የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልዋሎ ዓ/ዩ 0-0 ፋሲል ከነማ

ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ የነበረው የወልዋሎ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ያለ ጎል ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

“ጨዋታው ሚዛናዊ እንደመሆኑ ውጤቱ ተገቢ ነው” ፀጋዬ ኪዳነማርያም

ጨዋታው ጥሩ ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ እኛ የተሻልን ነበርን። ሁለተኛ አጋማሽ ደግሞ በኳስ ቁጥጥር ረገድ እነሱ የተሻሉ ነበሩ። በመሃል ሜዳ ተሰላፊዎች ላይ የተጫዋቾች ምርጫ ጥበት ነበረብን። ልምምድ ሳይሰሩ ያስገባናቸው ተጫዋቾችም ነበሩ። ሆኖም ውጤቱ በዚ በማለቁ ደስተኛ ነኝ። በተለይም በሠላም ማለቁ ደስ ብሎኛል። ጨዋታው በዘጠና ደቂቃው ስናየው ሚዛናዊ እንደመሆኑ ውጤቱ ተገቢ ነው ባይ ነኝ።

መስመሩን አልፋለች ብለው ጥያቄ ስላነሱባት የጎል ሙከራ

” በርግጥ እዚ ሆነን ስናየው ጎል ይመስላል። ግን ለሁኔታው ቅርብ የነበረው መስመር ዳኛው ነው እና ከዚ በላይ ምንም ማለት አልችልም። ”

ስለ ተጫዋቾች ጉዳት እና ተያያዥ ጉዳዮች

” እኛ ዛሬ የጎዳን ብርሃኑ ቦጋለ ከነጉዳቱ ነው ጨዋታው የጨረሰው። ኦዶንጎም ሳምንቱን ሙሉ ልምምድ ሳይሰራ ነው ያሰለፍነው። የተጫዋቾች ጉዳት መበራከቱ ጎድቶናል። ከዚ በተጨማሪ የዋለልኝ ገብረ እና አስራት መገርሳ ግልጋሎት አላገኘንም። ጎል በማስቆጠር ረገድም ክፍተቶች አሉብን። በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ዕድሎች አግኝተን ነበር አልተጠቀምንባቸውም ። ባጠቃላይ ስናየው ግን ፋሲል ከማም በተጫዋቾች ጥራት እና ጥልቀት ከኛ የተሻለ ስለነበር ጨዋታው ፈታኝ ነበር።

” በሜዳችን ሙሉ ሶስት ነጥብ ብናገኝ ጥሩ ነበር። ሆኖም ከነበረው የሜዳ እንቅስቃሴ እና የቡድን ጥልቀት ችግር ውጤቱ ጥሩ ነው። ከዛ በተጨማሪ ደጋፍያችን ላሳየው አደጋገፍ ማመስገን እፈልጋለው።”

” ጨዋታው በዚህ መልክ ማለቁ በጣም ደስ ይላል” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

” መጀመርያ ጨዋታው በሰላም ተጀምሮ በሰላም ማለቁ ትልቁ ነገር ነው። ያ በጣም አስደስቶኛል። ስንመጣ ስጋት ነበረን፤ ምክንያቱም ከረጅም ግዜ በኋላ ነው ጨዋታው የተደረገው። ስለዚህ ጨዋታው በዚህ መልክ ማለቁ ደስ ይላል።

ወደ ጨዋታው ስመለስ ከዕረፍት በፊት እና በኋላ የተለያየ መልክ ነበረው። ከዕረፍት በፊት ቡድናችን እርጋታ አልነበረውም። በነሱ በኩል ደግሞ ከፍተኛ መነሳሳት ነበር። ከዕረፍት በኋላ ግን ችግራችን ቀርፈን ገብተናል። ቢያንስ ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት አድርገናል። ባጠቃላይ ጨዋታው መጥፎ አይደለም። ”

የወልዋሎ ተጫዋቾች ኳስ መስመር አልፏል ብለው ስላነሱት ጥያቄ

” እኔንጃ፤ ምናልባት ይህን ግብ ከሆነም ካልሆነም ሊያይ የሚችለው የመስመር ዳኛው ነው። እሱም የጨዋታው አንድ አካል ስለሆነ ስለ እሱ ብዙ ማለት አልችልም። ምክንያቱም ጥያቄው የተነሳበት ቦታ በኔ በኩል አልነበረም። ስለዚ ጎል ሊሆን ይችላል አይሆንም ማየት ይከብዳል። ጨዋታው ከዛ በላይ ግብ ማስተናገድ ይችል ነበር። በኛም በነሱ በኩልም ባጠቃላይ ጥሩ ነው። ”

ስለ መቐለ ከተማ ቆይታቸው

“ቆይታችን አልተጠናቀቀም። ይሄ ጥያቄ መጨረሻ ቀን ላይ ቢሆንልኝ፤ እስካሁን ባለው ግን ደስተኛ ነኝ። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *