ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ ሶስት – ክፍል 3)

በእንግሊዛዊው የእግርኳስ ጸኃፊ ጆናታን ዊልሰን ደራሲነት በ2008 ለንባብ የበቃው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics ን በሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ክፍሎች እያቀረብንላችሁ እንገኛለን፡፡ በዛሬው መሠናዶም የምዕራፍ ሦስትን 3ኛ ክፍል እነሆ ብለናል፡፡

|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ LINK

ኸርበርት ቻፕማን (ካለፈው ሳምንት የቀጠለ…)

ቻፕማን ማንኛውንም የዋንጫ ስኬት ለማስመዝገብ ከአምስት ዓመት ያላነሰ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ቅድመ-ማሳሰቢያ በመስጠት እንዲሁም የክለቡ ፈላጭ ቆራጭ ኖሪስ ሳይወድ በግድ የተስማማባቸው ሁኔታዎች ላይ ምንም ዓይነት ገደብ እንዳይገጥመው ተደራድሮ የአርሰናል ስራውን ተረከበ፡፡ ቻርሊ ቡቻንንም የመጀመሪያ የክለቡ ፈራሚ አድርጎ አዛወረው፡፡ ሰንደርላንዶች ለተጫዋቹ አራት ሺህ ፓውንድ የመሸጫ ተመን አወጡለት፡፡ የክለቡ አሰልጣኝ ቦብ ኬይል ” በአንድ የውድድር ዘመን ሃያ ግቦች ለሚያመርት የመሃል አጥቂ ዋጋው የሚበዛ አይደለም፡፡” ሲሉ አጥብቀው ተከራከሩ፡፡ የሰሜን ለንደኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኖሪስ ” በተጫዋቹ ብቃት ከተማመናችሁ የክፍያ አፈጻጸሙን በተመለከተ ቅድመ ክፍያ ሁለት ሺህ ፓውንድ፥ በአርሰናል ቆይታው ለሚያስቆጥረው እያንዳንዱ ግብ ደግሞ አንድ መቶ ፓውንድ ለመክፈል እንስማማ!” በማለት ተደራደረ፡፡ ኬይልም ያለማቅማማት ተስማሙ፡፡ ቡቻንም በውድድር ዓመቱ አጠቃላይ ሃያ አንድ ጎሎችን አግብቶ ሰንደርላንዶች በኩራት አራት ሺህ አንድ መቶ ፓውንዳቸውን እንዲቀበሉ አደረገ፡፡

እንግዲህ ይህ ሁሉ ነገር በመስከረም ወር አርሰናል በኒውካስል ከደረሰበት አስደንጋጭ ሽንፈት በኋላ የሚሆን አይመስልም ነበር፡፡ ቡቻንን እንደ ተጫዋች ለማስተዳደር የማይመች ባህሪ ተላብሷል፡፡ በአርሰናል የመጀመሪያ ልምምድ መርኃግብር ላይ የቀረበለት ትጥቅ “በቂ አይደለም!” ብሎ ልምምዱን ሳይሰራ ወጥቶ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ በሁለተኛ የመስክ ስልጠና ፕሮግራም ላይ ደግሞ “በጥሩ ሁኔታ ታጥቦ የተዘጋጀ ካልሲ ሊቀርብልኝ ሲገባ ጭራሹኑ የረጋ ቫዝሊን ያለበት ጋምባሌ ተሰጠኝ!” ብሎ ልምምድ ለማድረግ አሻፈረኝ አለ፡፡ ሌሎች አሰልጣኞች ቢሆኑ የተጫዋቹን ድርጊት ” ሆን ብሎ የሚያሳየው ማን- አለብኝነት አልያም ደግሞ ተገቢነት የጎደለው ጥንቃቄ የማብዛት ትምክህት ነው!!” ሲሉ ይኮንኑት ነበር፡፡ ቻፕማን ግን ነገሩን በሌላ መነጽር ቃኘው፡፡ ድርጊቱን ተጫዋቹ ለራሱ ያስቀመጠው ከፍ ያለ ደረጃ ማሳያ እንደሆነ ተረዳለት፡፡ ቡቻንን ከዚህ አመሉ ውጪ የሚያደንቅበት ሌላ ምክንያትም ነበረው፡፡ አጥቂው በዘመኑ በነበሩ ተጫዋቾች ዘንድ ከተለመደው በተለየ ሁኔታ በእግርኳስ አጨዋወት መንገድ የራሱ የሆነ ነጻ አመለካከትን ያራምዳል፡፡ ይህን ጉዳይ በማስመልከት የቀድሞ ዳኛ ጆን ሌዊስ በ1914 ” እግርኳስን መደበኛ ስራቸው ያደረጉት ተጫዋቾቻችን በስፖርቱ ዘርፍ የሚወጣ ማንኛውንም ቲዎሪ ለመማርና ለመረዳት የመጓጓት ስሜት አይታይባቸውም፡፡… በብዙ ቡድኖች ዘንድ ከነባሩና ተለምዷዊው ስልት በተለየ በጥልቀት የታሰበበት ታክቲክ ወይም ተራማጅ ሃሳብ የማመንጨት ሁኔታ አይስተዋልም፡፡” ሲል በወቅቱ ይታይ የነበረው እግርኳሳዊ ጽንሰ-ሐሳቦችን የማግሸሽ አዝማሚያ ላይ ሒሳዊ አስተያየቱን ፃፈ፡፡ እንዲያም ሆኖ ቻፕማን ዘወትር ተጫዋቾቹ በጨዋታ ዘይቤ ጉዳይ የመከራከርና ውይይት የማድረግ ባህልን እንዲያዳብሩ ቢጥርም ብዙ አበረታች ለውጥ አልታየም፡፡

ቡቻን በዚያ ዘመን እግርኳስ በመከላከል አጨዋወት የሚያተኩር፣ በሜዳው ስፋትና ቁመት መሃል ላይ የሚሰለፍ የተከላካይ አማካይ (centre-half) መጠቀም ውጤታማ እንደሚያደርግ ሰንደርላንድ ውስጥ በነበረው ቆይታ በቡድን አጋሩ ቻርሊ ቶምሰን አማካኝነት ተገንዝቧል፡፡ ቶምሰን የመሃል-ተከላካይ አማካይ ከመሆኑ በፊት ኳስ መጫወት ሲጀምር ወደ ኋላ በጥልቀት ማፈግፈግ የሚወድ የመሃል አጥቂ (centre-forward) ነበር፡፡ አዲሱ የውድድር ዘመን እንደተጀመረ ” በቅርቡ የተቀየረው የ<ጨዋታ ውጭ> መመሪያ የመሃል አማካዮች (በተለይ ከሶስቱ የመሃለኛው) ከቀድሞው ይበልጥ የመከላከል ኃለፊነት እንዲያርፍባቸው ያስገድዳል፡፡” እያለ ሲሟገት ከርሟል፡፡ ይህ መከራከሪያ በሴይንት ጄምስ አርሰናሎች በኒውካስሎች ሲረቱ የማግፒሶቹ ተከላካይ-አማካይ ቻርሊ ስፔንሰር እጅጉን ወደ ኋላ አፈግፍጎ ሲጫወት በግልጽ ታየ፡፡ ተጫዋቹ በጨዋታው የማጥቃት ሒደት ያሳየው እንቅስቃሴ ውስን ሆኖ በዋነኝነት የአርሰናሎችን የማጥቃት እቅድ ከጅምሩ ሲያጨናግፍ ዋለ፡፡ በዚህ ሚናው ቡድኑ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እና ክፍተቶችን በአግባቡ የመሸፈን ብልጫ እንዲኖረው ረዳ፡፡ በእርግጥ ቻፕማን ወደ ኋላ ተስቦ በሚጫወት የተከላካይ አማካይ አስፈላጊነት በጽኑ ያምናል፡፡ ታዲያ ለመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የማድላት ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ኖሮት ቀደም ብሎ ይህን የጨዋታ ስልት ለመተግበር ያልፈለገበት ምክንያት ለብዙዎች ጊዜው ያልፈታው ምስጢር ሆኖ ቆየ፡፡

ስለእውነቱ ከሆነ ቻፕማን በክለብ ባለስልጣናት ቁጣና ዛቻ በቀላሉ የሚሸበር ሰው አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ከ1922ቱ ዋንጫ ፍጻሜ በኋላ የእግርኳስ ማህበሩ ያወጣው ማስጠንቀቂያ እና ተቋሙ ያነሳለት ከእግርኳስ የመራቅ የህይወት ዘመን እገዳ ምናልባትም መጠነኛ ተፅዕኖ ሳያሳድርበት አልቀረም፡፡ ሌሎችም ይህንኑ መላምት መደምደሚያቸው አድርገውታል፡፡ በእግርኳስ ታክቲካዊ ጉዳዮች ፍላጎት የማጣት አልያም ግንዛቤ የማዳበር ችግር የመሆኑ ጉዳይ ቀስ በቀስ የሚታይ ቢሆንም የሶስተኛው ተከላካይ ህልውና የ<ጨዋታ ውጭ> ህግ ከመሻሻሉ ከረጅም ጊዜ በፊትም የነበረ ነው፡፡ ለውጡ ያመጣው ውጤት አዳዲስ ታክቲካዊ ሙከራዎችን የማድረግ ተነሳሽነት እንዲጎለብት ማስቻሉ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሶስተኛ ተከላካይ በመጠቀም በአጠቃላዩ የሜዳ ክፍል ላይ የሚፈጠር ያልተጠበቀ ተጽዕኖ ካለ ቡድኖች ተግባራዊ ምርምር እንዲያደርጉም ይገፋፋል፡፡
ለአብነት ያህልም በጥቅምት 3-1923 አርሰናሎች በኒውካስሎች በከባድ ሁኔታ በተሸነፉበት ዕለት በ<ሳውዝአምፕተን ፉትቦል ኤኮ> ጋዜጣ የ<ቼሪ ብሉሰም> አምዱ ላይ ጆርጅ ኋይት የሚከተለውን ሰፋ ያለ ትንታኔ አቅርቧል፡፡

” ቅዳሜ-መስከረም 26 ሴይንቶቹ በዴል ስታዲየም በብራድፎርድ ሲቲዎች ታክቲካዊ ብልጫ ተወስዶባቸው ተሸንፈዋል፡፡ እንደኔ ግምት ባለሜዳዎቹ ከብራድፎርዶች በተሻለ ተጫውተዋል፤ አዝናኝ እግርኳስም አሳይተዋል፡፡ ይህ የሆነው እንግዲህ የ<ጨዋታ ውጭ> ህግ ከመቀየሩ በፊት ነው፡፡ ብራድፎርድ ሲቲዎች ኳሱ ላይ ብልጦች ሆነው ቢቀርቡም አብዛኛውን ስራ የሰሩት ታክቲካዊ ጉዳዮች ላይ ስለሆነ እነርሱ ሁለት አስቆጥረው ኒውካስሎች ከአንድ ግብ በላይ እንዳያገቡ አደረጉ፡፡ በወቅቱ መልበሻ ክፍሎች ውስጥ ‘ ከተቀየሩት የ<ጨዋታ ውጭ> ህግጋት አንጻር የተሰኘው የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ለማጥቃት የጨዋታ ሒደት አመቺ ነው ወይ?’ በሚል ውይይት ተደረገበት፡፡ በዚህ ፎርሜሽን የመሃል አጥቂውና ሁለቱ የጥገኛው መስመር አማካዮች በላይኛው የሜዳ ክፍል ጥሩ ጥምረት ይመሰርታሉ፤ ከጨዋታ ውጪ እንዳይሆኑም አንድ ሜትር ያህል በሚሆን ርቀት ከተጋጣሚ ተከላካዮች ፊትለፊት ይንቀሳቀሳሉ፤ በሜዳው ቁመት ከመስመር አማካዮቹ ትይዩ ከመሃል አጥቂው ግራና ቀኝ የሚሰለፉት ሁለቱ አጥቂዎች ደግሞ በተመጠነ ርቀት ወደ ኋላ ቀረት ይሉና ለመሃል አማካዮቹ ቀርበው ይጫወታሉ፡፡”

ጆርጅ ኋይት ከላይ ለማብራራት እንደሞከረው የብራድፎርዱ አሰልጣኝ ዴቪድ ሜንዚስ በእግርኳስ ታክቲክ የራሱ የሆነ አስተሳሰብ ያለው ብቸኛው ሰው ከነበረ ነገሩን የበለጠ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ ሆኖም ግን ራሱ ጸሃፊው በወቅቱ W-ፎርሜሽንን ጥቅም ላይ ማዋል በብዙ ቦታ ተስፋፍቶ እንደነበር መደምደሚያ ይሰጣል፡፡ ” እስካሁን የሚታየው ግብ የማስቆጠር ሒደት አዲሱ ፎርሜሽን በብዛት ተግባራዊ እየተደረገና እየተለመደ ስለመሆኑ ማስረጃ ይሰጠናል፡፡ ከዋናው አጥቂ ጎን የሚንቀሳቀሱት ሁለቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ጎሎችን ለማግባት የሚያደርጉት ትርምስ ቀንሷል፤ በሚያስደንቅ ድግግሞሽ በየጨዋታ እየተቆጠሩ ያሉትም ሶስት፣ አራትና አምስት ግቦች በመሃል አጥቂዎቹ አማካኝነት ነው፡፡ የመስመር አጥቂዎቹም ግብ የማስቆጠር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ጀምረዋል፡፡” ሲል ሃሳቡን አስፍሯል፡፡

ልክ እንደ ሳውዛምፕተኖች ሁሉ በጊዜው በሁለተኛ ዲቪዚዮን ይሳተፍ የነበረው ቼልሲም በአዳዲሶቹ የጨዋታ ህግጋት ከተጠቀሙ ዋነኛ ክለቦች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ በቡድኑ ለረጅም ጊዜ የተጫወተው፣ እድሜው የገፋውና የከዳው ፍጥነቱ ያን ያህልም አሳሳቢ በማይሆንበት ቦታ ወደ ኋላ አፈግፍጎ እንዲጫወት የተፈቀደለት ስኮትላንዳዊው አንዲ ዊልሰን በአዲሱ ሚናው ይበልጥ ደምቆ ታየ፡፡ ተጫዋቹ ቀደም ሲል በነበረው የውድድር ዘመን በመሃል የፊት አጥቂነት ይሰለፍ ነበር፡፡ ኋይት ገለጻውን ይቀጥላል፦ ” በዚህ የማጥቃት አቀራረብ እንቅስቃሴያዊ የቦታ ሽግሽግ ሲደረግ ከሶስቱ የፊት አጥቂዎች ጀርባ የሚገኙት ሁለቱ ያፈገፈጉ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ቡድናቸው በመከላከል የጨዋታ ዑደት ውስጥ ሲገኝ እንደ ተጨማሪ አማካይ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ በዚህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የመሃል-ተከላካይ አማካዩ ደግሞ ሶስተኛ ተከላካይ ይሆናል፡፡”
ጸሃፊው በዚያው ዕለት ከሰዓት በሚደረግ የሳውዛምተንና የፖርት ቬል ጨዋታ ሳውዛምፕተኖች የW ፎርሜሽንን እንዲጠቀሙ ወተወታቸው፤ ተቀበሉት፤ በሜዳ ላይም ተገበሩት፡፡ ከሜዳቸው ውጪ ባካሄዱት ከባድ ግጥሚያም የአቻ ውጤት አገኙበት፡፡ ከዚያም በቀጣዩ ሰኞ በሜዳቸው ዳርሊንግተንን 4-1 ሲረቱ በድጋሚ ፎርሜሽኑን ጥቅም ላይ አዋሉት፡፡ አርሰናል በኒውካስል በተሸነፈ፥ ሳውዛምተን ከፖርት ቬል አቻ በወጣ በሳምንቱ ቅዳሜ የ<ቼሪ ብሉሰም> አምድ የሬይዝ ሮቨርሱን ዴቭ ሞሪስ ” ወደኋላ በማፈግፈግ የሚጫወት የዘመኑ ምርጥ የመሃል- ተከላካይ አማካይ (Deep-Lying Centre Half) ” ሲል አወደሰው፡፡ ” ተጫዋቹ በሜዳ ላይ ከተከላካዮች መሃል በመጠኑ ወደፊት ፈቅ ብሎ ይንቀሳቀሳል፤ የመስመር አማካዮቹ የተጋጣሚ መስመር አጥቂዎችን ሲቆጣጠሩ፥ የመስመር ተከላካዮቹና የመሃል-ተከላካይ አማካዩ ደግሞ ሶስቱን የተጋጣሚ የመሃል አጥቂዎች እንቀስቃሴ ይከታተላሉ፡፡ በዚህ ፎርሜሽን ከመሃል አጥቂው ግራና ቀኝ የሚገኙ ሁለቱ አጥቂዎች(Inside Forwards) ከበፊቱ በበለጠ ለመሃል-ተከላካይ አማካዩ ቀርበው ይጫወታሉ፡፡ እርሱም (centre-half) በቡድኑ ውስጥ የመከላከል እና የማጥቃት ማዕከል በመሆን አጥቂዎቹ ጥሩ እድል ሲፈጠርላቸው ስኬታማ ቅብብሎችን ያደርግላቸዋል፡፡” በማለትም የተጫዋቹን የሜዳ ላይ ኃላፊነቶች በዝርዝር አቀረበ፡፡

አዲሱ የW-ፎርሜሽን የቴሌቪዥን ስርጭት ባልነበረበት ጊዜ በሚያስገርም ፍጥነት ተመነደገ፡፡ በዚሁ ዓመት ጥቅምት ወር መጀመሪያ እንደ ሬይዝና ሳውዛምፕተን ያሉ የተለያዩ ክለቦች ፎርሜሽኑን ባይተገብሩ ኖሮ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ሰባት አልያም ስምንት ጨዋታዎች ላይ የሚሞከር በሃገሪቱ ብቻ የተወሰነ ክስተት ይሆን ነበር፡፡ በእርግጠኝነት የመሃል-ተከላካይ አማካይ ሶስተኛ ተከላካይ (Third Back)ሊሆን እንደሚችል ድምዳሜ ላይ በመድረስ አርሰናሎች የመጀመሪያዎቹ ባይሆኑም ከየትኛውም ክለብ በተሻለ አዲሱን ፎርሜሽን በወጥነት እና በከፍተኛ ስኬት ለመጠቀም ችለዋል፡፡

ቡቻን ቀደም ብሎ “የመሃል-ተከላካይ አማካይን ወደ ኋላ በጥልቀት እንዲያፈገፍግ ማድረግ የመሃል ክፍል ላይ የመሳሳት ችግር ያስከትላል፡፡” የሚለውን ሃሳብ ደግፎ ተከራክሮ ነበር፡፡ ቻፕማን በቡቻን ሃሳብ ተስማማ፡፡ይህን ችግር ለመቅረፍ በ2-3-5 ፎርሜሽን ከመሃል አጥቂው በስተቀኝ የሚገኘውን የፊት መስመር ተሰላፊ (Inside Right) ወደ ኋላ በመሳብ በትንሹ ሚዛናዊነት የሚጎድለውን፣ ልል የሆነው እና በ2-3-5 እና በW መካከል የሚገኘውን 3-3-4 ፎርሜሽን ፈጠረ፡፡ ቻፕማን የቡቻንን ግብ የማስቆጠር ብቃት በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚተማመን ወደኃላ በማፈግፈግ የማጥቃት ሒደት የመምራት ሚናውን ለአንዲ ኒል ሰጠው፡፡ በሚያስገርም መልኩ ኒል የሶስተኛ ቡድን ተጫዋች ቢሆንም ውሳኔው በተነሳሽነት ስሜት የተሰ፣ የቻፕማንን ንድፈ-ሐሳብ የማመንጨት እንዲሁም የተለየ የሚባለው ክህሎት በየትኛው ተገቢ ቦታ ላይ አስፈላጊ እንደሆነ ክፍፍሎች የማድረግ ችሎታን የጎላ ትኩረት እንዲያገኝ የሚያስችል ማስረጃና ድጋፍ ይሆናል፡፡ እየዋለ እያደር የቻፕማን ታማኝና ወሳኝ የሁለት ቁጥር ቦታ ተጫዋች የነበረው ቶም ዊታከር አሰልጣኙ ኒልን “እንደ ቀብር ስነስርዓት ዝግ ያለ” ብሎ ሲገልጸው ያስታውሳል፡፡ “ሆኖም ግን ቀርፋፋነቱ ችግር አልሆንበትም፤ ምንክንያቱም አስደናቂ ኳስ የመቆጣጠር ክህሎት ነበረው፤ ኳሷ ከእግሩ ስር ሳትወጣ አዕምሮውን የመጠቀም ችሎታን አዳብሯል፡፡” በማለት የቡድን ጓደኛውን ክህሎት ያወሳል፡፡

የአዲሱ ፎርሜሽን አዎንታዊ ተጽዕኖ እያደገ ሲሄድ ተፈጥሮዓዊ የመፍጠር ብቃቱን ለመገምገም አስቦ በጥልቀት ወደ ኋላ ያፈገፈገ የተከላካይ አማካይ ሆኖ ለመጫወት ፍላጎት እንዳለው ያሳወቀውን ጃክ በትለር እና በተለወጠው የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ደስ የተሰኘውን ቻርሊ ቡቻን የያዙት አርሰናሎች በኒውካስሎች ድንገተኛ ሽንፈት ከገጠማቸው ሁለት ቀናት በኋላ ዌስትሃሞችን በአፕተን ፓርክ 4-1 ረመረሙ፡፡ በውድድር ዘመኑ ማብቂያ ላይም ሃደርስፊልዶችን ተከትለው ሁለተኛ ሆነው አጠናቀቁ፡፡ በወቅቱ ይህ ስኬት ከለንደን የመጣ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀዳጀው ከፍተኛው የሊግ ደረጃ ነበር፡፡ በአንድ በኩል ቀደም ሲል የተመዘገበው አንጻራዊ ስኬት ያስከተለው ቅጥ ያጣ የራስ መተማመን፥ በሌላ በኩል ደግሞ ተጋጣሚዎች የበትለርን ተፈጥሮዓዊ የመከላከል ድክመት መጠቀም በመጀመራቸው በቀጣዩ የውድድር ዓመት አርሰናሎች እጅጉን ተዳክመው ቀረቡ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ቡድኑ ተለምዷዊውን ነባር 2-3-5 ፎርሜሽን መጠቀም እንዲጀምር ሞገቱ፡፡ ቻፕማን ግን ችግሩ በፎርሜሽኑ ላይ የተፈጠረው ታክቲካዊ አብዮት ሳይሆን ለውጡን በአግባቡ በተጫዋቾች አዕምሮ ለማስረጽ ካለመቻል ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ለመሃል-የተከላካይ አማካይነት የሚሆኑ ተጫዋቾች ፍጹም ከማስመሰልና ከመልፈስፈስ የራቁ መሆን እንደሚገባቸው አመነ፡፡ ያልተጠበቀው ኸርቢ ሮበርትስ ደግሞ ይህን ባህሪ የተላበሰ ተጫዋች ሆኖ ተገኘ፡፡ ባለ ቡናማ ቀለም ጸጉሩና ቀውላላው ሮበርትስ በቻፕማን አማካኝነት በሁለት መቶ ፓውንድ ከኦስዌስትሪ ታውን አርሰናሎችን የተቀላቀለ የመስመር አማካይ ነበር፡፡

ዊታከር ” የሮበርትስ ችሎታ ከአዕምሯዊ ጉብዝናው ጋር ይያያዛል፡፡ በተጨማሪም የሚነገረውን በትክክል መተግበር ይችላል፡፡” ሲል ስለተጫዋቹ ብቃት ይመሰክራል፡፡ በእርግጥ ተጫዋቹ ነገሮችን በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚመለከት ወግ አጥባቂ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ግን እይታው እጅግ አስፈላጊ ቦታ ላይ ነው፡፡ ዊታከር በጽሁፉ ” የሮበርትስ ዋነኛ የሜዳ ተልዕኮ በመሃል ክፍሉ ላይ በተጋጣሚ ቡድን የሚደረጉ ቅብብሎችን በማቋረጥ ለቡድን አጋር በግንባር በመግጨት አልያም በአጭሩ በመሬት ማቀበል ነበር፡፡ ስለዚህ ተጫዋቹ ኳሷን አጠንክሮ በርቀት የመምታት ችሎታው የተደበቀ እንደነበር ትታዘባላችሁ፡፡” ይለናል፡፡ ለእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን በአማተርነት የተጫወተ የመጨረሻ ተጫዋች የነበረውና ኋላ ላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ብቅ ያለው ቤርናርድ ጆይ በ1935 የሮበርትስ ምክትል በመሆን የአርሰናል ክለብ የአሰልጣኞች ቡድን አባል ሆነ፡፡ ለ<ፎርዋርድ አርሰናል!> ጋዜጣ ሲፅፍ ” ሮበርትስ ቀጥተኛ ተናጋሪ ነበር፡፡ በቴክኒክ ችሎታው ከበትለር ቢያንስም በአካላዊ ቁመናውና በአጨዋወት ባህሪው ለተሰጠው ሚና የሚስማማ ምቹ ተጫዋች ነበር፡፡ በመለሎ ቁመቱ በመታገዝ ቡናማ ጸጉሩ በሸፈነው ግንባሩ ኳሷን እየገጨ የጨዋታን የመከላከል ሒደት ለመምራት ይጥራል፤ ከፍተኛ ጫና እና ጠንካራ የተወቃውሞ ጩኸትን የሚቋቋምበት አስገራሚ ትዕግስት ተላብሷል፡፡ ይህ በቀላሉ ያለመረበሽና ተፈጥሮአዊ እርጋታው የአርሰናል ተከላካይ ክፍል ምሰሶ እንዲሆን ረዳው፡፡ ክለቡ የመሰረተው አዲስ የመከላከል አጨዋወት ዘይቤም በመላው ዓለም ተቀባይነት አግኝቶ በርካታ የእግርኳስ ሃገራት የሚመርጠት ስልት ሆኖ ተገኘ፡፡” ብሏል፡፡ የአዲሱ አጨዋወት መንገድ በሰፊው መንሰራፋት በተወሰነ ደረጃ ችግር ፈጠረ፡፡ እርግጥ አርሰናሎች እጅግ ስኬታማ ሆኑበት፤ ለአጨዋወቱ አመቺ ተጫዋቾችን ሳይዙ እና እንዴት ባለ ሁኔታ መጠቀም እንዳለባቸው ሳይረዱ ዘይቤውን የኮረጁ ሌሎች ቡድኖች ግን አሉታዊ ውጤት ከማስመዝገብ ያለፈ ልዩነት አላገኙበትም፡፡

በ1927 አርሰናሎች የኤፍ.ኤውን ዋንጫ በካርዲፎች ተነጠቁ፡፡ በ1929 የእግርኳስ ማህበሩ በክለቡ ላይ የተጋረጠውን የፋይናንስ አለመረጋጋት ለመመርመር ሲዘጋጅ ኖሪስ ቡድኑን ተሰናበተ፡፡ ከዚያ በኋላ ስኬት የክለቡን በር ማንኳኳት ጀመረች፡፡ ቀደም ብሎ በ1928 መጨረሻ ራሱን ከእግርኳስ ባገለለው ቡቻን ምትክ ቻፕማን አጭሩን ስኮትላንዳዊ አሌክስ ጄምስ ከፕሪስተን በዘጠኝ ሺህ ፓውንድ አስፈረመ፡፡ ተጫዋቹም በአርሰናል የቻፕማንን አዲስ የአጨዋወት ስልት አስቀጠለ፡፡ ክለቡ በታሪክ ማህደሩ ውስጥ ” ማንም ሰው ጄምስ በአርሰናል የ1930ዎቹ ውጤታማ ዓመታት ወቅት ለክለቡ ያበረከተውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማንኳሰስ አይገባውም፡፡ እርሱ የቡድኑ ቁልፍ ሰው ነበር፡፡” ሲል ስራውን በደማቁ አሰፈረለት፡፡ ድካም ለመቀነስ በታቀደ የተመጠነ እንቅስቃሴው ራሱን ነጻ በማድረግ ኳስን ለመቀበል የሚያስችል ድንቅ ቦታ አያያዙ ከኋላ መስመር ጨዋታን ለመመስረት የበቃ ወሳኝ ተጫዋች እንዲሆን አደረገው፤ ቴክኒካዊ ክህሎቱና እይታው ደግሞ ቅብብሎችን በፍጥነትና በትክክል ለፊት መስመር ተሰላፊዎች እንዲያሰራጭ አስቻለው፡፡ ጆይ ስለ ጄምስ ብቃት ሲመሰክርም “እርሱ አብሬያቸው ከተጫወትኳቸው ተጫዋቾች በሙሉ እጅግ ብልሁ ነበር፡፡ በሜዳ ላይ ሁለት-ሶስት የወደፊት እንቅስቃሴዎችን በቅልጥፍና የማሰብና የመከወን ተሰጥዖ ነበረው፡፡ ብልጠት የታከለበት ቦታ አያያዙን እየተጠቀመ ከራሱ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል አካባቢ ስኬታማ ቅብብሎችን በተጋጣሚ ደካማና ክፍት ቦታዎች ላይ በማድረስ የበርካታ ጨዋታዎችን ውጤት ቀይሯል፡፡” ብሎለታል፡፡

ቻፕማን ቀደም ሲል በገባው ቃል መሰረት ክለቡን ከተረከበ አምስት ዓመታት በኋላ አርሰናሎች በ1930 የኤፍ.ኤውን ዋንጫ በማንሳት የመጀመሪያ ድላቸውን ሲያሳኩ የW-ፎርሜሽን በእግርኳስ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶና አዲሱ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያዊ ቦታ አጠቃቀም ግልጽ የሆነ ቅርጽ ይዞ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የመስመር ተከላካዮች(Wing Halves) በተጋጣሚ ቡድን ውስጥ ከመሃል አጥቂው ግራና ቀኝ የሚሰለፉ አጥቂዎችን (Inside Forwards) እንቅስቃሴ ከመቆጣጠር ይልቅ የተጋጣሚዎችን የመስመር አማካዮች (Wingers) እንቅስቃሴ መከታተል ያዙ፡፡ በሜዳው ቁመት መሃለኛው መስመር ላይ የሚሰለፉ የክንፍ አማካዮችም (Wing Halves) የተጋጣሚን የመስመር አማካዮች መያዝ ትተው ሁለቱን የግራና ቀኝ አጥቂዎች (Inside Forwards) እንቅስቃሴ ማፈን ቀዳሚ ተግባራቸው ሆነ፡፡ በቀድሞው ፎርሜሽን የመሃል-ተከላካይ አማካይ (Centre-Half) የነበረውና በአዲሱ ሲስተም ጥቂት ወደ ኋላ አፈግፍጎ የመሃል ተከላካይ(Third Back) ሆነና ከተቃራኒ ቡድን የመሃል አጥቂ (Centre-Forward) ጋር ቀጥተኛ ፍልሚያ ማድረግ ጀመረ፡፡ ሁለቱ የግራና ቀኝ አጥቂዎች ደግሞ በጥልቀት ወደ ኋላ ተስበው 2-3-5 ወደ 3-2-2-3 ወይም WM ቅርጽ ተቀየረ፡፡ ጆይ እንደጻፈው
” ለውጡ ማጥቃት ላይ ያተኮረ አይደለም፥ የመልሶ-ማጥቃት ላይ እንጂ! የእያንዳንዱን ተጫዋች ምርጥ ብቃት ለመጠቀም አቀድን፡፡ በእንቅስቃሴ ወቅት በሁለቱም የፍጹም ቅጣት ምት አካባቢዎች በጨዋታው ሙሉ ክፍለ ጊዜ ትርፍ ተጫዋች እንድናገኝ አሰብን፡፡ የመሃል ሜዳውን በቁጥጥር ስር ማድረግ አልያም የባላጋራ የመከላከል ወረዳ ላይ ጫና መፍጠር የጨዋታችን ዋነኛ ግብ አልነበረም፡፡ ሆን ብለን ወደ ራሳችን የግብ ክልል እናፈገፍግና ተጋጣሚዎቻችን ተከትለውን እንዲመጡ እንጋብዛቸዋለን፤ በመከላከያ ወረዳችን ላይ ጠንክረን የእነርሱን የማጥቃት እንቅስቃሴ እንገታለን፡፡ ከዚያም ኳሱን እንቀማቸውና በፍጥነት ወደ ፊት በመግፋት በረጅሙ ለመስመር አማካዮቻችን እናሻግርላቸዋለን፡፡” በማለት የመልሶ ማጥቃቱን ሒደትና ትልም ያብራራል፡፡

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

Sunderland: A Club Transformed (2007)

Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

The Anatomy of England (2010)

Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

The Anatomy of Liverpool (2013)

Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)


 

ቀደምት ምዕራፎች
መቅድም LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አራት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል አራት LINK
ምዕራፍ 3 – ክፍል አንድ
LINK
ምዕራፍ 3 – ክፍል ሁለት
LINK

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *