ሪፖርት | ስሑል ሽረ በፕሪምየር ሊጉ የመጀመርያ ድሉን አስመዘገበ

በ13ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስሑል ሽረ በሰዒድ ሁሴን ብቸኛ ጎል ታግዞ ደደቢትን በማሸነፍ ከ13 ሳምንታት ጥበቃ በኋላ የመጀመርያ የሊግ ድሉን አስመዝግቧል። 

ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ባለፈው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ከገጠመው ቡድናቸው ክዌክ ኢንዶህ እና አቤል እንዳለን  በኤፍሬም ጌታቸው እና እንዳለ ከበደ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ስሑል ሽረዎችም በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ሰዒድ ሁሴን እና ሳሙኤል ተስፋዬን በሙሉጌታ ዓንዶም እና አሸናፊ እንዳለ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሳቢ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና ንፁህ የግብ ሙከራዎች ባልታዩበት የመጀመርያው አጋማሽ በአንፃራዊነት እንግዶቹ ሽረዎች ተሽለው የታዩ ሲሆን በአንፃሩ ሰማያዊዎቹ በመጀመርያው አጋማሽ የሚታወቁበት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ሳይወስዱ እና ምንም ዒላማው የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ነበር ወደ ዕረፍት ያመሩት። 3-5-2 አሰላለፍ ምርጫቸው አድርገው ወደ ሜዳ የገቡት ሽረዎች ወደ ሁለቱም አጥቂዎች በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች መሰረት አድርገው ሲጫወቱ በርከት ያሉ ዕድሎችም ፈጥረዋል። በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጅላሎ ሻፊ የፈጠራቸው ዕድሎችም የተሻለ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በተለይም አማካዩ ከርቀት መቷት ለጥቂት የወጣችበት፣ ሙሉጌታ ዓንዶም አሻምቷት ልደቱ ለማ በግንባሩ ገጭቶ የወጣበት፣ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ደሳለኝ ደባሽ በግንባሩ ገጭቶ የወጣበት እንዲሁም ልደቱ ለማ መትቶ ረሺድ ማታውሲ የመለሳት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

ከዚ በተጨማሪ በመጀመርያው አጋማሽ ላይ በደደቢት ሳጥን ጠርዝ ላይ የተገኘችውን ቅጣት ምት ደደቢቶች በአምስት ተከላካዮች አጥር ሰርተው ለመከላከል ሲጥሩ በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ብዙ የቁጥር ብልጫ የነበራቸው ሽረዎች ዕድሉን ሳይጠቀሙበት የቀሩ ሲሆን አጋጣሚው የሁለቱም ቡድኖች የቆመ ኳስ አጠቃቀም እና የመከላከል ድክመት የታየበት ነበር።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ፍሰት ደረጃ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ቢሆንም ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። ዳንኤን ጌድዮን እና አቤል እንዳለ ቀይረው ወደ ሜዳ በማስገባት የተወሰደባቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በማርገብ ሁለቱ የስሑል ሽረ ተመላላሾች (wing back) ትተውት የሚሄዱትን ክፍተት ተጠቅመው በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ፍፁም ብልጫ የወሰዱት ደደቢቶች እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በግቡ አፋፍ የነበረው ዳንኤል ጌድዮን ከመስመር የተሻገረችለትን ኳስ መትቶ ተከላካዮች ተደርበው ለጥቂት ያወጧት እና ዓለምአንተ ካሳ ብቻውን በነፃ አቋቋም ከግብ ጠባቂው ተገናኝቶ ለጥቂት ያመከናት ወርቃማ ዕድሎችም የሚጠቀሱ ነበሩ። ከዚ ውጭ በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ማሻሻያዎች አድርገው ወደ ሜዳ የተመለሱት ደደቢቶች በዳንኤል ጌድዮን እና ዓለምአንተ ካሳ ሌሎች ወደ ግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ዳንኤል ጌድዮን አክርሮ መቷት ሃፍቶም ቢሰጠኝ በሚያስደንቅ ሁኔታ የመለሳት ኳስ ደደቢትን ቀዳሚ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

በሁለተኛው አጋማሽ ከተጋጣሚያቸው አንፃር ሲታይ ወርደው የታዩት ሽረዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በርካታ ቅያሪዎች በማድረግ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። በዚህም ተቀይሮ የገባው ሰዒድ ሁሴን በ83ኛው ደቂቃ ከሚድ ፎፋና የተላከችለትን ኳስ ጨርፎ በማስቆጠር ቡድኑ መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ከዳኛው ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ሲገባ የታየው የደደቢቱ አቤል እንዳለ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ስሑል ሽረዎች በዓመቱ የመጀመርያ ሶስት ነጥብ ሲያገኙ ቀሩ ጨዋታዎች እያላቸው በመጨረሻ ደረጃ የሚገኙት ደደቢቶች ከበላዮቻቸው ጋር ያላቸውን ልዩነት ማጥበብ አዳጋች ሆኖባቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *