ሪፖርት | መቐለ ደቡብ ፖሊስን በማሸነፍ አራተኛ ተከታታይ ድል አሳክቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስን ከሜዳው ውጪ የገጠመው መቐለ 70 እንደርታ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ደቡብ ፖሊስ በሀዋሳ ሽንፈት ከገጠመው ቡድኑ ላይ የስድስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርጎል፡፡ በዚህም አበባው ቡታቆ ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ ፣ ዮናስ በርታ ፣ ልዑል ሀይሌ ፣ ብሩክ ኤልያስ እና ዘላለም ኢሳያስን በማስወጣት ዘሪሁን አንሼቦ ፣ አዲስአለም ደበበ ፣ ኤርሚያስ በላይ ፣ በኃይሉ ወገኔ ፣ የተሻ ግዛው እና መስፍን ኪዳኔን ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት አምጥቷል። መቐለዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ ቡናን ከረቱበት ጨዋታ ሥዩም ተስፋዬን በቢያድግልኝ ኤልያስ ብቻ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።

በከፍተኛው ሊግ ቅጣት የተጣለበት ሀላባ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ሲያደርጉት የነበረው ጨዋታ በጊዜ ባለመጠናቀቁ ምክንያት ጨዋታው ከተያዘለት ሰዓት 35 ያህል ደቂቃዎች ዘግይቶ ነበር የጀመረው። ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ያላቸውን ኃይል አሟጠው በመጠቀም ከውጤት ቀውስ ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች ገና በጊዜ በተከላካዮቻቸው መካከል በተፈጠረ ያለመናበብ ግብ ተቆጥሮባቸዋል፡፡ 4ኛው ደቂቃ ላይ ጋብሬል አህመድ በረጅሙ ወደ ፖሊስ የግብ ክልል ሲልካትን ኳስ ያሬድ ከበደ በቶሎ ወደ ግቡ ሲንደረደር ላስተዋለው አማኑኤል ገብረሚካኤል ሰጥቶት አማኑኤል በድንቅ አጨራረስ የፖሊስ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ገና በጊዜ መቐለን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡


ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ በግራ እና ቀኝ መስመሮች በአናጋው ባደግ እና የተሻ ግዛው ተጠቅመው አቻ ለመሆን ጥረታቸውን የቀጠሉት ደቡብ ፖሊሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መጠጋት ቢችሉም አጋጣሚዎችን ወደ ውጤት ለመለወጥ ግን ሲቸገሩ ታይቷል፡፡ የተሻ ግዛው በራሱ ጥረት ሁለት ጊዜ አግኝቶ የሳታቸው ኳሶች ለዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ መልሶ ማጥቃትን ምርጫቸው ያደረጉት መቐለዎች በተደጋጋሚ ከአማካይ ክፍሉ የሚነሱ የተሳኩ ኳሶችን ወደ አማኑኤል እና ያሬድ በማድረስ ተፅዕኖ ለመፍጠር ችለዋል፡፡ በተለይ ሐይደር ሸረፋ ከቡድን ጓደኞቹ ጋር የተሳኩ ቅብብሎችን ካደረገ በኃላ ይሰጣቸው የነበሩት ኳሶች በጉልህ ተጋላጭ ለነበረው የፖሊስ የተከላካይ ክፍል ስጋት ሲሆኑ ነበር። 12ኛው ደቂቃ ላይ ቢያድግልኝ ከሐይደር ተቀብሎ ያሻማው እና አንተነህ ገብረክርስቶስ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት ሙከራ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ ደቡብ ፖሊሶች አቻ ለመሆን ወደ መቐለ የሜዳ ክፍል አድልተው ቢጫወቱም ወደ ማጥቃት በሚሸጋገሩበት ወቅት በቁጥር በማነሳቸው የመከላከል አቅማቸውን ላጎለበቱት መቐለዎች ኳሶችን ማቋረጥ ከባድ አልነበረም።


31ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተገኘን ኳስ ተቀባብለው የጀመሩት መስፍን እና በኃይሉ ወደ ግብ ከተጠጉ በኃላ በኃይሉ አክርሮ ወደ ግብ መትቶ ፊሊፕ ኦቮኖ ሲተፋው ከግቡ ትይዩ የነበረው ደስታ ጊቻሞ ወደግብነት ለወጠው ሲባል መጠቀም ሳይችልባት ቀርቷል፡፡ 41ኛው ደቂቃ ላይ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው አዋጭ የሆነላቸው መቐለ 70 እንደርታዎች ሁለተኛ ግባቸውን አግኝተዋል፡፡ ቢያድግልኝ ኤልያስ በቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ ወደ ግብ የላካትን ኳስ አሁንም የተከላካዮች ስህተት ታክሎበት ያሬድ ከበደ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ የመቐለን መሪነት ወደ ሁለት ማሳደግ ችሏል፡፡ ከግቧ በኃላ በስታድየሙ የተገኘው ደጋፊ የደቡብ ፖሊሱን ግብ ጠባቂ ዳዊት አሰፋን ሲቃወምም ታይቷል፡፡ ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ ሰከንዶች ሲቀሩ በታየው የመጨረሻ ሙከራምየተሻ ግዛው የግብ አጋጣሚን አግኝቶ ኦቮኖ ይዞበታል፡፡


ከእረፍት መልስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተጫዋች ቅያሪን ያደረጉት ፖሊሶች ተቀዛቅዘው የታዩትን አዲስአለም ደበበን እና መስፍን ኪዳኔን በአበባው ቡታቆ እና ዘላለም ኢሳያስ በመተካት ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ አበባው ቡታቆ በ47ኛው ደቂቃ ወደ ሜዳ ከገባ በኃላ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ በማክረር መትቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት ሙከራም የምትነሳ ናት፡፡ በሌላ ሙከራ ደግሞ በኃይሉ ወገኔ ወደ ግብ ተጠግቶ አክርሮ መትቶ በርካታ ኳሶችን ሲያመክን የነበረው ኦቮኖ በሚገርም ሁኔታ አውጥቶበታል፡፡ ከእረፍት መልስ አጨዋወታቸውን በሙሉ ወደ መልሶ ማጥቃት የለወጡት መቐለዎች በደቡብ ፖሊስ የእንቅስቃሴ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በቀላሉ ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ክልል ይደርሱ ነበር፡፡ ከአጋጣሚዎቹ መካከልም 55ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ከተገኘች ኳስ ዮናስ ገረመው ለአማኑኤል ሰጥቶት አማኑኤል መጠቀም ሳይችልም ቀርቷል፡፡


ዘላለም ኢሳያስ ተቀይሮ ከገባ በኃላ መሀል ላይ ብልጫን መውሰድ የቻሉት ቢጫ ለባሾቹ ወደ ሳጥን መጠጋት ቢችሉም ከፍተኛ የአጨራረስ ችግራቸው ግብ ከማስቆጠር አግዷቸዋል፡፡ ኄኖክ አየለ ከዘላለም ያገኛቸውን ሁለት የማግባት አጋጣሚዎች ያመከነባቸው ቅፅበቶችም ለቡድኑ የሚያስቆጩ ነበሩ፡፡ በየተሻ ግዛው በኩል ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በማጥቃቱ የተሳካላቸው የነበሩት ፖሊሶች በየተሻ እና ዘላለም አስደንጋጭ ሊባሉ የሚችሉ ዕድሎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙባቸው የቀሩ ሲሆን 78ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው የተሻ የደረሰውን ኳስ ለአበባው አቀብሎት አበባው በቀጥታ ወደ ግብ ሲሞክር ኳስ በግቡ ቋሚ ስር አልፋ ወጥታበታለች ፡፡ በጭማሪው ደቂቃ ላይ ግን ዘላለም ኢሳያስ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ያሻገራትን ኳስ በተከታታይ ለደቡብ ፖሊስ ግብ እያስቆጠረ የሚገኘው ኄኖክ አየለ በግንባር በመግጨት ኳስ እና መረብን ቢያገናኝም ደቡብ ፖሊስን ከሽንፈት መታደግ ሳይችል ጨዋታው በመቐለ 2-1 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *