በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ወደ ድሬዳዋ ያቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳላዲን ሰዒድ በ86ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ድንቅ የጭንቅላት ኳስ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል።
ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ባህር ዳር ከተማን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰው የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት በአዳማ ከተማ 1-0 ከተረታው የቡድን ስብስብ ውስጥ አጥቂው ሲላ መሐመድን በኃይሌ እሸቱ ብቻ ቀይረው ወደ ጨዋታ ሲቀርቡ፤ በአንፃሩ እንግዶቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባሳለፍነው ሳምንት በአስደናቂ መልኩ መከላከያን 5-1 ከረታው የቡድን ስብስብ ላይ በተመሳሳይ አንድ ተጫዋች ብቻ ቅያሪ በማድረግ በኃይሉ አሰፋን በአቡበከር ሳኒ ቀይረው ወደ ጨዋታው መቅረብ ችለዋል፡፡
ከጨዋታው መጀመር በፊት የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች ከሰሞኑ የስምንት ጨዋታ ቅጣት የተላለፈበት ኢታሞና ኪይሞኒን ቅጣት በመቃወም “ፍትህ ለኢታሙና ኪይሙኒ” እንዲሁም” ፍትህ ለድሬዳዋ ከነማ” እና መሠል መልዕክቶችን ያዘሉ ፅሁፎችን ይዘው በስታዲየሙ ሲዘዋወሩ ተስተውሏል። ከጨዋታው መጀመር በፊት እንደተገለፀው ከሆነ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስፓርት ኮሚሽንና ስፖርት ክለቡ በመተባበር የዕለቱ የስታዲየም ገቢ ሙሉ በሙሉ ለከተማው ተወላጅ ለሆነችው ህፃን ህያብ ተስፋዬ የህክምና ወጪ እንዲውልም ተደርጓል፡፡
እምብዛም ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ባልተስተናገዱበት የመጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ በግብ ሙከራዎች ባይታጀብም የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ችለው ነበር፡፡ ገና ከመጀመርያው ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች 6ኛው ደቂቃ ላይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ኳስ በእጅ በመንካቱ ያገኙትን የቅጣት ምት ረመዳን ናስር ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ወደ ግብ የላካትና ከግቡ አናት በላይ በወጣችበት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር፡፡
በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ወደ ጨዋታ ለመግባት እጅግ የተቸገሩ የሚመስሉት ጊዮርጊሶች በተለይ በቅድሚያ ለመጠቀም በፈለጉት ለ4-4-2 የቀረበ አደራደር በቀኝ መስመር አማካይነት የተሰለፈው ታደለ መንገሻ ከቀኝ መስመር እየተነሳ ወደ መሀል በማጥበብ በመስመሮች መካከል እንዲጫወት በተሰጠው ሚናና በመከላከል ሽግግሮች ወቅት ባለው አነስተኛ ተሳትፎ የተነሳ የቡድኑ ተጋላጭነት ከፍተኛ ነበር፤ በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳዎች የግብ እድል የፈጠሩባቸው አጋጣሚዎች በሙሉ በዚህ መስመር ከተሰለፉት ምንያህል ይመርና ሳሙኤል ተስፋዬ የተነሱ ነበሩ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በጥሩ ብቃት መከላከያን ያሸነፉት ጊዮርጊሶች በዛሬው ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ደካማ እንቅስቃሴን ነበር ሲያደርጉ የነበሩት። በ37ኛው ደቂቃ ሳልሀዲን ሰዒድ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ የላካትና ሳምሶን አሰፋ ካዳነበት ኳስ በቀርም በተደራጀ መልኩ ወደ ግብ ለመድረስ ተቸግረው ተስተውለዋል፡፡
በአንፃራዊነት የተሻሉ በነበሩት ድሬዳዋዎች በኩል በ20ኛው ደቂቃ ፍሬድ ሙሼንዲ እንዲሁም በ27ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ወልዴ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደግብ የላኳቸውና ኢላማቸውን ሳይጠብቁ የቀሩት ኳሶች ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። በተጨማሪም በ35ኛው ደቂቃ ምንያህል ይመር በረጅሙ በሶስቱ የመሐል ተከላካዮችና ጀርባ የጣለውን ኳስ ሐብታሙ ወልዴ ሚዛኑን ሳይጠብቅ ቀረ እንጂ ጥሩ አጋጣሚ ነበረች፡፡
በዚሁ አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ሁለት ጥሩ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ማግኘት ቢችሉም በተለይም በሁለቱ የአጥቂ ተሳላፊዎች ሐብታሙና እና ኃይሌ ደካማ የቦታ አያያዝ እና ውሳኔ አሰጣጥ ምክንያት ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። ለዚህም ዋንኛ ማሳያ የምትሆነው በ40ኛው ደቂቃ ምንያህል ይመር ያስጀመረው የመልሶ ማጥቃት ሳሙኤል ዮሐንስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ካለፈ በኃላ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ሐብታሙ ወልዴ ማስቆጠር ሲችል ዘግይቶም ቢሆን ወደ ግብ የላከው ኳስ ፓትሪክ ማታሲና የግቡ ቋሚ ተጋግዘው ሊያመክኑበት ችለዋል፡፡
ያለ ግብ ወደ እረፍት ያመሩት ሁለቱ ቡድኖች በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ጨዋታው ለመግባት ከፍተኛ መነሳሳትን አሳይተዋል፡፡ ወደ ቀደመው የ3-4-1-2 አሰላለፋቸው የተመለሱት ጊዮርጊሶች ፊት መስመር ላይ የተሰለፈው ሳላዲን ሰዒድ በግሉ ከቀጥተኛ አጨዋወት የሚመጡትን ኳሶች ለማሸነፍም ሆነ ኳሶቹን ተጠቅሞ የቡድን አጋሮቹን ወደ ጨዋታ ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ምንም እንኳን ከአጣማሪው ጌታነህ ከበደ እንዲሁም ከጀርባው ከተሰለፈው ታደለ መንገሻ በቂ ድጋፍ ባያገኝም፡፡ በዚህ አጋማሽ ፍፁም የተሻሉ የነበሩት ጊዮርጊሶች በ47ኛው ደቂቃ በሳላዲን ሰዒድ እና ናትናኤል ዘለቀ አከታትለው ያደረጓቸው ሙከራዎችን ሳምሶን አሰፋ ሊያድንባቸው ችሏል፡፡ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ይታይባቸው የነበረው ከፍተኛ ተነሳሽነት ተዳክመው ተስተውለዋል፡፡
በዚሁ አጋማሽ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አቡበከር ሳኒ እና ጌታነህ ከበደ ባጋጠማቸው ጉዳት የተነሳ በአብዱልከሪም መሐመድና አሜ መሐመድ ተተክተው ከሜዳ ሊወጡ ችለዋል፡፡ በተለይ ከአሜ መሐመድ መግባት በኃላ አስደናቂ ፍጥነቱን በመጠቀም ከፍተኛ ድካም ይታይባቸው ለነበሩት የድሬዳዋ ተከላካዮች ተጨማሪ ፈተና ሲሆንባቸው ተስተውሏል፡፡
በ86ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሐመድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በተቃራኒ አቅጣጫ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ኄኖክ አዱኛ ዳግም ተቆጣጥሮ ወደ ሳጥን ሲያሻግር ሳላዲን ሰዒድ በሁለቱ የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች መሐል በአስደናቂ ሁኔታ ተነስቶ በግንባሩ ማራኪ የሆነች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ይህች ግብ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ስታስጨብጥ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ለሁለተኛ ተከታታይ ሳምንት በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ ተሸናፊ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡