የኮከቦች የገንዘብ ሽልማት እስካሁን አልተፈፀመም

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ2010 የውድድር ዘመን የኮከቦች የሽልማት ገንዘብ ክፍያ እስካሁን ያልተፈፀመ መሆኑ በተሸላሚዎች ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል።

በ2010 የውድድር ዓመት በተደረጉ ሁሉም የሊግ ውድድሮች ላይ ኮከብ የሆኑ አሰልጣኞች ፣ ተጫዋቾች ፣ ጎል አስቆጣሪዎች እና ምስጉን ዳኞች ሽልማት መርሐ-ግብር ህዳር 6 በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት መካሄዱ ይታወቃል። ሆኖም በወቅቱ በስነ-ሥርዓቱ ላይ የተገለፁ የገንዘብ ሽልማቶች እስካሁን ለተሸላሚዎች ገቢ እንዳልተደረጉ ታውቋል።

ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ ኮከብ ተሸላሚዎች ለሶከር ኢትዮዽያ እንደተናገሩት እስካሁን የሽልማታቸው ገንዘብ ዛሬ ነገ ይሰጣችኋል እየተባለ ከሁለት ወር በላይ ሳይፈፀም መቅረቱ ቅር እንዳሰኘቸው ገልፀው ፌዴሬሽኑ ሽልማታቸውን እንዲሰጣቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

በዚህ ጉዳይ ፌዴሬሽኑን አናግረን በተሰጠን ምላሽ የፋይናስ ክፍሉ ክፍያውን ለመፈፀም ስራዎችን እየሰራ መሆኑን እና በቅርቡ ክፍያው እንደሚፈፀምላቸው ገልጿል። አምና በተለየ መልኩ በአንድ መድረክ ላይ መከናወን የጀመረው የኮከቦች ሽልማት በተመሳሳይ ሁኔታ እንደ ዘንድሮው ሁሉ ተሸላሚዎች ገንዘቡ ሊከፈለን አልቻለም በማለት ቅሬታቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ ዘግይቶ ክፍያውን መፈፀሙን መዘገባችን ይታወሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *