ሪፖርት | ሲዳማ ቡና መከላከያን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት በሜዳው መከላከያን የገጠመው ሲዳማ ቡና 2-0 በመርታት ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አድርጓል። 

ሲዳማ ቡናዎች በ11ኛው ሳምንት ደቡብ ፖሊስን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሶስት ተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ ግሩም አሰፋ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ እና ሰንደይ ሙቱኩን በሚሊዮን ሰለሞን፣ ግርማ በቀለ እና ዳግም ንጉሴ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ ከሸረው ጨዋታ በተመሳሳይ የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉት መከላከያዎች ሽመልስ ተገኝ፣ አዲሱ ተስፋዬ እና ዳዊት ማሞን በማስወጣት በዓለምነህ ግርማ፣ አበበ ጥላሁን እና በኃይሉ ግርማን ተጠቅመዋል። 

በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሲዳማ ቡናዎች ከሁሉም አቅጣጫዎች በተደጋጋሚ ወደ መከላከያ የግብ ክልል በመድረስ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በተለይ በቀኝ በኩል ሐብታሙ ገዛኸኝ የመከላከያን ክፍት አደረጃጀት ሂደትን ሰብሮ እየገባ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለጦሩ ፈታኝ ሆኖ ውሏል፡፡ አጀማመራቸው ጥሩ ይመስል የነበሩት መከላከያዎች ከቴዎድሮስ ታፈሰ እግር ከሚነሱ ኳሶች በረጃጅሙ ለምንይሉ ወንድሙ እና ፍፁም ገብረማርያም በማድረስ የሚደረግን ጥቃት ኢላማቸው ቢያደርጉም በሲዳማ ቡናዎች በፍጥነት ሲነጠቁ ተስተውሏል፡፡ 

ቶሎ ቶሎ ወደ መከላከያ ግብ መድረስ የቻሉት ሲዳማዎች ገና በጊዜ ነበር የግብ አጋጣሚን መፍጠር የቻሉት። ሐብታሙ ከመሐመድ ናስር የተቀበለውን ጥሩ ኳስ ወደ ግብነት ለወጠው ሲባል አበበ ጥላሁን ደርሶ እንድምንም ሲያስጥለው 7ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ መሐመድ ናስር በግንባሩ ገጭቶ ይድነቃቸው ኪዳኔ እንደምንም በአስደናቂ ብቃት አውጥቶበታል፡፡ በመከላያዎች በኩል 15ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ገብረማርያም ግብ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጭ ከተባለችው ሙከራ በቀር ተጨማሪ የጎል እድል ለመፍጠር ተቸግረዋል። 

ጨዋታው በሲዳማ የእንቅስቃሴ በላይነት ቀጥሎ . ሚሊዮን ሰለሞን በግንባር ገጭቶ ይድነቃቸው ሲያወጣበት አዲስ ግደይ በአንድ ሁለት ቅብብል ከመሐመድ ጋር በመጫወት አንድ ለአንድ የተገናኘው ግብ ጠባቂው ይድነቃቸውን ማለፍ ቢችልም ዓለምነህ ግርማ ከኋላ ደርሶ አስጥሎታል፡፡ ሐብታሙ ገዛኸኝ 28ኛው ደቂቃ ወደ ግብ ሙከራ አድርጎ የግቡ ቋሚ የመለሰበትም እንዲሁ ሌላው ለግብ የቀረበ ሙከራ ነው። ሁለት ደቂቃዎች በኋላ ፈቱዲን ጀማል ከራሱ ግብ ክልል እየገፋ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመቅረብ ያሻገረውን ኳስ አዲስ ግደይ ወደ ግብነት ለውጦ ሲዳማን ቀዳሚ አድርጓል። መከላከያወች ኳሷ ከጨዋታ ውጭ ነበረች በሚል ረዳት ዳኛው ሙስጠፋ መኪ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን አሰምተዋል፡፡ 

ከጎሉ በኋላ ሲዳማዎች ተጨመሪ ጎል ለማስቆጠር ብዙም ጊዜ አልፈጀባቸውም። 36ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ሐብታሙ ገዛኸኝ በቀኝ መስመር ያሻማትን ኳስ መሐመድ ናስር በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ሲዳማ ቡና 2-0 እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል አቅንተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ሲዳማ ቡናዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ብለው ቢታዩም የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ግን አልተቸገሩም። ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተንቀሳቅሰው ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያደረጉት መከላከያዎች ኳስን ተቆጣጥረው መጫወት ቢችሉም በሚገኙ ክፍት ዕድሎች ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጉት ግን ጥረት እምብዛም ነበር፡፡

47ኛው ደቂቃ ላይ ላይ ፍፁም ገብረማርያም መሀል ለመሀል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ፍቅሩ ያስጣለው ኳስ ምናልባትም መከላከያዎች ወደ ጨዋታ እንዲመለሱ ልታደርግ የምትችል አጋጣሚ ነበረች፡፡ በሲዳማ በኩል ደግሞ በመልሶ ማጥቃት በመስመር በኩል የተገኘችን ዕድል አዲስ ግደይ አግኝቶ በይድነቃቸው ኪዳኔ በግሩም ሁኔታ የተነጠቀው፣ አበባየሁ ዮሐንስ ከርቀት መትቶ ይድነቃቸው ኪዳኔ ያወጣበት እና ተቀይሮ ከገባ በኋላ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ጫላ ተሺታ በጭማሪ ደቂቃ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ሐብታሙ ያመከናት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ። 


ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች በሲዳማ ቡና አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሲዳማ ነጥቡን 20 በማድረስ ወደ ሁለተኛ ከፍ ሲል ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት መከላከያ በስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ከድል ርቆ በ9 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *