የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1-0 ወላይታ ድቻ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታ ዛሬ ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን አስተናግዶ 1-0 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል።

”እስከ መጨረሻው ታግሰን በመጫወታችን ውጤት ይዘን ወጠናል” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። በአራት ቀን ውስጥ ነው ሁለት ጨዋታ ያደረግነው። ተደራራቢ ጨዋታ ሲኖር ድካም ቢኖርም እስከ መጨረሻው ታግሰን ጥሩ እቅስቃሴ በማድረጋችን ውጤት ይዘን ወጠናል።

በአራት ቀን ውስጥ ሁለት ጨዋታ ስለማድረግ

በጣም ከባድ ነው፤ በጣም ጫና አለው። ጉዳት ሲኖር ቶሎ ተጫዎቾች ማገገም አይችሉም። በከፍተኛ ኃይል መጫወት አትችልም። ስለዚህ መርሐ ግብሩ እንደዚህ መጣበቡ ከባድ ነው። ግን ከዚህም በኋላም ተከታታይ ጨዋታዎች አለብን። ፕሮግራሞችን የመቀየር አመቺ መንገድ ከሌለ ተጫዋቾቻችንን በመቀያየር ድካሙ እንዳለ ሆኖ እንጫወታለን።

ወደ መሪነት ስለመጠጋት

ከዕለት ዕለት በቡድናችን ላይ መዋሃድ እያየሁ ነው። የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው። በይበልጥ ግን ክፍተቶች ያሉብን ቦታዎች ላይ ሰርተን ጠንካራ ቡድን ለመፍጠር ነው ጥረት የምናደርገው። እስከመጨረሻው ሂደታችን እስከሚገፋን ድረስ እንጓዛለን። ነገር ግን በዚህ ሰዓት ስለ መጨረሻችን መናገር ከባድ ነው። ጠንካራ ነገር እያየን ነው፤ ያንን እናስቀጥላለን።

ስለ ዳኝነቱ

ፍፁም ቅጣት ምቶች በዳኛ ውሳኔ የሚሰጡ ናቸው። ከዕረፍት በፊት ግልፅ የሆኑ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች ተከልክለናል። በመጨረሻ ደቂቃ ያገኘነውም ተገቢ ነው።

”እንደዚህ አይነት ዳኝነት ገጥሞኝ አያውቅም፤ ወደ ፊትም ይገጥመኛል ብዬ አላስብም” ዘነበ ፍስሃ – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው

የዛሬው ጨዋታ ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። በሁለቱም ቡድን ላይ የታየው ጥሩ የታክቲክ ጨዋታ ነው። ተመጣጣኝ ጨዋታ ነው፤ መልካም ነገር አይተናል። ነገር ግን ትልቅ የዳኝነት ችግር ታይቶኛል።

ስለ ዳኝነቱ

አሳፋሪ ዳኝነት ነው። እንደዚህ አይነት ዳኝነት ገጥሞኝ አያውቅም። ወደ ፊትም ይገጥመኛል ብዬ አላስብም።

ስለ ውጤት መጥፋት

ጥሩ ያልሆነው ብዙ አዳዲስ ተጫዋቾች ስላሰባሰብን ነው። ያንን የማቀናጀት ስራ እየሰራን ጊዜ ወስዶብን ተፅዕኖ አርጎብናል። ነገር ግን ብዙ የሚያስከፋ አይደለም፤ የተሻለ እየሰራን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *