ሪፖርት | ፋሲል ከነማ በመጨረሻ በተገኘች ፍፁም ቅጣት ምት ጎል ሶስት ነጥቦች አሳክቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ጎንደር ዐፄ ፋሲለ ደስ ስታድየም ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን አስተናግዶ በመጨረሻ ደቂቃ ያሬድ ባዬ ባስቆጠራት ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል 1-0 አሸንፏል፡፡

ፋሲል ከነማዎች ከባለፈው ሳምንት አሰላለፍ በጉዳት ምክንያት ሙጅብ ቃሲምን በከድር ኩሊባሊ እንዲሁም ሱራፌል ዳኛቸውን በኢዙ አዙካ እንዲሁም ዓለምብርሀን ይግዛውን ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት በተመለሰው ሽመክት ጉግሣ በመተካት ነበር ወደሜዳ የገቡት። ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው ከወልዋሎ 1-1 በሜዳቸው አቻ ከወጡበት ስብስብ በአንዱዓለም ንጉሴ ምትክ ፍፁም ተፈሪን ብቻ በመለወጥ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

በጨዋታው 3ኛ ደቂቃ ላይ የጨዋታው የመሀል ዳኛ ተካልኝ ለማ የለበሰው መለያ ከወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ጋር በመመሳሰሉ ጨዋታዉን ትጥቁን ለመቀየር በመገደዱ ጨዋታው ለተወሰነ ደቂቃ ያህል ተቋርጦ ነበር በድጋሚ የጀመረው፡፡በመጀመሪያው አጋማሽ ግጭት የበዛበት ጨዋታ የነበረ ሲሆን በፋሲል ከነማ በኩል የግብ እድሎችን ለመፍጠር በርካታ ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በሙከራ ደረጃ 8ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሣ ላይ በተሰራ ጥፋት አምሳሉ ጥላሁን የመታውን የቅጣት ምት ከድር ኩሊባሊ በጭንቅላት ገጭቶ የወጣበት ሙከራ ለባለሜዳወቹ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። በመልሶ ማጥቃት ኢንቀሳቀሱ በነበሩት ድቻዎች በኩል በ13ኛ ደቂቃ ላይ ባዬ ገዘህኝ የከድር ኩሊባሊን ጥፋት ተጠቅሞ ወደግብ የሞከረው ኳስ ጥሩ የሚባል ሙከራ ነበር።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ፋሲሎች ሙከራ ማድረጋቸውን ቀጥለው 28ኛ ደቂቃ ላይ ከአምሳሉ ጥላሁን ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ሽመክት ጉግሣ ወደ ግብ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂ ሲያድንበት በዚሁ ሒደት የተገኘውን የማዕዘን ምት አምሳሉ ጥላሁን ወደ ግብ አሻምቶ በድቻ ተከላካዮች ተገጭቶ ራሳቸው ግብ ላይ ሊያስቆጥሩ የነበረበት አጋጣሚም ነበር። 40ኛው ደቂቃ ላይ ኢዙ አዙካ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መትቶ አብዱረህማን ሙባረክ ያስቀረበት፤ የኤፍሬምን በጉዳት መውጣት ተከትሎ ተቀይሮ የገባው ሰለሞን ሐብቴ ከግራ መስመር ኳስ ይዞት በመግባት የሞከረው እንዲሁም በ44ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻማን ኳስ ኢዙ አዙካ በጭንቅላት ገጭቶ ወደ ግብ ቢሞክረውም ግብ ጠባቂው ያዳነበት በመጀመሪያዉ አጋማሽ ፋሲሎች ያደረጓቸው ሙከራዎች ነበሩ።

ሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ ብልጫ የወሰዱት ባለሜዳዎቹ ይበልጥ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማጠናከር ዮሴፍ ዳሙዬን አስወጥተው ኤዲ ቤንጃሚንን በማስገባት የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ቸለዋል። በአንፃሩ እንግዳው ቡድን ወላይታ ድቻ የመከላከል እንቅስቃሴውን በማጠናከር የፋሲል ከነማን ጨዋታ መሐል ሜዳ ላይ ገድቦት ተስተውሏል፡፡ ፋሲሎች ወደ ፊት ረጃጅም ኳሶችን ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል ቢልኩም የወላይታን የተከላካይ መስመር ሰብሮ ለማለፍ ሲቸገሩ ታይቷል።

48ኛው ደቂቃ ላይ ከድር ኩሊባሊ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ኤዲ ቤንጃሚን በጭንቅላት የገጨው ኳስ የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። 51ኛው ደቂቃ ላይ አብዱራህማን ሙባረክ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውን ግብ ጠባቂው ታሪክ ሲያድንበት 65ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ከሽመክት የተሻገረለትን ኳስ ሰለሞን ሀብቴ ወደ ግብ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ሌላ ጠንካራ የምትባል ሙከራ ነበረች፡፡ ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ሰዓት ማባከን የጀመሩት የድቻ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ሲወድቁም ታይተዋል፡፡ በ73ኛ ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የሄደውን ኳስ ሳምሶን ቆልቻ ከርቀት ሞክሮ በቀላሉ ሚካኤል ሳማኪ ያዳነበት ሙከራም ብቸኛ የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር።

በ85ኛው ደቂቃ ከመሐል ወደ ወላይታ ድቻ ግብ ክልል የተሻማን ኳስ አምሳሉ ጥላሁን ዘሎ በሚገጭበት ስዓት በወላይታ ድቻ ተከላካዮች በሳጥን ውስጥ በመገፋቱ ፋሲል ከነማ የፍፁም ቅጣት ምት ማግኝት ችሏል። የተገኝውን የፍፁም ቅጣት ምትም አምበሉ ያሬድ ባዬ በአግባቡ ተጠቅሞባት ፋሲል ከነማን አሸናፊ ማድረግ የቻለችውን ጎል አስቆጥሯል፡፡ ፍፁም ቅጣት ምቱ ተገቢ አይደለም በሚል የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች እና አመራሮች ጨዋታውን አስቁመው በዕለቱ ዳኛ ተካልኝ ለማ ላይ የቅሬታ ክ ያስመዘገቡ ሲሆን በቀሪው ደቂቃ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በዐፄዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *