የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 1-0 ሀዋሳ ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ሲዳማ ቡናን ከሀዋሳ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በሲዳማ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ሀዋሳዎች ይዘውት የመጡት አጨዋወት አስቸግሮን ነበር ” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና

ስለ ድሉ

በጣም ጠንካራ ጨዋታ ነበር። በተለይ ከእረፍት በፊት ተጋጣሚያችን ይዞት የመጣው አጨዋወትን ለመስበር ተቸግረን ነበር። ከእረፍት በኋላ ግን ፈጣን እንቅስቃሴን ሊያደርጉ የሚችሉ ተጫዋቾችን በመቀየር በተደጋጋሚ ጎል ጋር ለመድረስ ሞክረናል። ተቃራኒ ቡድን ሜዳቸውን እየሸፈኑ በረጃጅም ኳስ ነበር ሲወጡ የነበሩት። ያ ደግሞ ለተከላካዮቻችን አላስቸገረም። እኛም የነሱን ሰብረን ለመግባት ተቸግረን ነበር። ዞሮ ዞሮ ሶስት ነጥብ አግኝተናል። እንደ በፊቱ ዛሬ ጫና የሚፈጥር ኳስ አልተጫወትንም ብለን እናስባለን።”

ግርማንና ዮሴፍን በተመሳሳይ ቦታ ስለማሰለፋቸው

“ይህን በመጠቀማችን ተጠቅመናል። አንደኛ ዮሴፍ እና ግርማን መሐል ላይ ስናደርግ ብልጫውን ለመውሰድ ፈልገን ነው፤ ያ ደግሞ ተሳክቶልናል። ጥንቃቄንም ስለፈለግን ነው። ከዛ በኋላ ግን ግርማን ቀይረን አውጥተነዋል። ምክንያቱም ከመከላከሉ ይልቅ አጥቅቶ የሚጫወት ተጫዋች ስለነበረን በሱ ቀይረነዋል።

የአዲስ ግደይ በአጥቂ መጀመር

” አዲስን ከፊት አድርገን ያስጀመርንበት ምክንያቱ ጨዋታው ደርቢ በመሆኑ ነው። ብዙ የሀዋሳ ተጫዋቾች የተለምዶ ቦታውን ስለሚያውቁት ብንቀይረው የሆነ ነገር ይኖረናል ብለን ስላሰብን ነበር። በኋላ ላይ ወደ ቦታው አምጥተነው ጥሩ ተንቀሳቅሷል፤ ጠቅሞናልም። አዲስ ደረጃው የተለየ ስለሆነ እንጂ ሌሎቹም የተሻሉ በቡድኔ ውስጥ አሉ።

“ጎል ጋር የመድረስ አጋጣሚን አግኝተን መጠቀም አልቻልንም” አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

” ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ በተለይ ጎል ከገባብን በኃላ ያደረግነው እንቅስቃሴ የተሻለ ነው። የመጀመሪያ አርባ አምስት ደቂቃ እነሱ ጥሩ ነበሩ፤ ኳሱን ተቆጣጥረው ተጫውተዋል። የተጫዋቾቼ ጉጉት እና ደጋፊው ትንሽ ተፅዕኖ አድርጎብናል። ስንጀምር ኋላ ላይ ነበር ትኩረታችን። ካገቡብን በኃላ ነው ጥሩ የሆንነው። ከተቆጠረብን በኋላ ያደረግነውን እንቅስቃሴ ከመጀመርያውም ብናደርግ ጥሩ ነበር። ግን ጎል ጋር የመድረስ አጋጣሚን አግኝተን መጠቀም አልቻልንም”

የታፈሰ አለመኖር፣ የዳንኤል እና የደስታ የማጥቃት እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ…

” የታፈሰ አለመኖር የሚያስከፍለን ነገር ይኖራል። ታፈሰ የኳስ ችሎታው ጥሩ ነው። በሱ ምትክ ያስገባነው ተጫዋች ነጋሽ ታደሰ የመጀመሪያው ጨዋታ ስለሆነ ሲዋከብ አይተነዋል። እንደፈለግነው ሊሆን ስላልቻለ ወዲያው ነው የቀየርነው። ከዛ ሁለቱ አማካዮች ወደፊት እንዲሄዱ አደረግን። ከተከላካይ ፊት ልምድ ያለው አስጨናቂን ነበር ያደረግነው። ከዛ በኃላ የተሻለ ተንቀሳቅሰናል። በዚህም ጎል ጋር ደርሰናል ያለመረጋጋታችን እንጂ።

” የታፈሰ አለመኖር እንደጎዳን አይተናል። አዲስ ግደይንም በመስመር ስንጠብቀው በአጥቂነት መምጣቱ ያልጠበቅነው ነበር። ወደ መስመር ከወጣ እና ረጃጅም ኳሶች ከመጡ በኃላ ከባድ ነበሩ። ጎሉም ከዚህ አጨዋወት የመጣ ነበር። በተመሳሳይ የመስመር አጨዋወታችን ልክ አልነበረም። የዳንኤል እና የደስታ መቀዛቀዝም ክፍተቶችን ፈጥሮብናል። “