ሪፖርት | ትኩረት የሳበው የወልዋሎ እና የፋሲል ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በዘጠነኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ የተካሄደው ብቸኛ የዕለቱ መርሐ ግብር በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጥቅምት 26 ቀን 2010 በወልዋሎ እና ፋሲል ከነማ መካከል ከተካሄው ጨዋታ በኋላ በትግራይ እና አማራ ክልል ክለቦች መካከል የተካሄዱ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ ሲከናወኑ ቆይተው በዘንድሮ የውድድር ዓመት በየሜዳቸው ጨዋታዎቹ እንዲደረጉ በተደረሰ ስምምነት መሰረት የመጀመርያው ጨዋታ በዛሬው እለት ተከናውኗል። የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሰውነት ቢሻው (ኢንስትራክተር) በተገኙበት በተደረገው በዚህ ጨዋታ ስለ ሠላም የሚሰብኩ ባነሮች እና ቲሸርቶች የተስተዋሉ ሲሆን ጨዋታውም ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ ተከናውኗል።

ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት ከጅማ አባ ጅፋር አቻ ከተለያየው ስብስባቸው አስራት መገርሳን በአማኑኤል ጎበና ቀይረው ሲገቡ ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው ወደ ሐረር አቅንቶ አሸንፎ ከተመለሰው ስብስባቸው አምሳሉ ጥላሁንን በሰለሞን ሃብቴ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ጥሩ የኳስ ፍሰት፣ ተመጣጣኝ ፉክክር እና ጥቂት ንፁህ የግብ እድሎች በተፈጠሩበት የመጀመርያው አጋማሽ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ  እንግዳዎቹ ፋሲሎች በራሳቸው የግብ ክልል ከሚያደርጓቸው ቅብብሎች ውጭ ይህ ነው የሚባል ንፁህ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በቡድኖች በኩል ስኬታማ የሆኑ የማጥቃት ሂደቶች ባይታዩበትም በአንፃራዊነት ወልዋሎዎች የተሻሉ ነበሩ ፤ በተለመደው የመስመር አጨዋወታቸው ለማጥቃት የሞከሩት ቢጫ ለባሾቹ በርከት ያሉ ዕድሎች ሲፈጥሩ በተለይም ፕሪንስ ሰቨሪንሆ አክርሮ መቷት ወደ ውጭ የወጣችው እና ብርሃኑ ቦጋለ ከግማሽ ሜዳ አለፍ ብሎ ያደረጋት ሙከራ  የተሻሉ ለጎል የቀረቡ ነበሩ።

የወልዋሎ ሶስቱ የፊት መስመር ተጫዋቾችን ጫና ተቋቁመው በጥሩ ሁኔታ ኳስ መመስረት የተሳናቸው ፋሲል ከነማዎችም አልፎ አልፎ በጥሩ ፍሰት ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉም ለብቸኛ አጥቂያቸው ኢዙ ኢዙካ ይህ ነው የሚባል ጥሩ የጎል ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም አጥቂው ከዕረፍት በፊት በሁለት አጋጣሚዎች ጥሩ የግብ ሙከራ ከማድረግ ግን አልቦዘነም። በ45ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ያደረጋት ሙከራም በፋሲል ከነማ በኩል ከተሞከሩት የተሻለ ወደ ግብ የቀረበች ነበረች። በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ወልዋሎዎች በሁለት አጋጣሚዎች መርተው ወደ ዕረፍት ለማምራት ተቃርበው በተለይም አፈወርቅ ኃይሉ ከማዕዝን አሻምቷት ቢንያም ሲራጅ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ የላካት ኳስ የፋሲል ተከላካዮች ተረባርበው ያወጧት ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ሲታይ የተሻለ የፉክክር መንፈስ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች ሁለት ቅያሪዎች በማድረግ ወደ ጨዋታው ሲገቡ ቡድኑም ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ሚዛናዊ ሆኗል። በተለይም ከድር ኩልባሊ ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኤፍሬም ዓለሙ ቡድኑ በመጀመርያው አጋማሽ ያጣውን ሚዛን በመመለስ የአምበሳው ድርሻ ይወስዳል።

ብርሃኑ አሻሞ ከቅጣት ምት መትቶ ጀማል ጣሰው በድንቅ ብቃት ባወጣው ሙከራ የጀመረው የሁለተኛው አጋማሽ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በርከት ያሉ ሙከራዎች ታይተውበታል። በወልዋሎ በኩል አማኑኤል ጎበና ከማዕዘን የተሻማችለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት፤ በፋሲል ከነማዎች በኩልም ሱራፉኤል ዳኛቸው ከርቀት ያደረጋት፣ በ55ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል የገቡትን ኳስ ተጠቅሞ አብዱልራሕማን ሙባረክ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ግብጠባቂው አብዱልዓዚዝ ኬይታ በድንቅ ብቃት የመለሰበት የሚጠቀሱ ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ቶሎ ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመግባት የተቸገሩት ወልዋሎዎችም ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር ።

በተለይም አማኑኤል ጎበና ከ ሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት የግቡን ቋሚ ገጭታ የተመለሰችው እና አፈወርቅ እና ዳዊት በጥሩ ቅብብል ይዘው በመግባት ኤፍሬም አሻሞ አግኝቶ ያመከናት ይጠቀሳሉ። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ፋሲሎች በበርካታ አጋጣሚዎች የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ቢያገኙም በደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሰዒድ ሃሰን ብቻውን ሄዶ ያመከናት ኳስ እና ሽመክት ጉግሳ ያልተጠቀመባቸው ዕድሎች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። ጨዋታውም ግብ ሳይስተናገድበት በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አድርጓል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *