የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 0-0 አዳማ ከተማ 

የ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዐፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማን 0-0 ከተለያዩ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች በሚከተለው መልኩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
” ተጋጣሚያችን ይዘው የቀረቡት አቀራረብ ጨዋታውን የበለጠ ከባድ እንዲሆን አድርጎታል” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው

” እኛ ጨዋታውን ያደረግ ነዉ  በርካታ ቋሚ ተሳላፊዎች በሌሉበት ሁኔታ ነው። ቢሆንም ግን ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ አጥቅተን ለመጫወት እና የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሞክረናል በብዙ ነገር የተሻልን ነበርን። በመጨረሻም አስፈላጊውን 3 ነጥብ መያዝ አልቻልንም፤ ከዛዉጭ ያለዉ ነገር ግን ጥሩ ነው። ምን አልባት ተጋጣሚያችን ይዘው የቀረቡት አቀራረብ ጨዋታውን የበለጠ ከባድ እንዲሆን አድርጎታል። ነጥብ ከመጣላችን ውጪ ጨዋታዉ ላይ የነበረዉ እንቅስቃሴ፤ ተጫዋቾቼ ላይ ያየሁት የማሸነፍ ተነሳሽነት ጥሩ ነበር። ” 

የተጋጣሚ አጨዋወት የፈጠረው ተፅዕኖ

” ተፅዕኖ አለው፤ እንዳያችሁት በነሱ በኩል አንደኛ ብዙ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ናቸዉ ያሉት። በዛ ላይ ደግሞ አፈግፍገው ነው የሚጫወቱት። የኛ ስራ ያንን ሰብሮ መግባት ነበር፤ ግብ ማስቆጠር ነው የኛ ስራ። አልፎ አልፎ ከሰዓት ማባከን ጋር ያለው ነገር ተጫዋቾቼን ስሜታዊ ሊያደርጋቸው ችሏል። ”

ዳኝነት

” ስለ ዳኝነት ብዙ ምናገረዉ ነገር የለኝም። ምክንያቱም በሁለቱም ቡድን ሊወቀስ ይችላል። ነገር ግን ከሰዓት ማባከን ጋር ተያይዞ የሚደረጉ ነገሮች ብዙ አላስደሰቱኝም። ምክንያቱም ሜዳ የምንመጣዉ ከማሸነፍ መሸነፍ በተጨማሪ ለመጫወት ነው፤ ሜዳ የሚገባ ተጫዋች ኳስ መጫወት ነው ያለበት። 90 ደቂቃ ሳንጫወትበት ማለቅ የለበትም የሚል እምነት አለኝ። በተለይ ግብ ጠባቂው በርካታ ጊዜ ሰዓት ሲያባክን ነበር። ስለዚህ ያነን ማስጠንቀቅ መቻል ነበረባቸው። ከዕረፍት በፊት በርካታ ደቂቃዎች ባክነዉ 1 ደቂቃ ነበር የተጨመረው። ከእረፍት በኋላ 5 ደቂቃ ነው የተጨመረዉ። በኔ በኩል ያልተጨመረው ደቂቃ ይበዛል። ”

” ከፋሲል አንድ ነጥብ መውሰድ ማለት በጣም ትልቅ ነው” ሲሳይ አብርሀም – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው

” ጨዋታው ጥሩ ነው፤ ጥሩ ፉክክር ነበረው። ፋሲል ከነማ ጥሩ ነበሩ። ብዙ የግብ እድሎችን አምክነዋል። ይሄ በኳስ የሚያጋጥም ነው። ግን ደስ ያለኝ ሜዳ ላይ ያለዉ ነገር ንክኪ ቢኖረውም ተጫዋቾቸ ተባብረው ጨዋታውን ይዘውት ወጥተዋል። ከፋሲል አንድ ነጥብ መውሰድ ማለት በጣም ትልቅ ነው። ከሜዳ ዉጭ በዚህ ሁሉ ህዝብ መሀል ተጫውተህ መውሰድ ጥሩ ነው። ውበቱም የልጅነት ጓደኛዬ ነው፤ አለመጣላታችን (አቻ መዉጣታችን) ደስ ብሎኛል። 

” ፋሲል ጫና ፈጥሮብናል። መስመር ላይ የነበሩ ተጫዋቾች ጥሩዎች ናቸው። ሽመክት ጉግሣ እንዲሁም ሱራፌልም ወደ መስመር እየወጣ፤ ወደ ውስጥ እየገባ ነበር የሚጫወተው። የግድ እነሱን ማስቆም ነበረብን፤ ለዘም አፈግፍገን መጫወት መርጠናል። የሜዳው ሁኔታም ያንን እንድናደርግ አድርጎናል። የነሱ መስመራቸዉ ጥሩ ነበር። ያንን በመቋቋም በመልሶ ማጥቃት ነበር መጫወት የመረጥነው።”

ዳኝነት

” ጨዋታው  ትንሽ ግጭት ነበረው። ዳኛ ደግሞ ባየው ነገር ነው የሚፈርደው። አንዴ ከወሰነ ወሰነ ነው። እና ይሄንንም ችለህ ነው ሜዳ ዉስጥ መቆየት ያለብህ። ተጫዋቾቻችንም ይሄን ችለው ነው እንዲሄዱ ማድረግ ያለብን። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *