገሮች ብዙ ደስ አይልም። ለእኔ በግሌ ፍፁም ቅጣት ምቱ የተሰጠበት መንገድ አላሳመነኝም፡፡”

ከግቧ መቆጠር በኋላ የተሻለ አጥቅተው ስለመጫወታቸው

“የትኛውም ቡድን ግብ ከተቆጠረበት በኋላ በፊት ከነበረው መንገድ በተሻለ ለመጫወት ይሞክራል። እኛም ያደረግነው ይህንን ነው፡፡ የማጥቃት ኃይላችንን ቁጥር ጨምረን በመጫወት ሞክረን እንጂ ከመጀመሪያው በተለየ ያደረግነው ነገር የለም፡፡”