ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ አቻ ተለያይተዋል

በ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪምየር ሊግ ዛሬ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ባህር ዳር ከተማን ያስተናገደበት ጨዋታ በ1-1 ውጤት ተፈፅሟል።

ወላይታ ድቻዎች በ12ኛው ሳምንት ጅማ ላይ 2-0 ከተሽነፉበት ጨዋታ ውብሸት ክፍሌን ከቅጣት በተመለሰው እሸቱ መና ብቻ በመለወጥ ወደ ሜዳ ሲገቡ እንግዳው ባህር ዳር ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ከተለያየበት አሰላለፍ ውስጥ በተመሳሳይ የአንድ  ተጫዋች ለውጥ በማድረግ  ማራኪ ወርቁን በግርማ ዲሳሳ ለውጦ ጨዋታውን ጀምሯል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በ12ኛው ሳምንት ከባህር ዳር ወደ ጎንደር ክለባቸውን ደግፈው ሲመለሱ በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ላጡት ሁለት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል።


እልህ እና ወጥረት የተሞላበት እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ቀዳሚ 30 ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ ድቻዎች ከገጠማቸው የደጋፊ ጫና ለመውጣት በሚመስል መልኩ በተደጋጋሚ በሁለቱም መስመሮች በዘላለም እያሱ ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና ሳምሶን ቆልቻ አማካይነት ወደ ባህር ዳር ከነማ የግብ ክልል ሲገቡ እና ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በአንፃሩ የጣና ሞገዶቹ በነዚህ ደቂቃዎች ውስጥ በድቻ ተደጋጋሚ ጫና መፍጠር ምክንያት ሲረበሹ እና የጨዋታውን ቅርጽ ለማግኘት ሲቸገሩ ነበር።

ጨዋታው በተጀመረ ጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ሙከራ ማድረግ በጀመሩት ድቻዎች በኩል ቸርነት ጉግሳ ከመሃል የተሻገረለት ኳስ ላይ ለመድረስ ጥረት ቢያደርግም ሃሪሰን በፍጥነት በመውጣት ኳሷን የያዘበት እንዲሁም በ5ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረለትን ኳስ ሳምሶን ቆልቻ በግንባሩ ሞክሮ ኳስ ሃሪሰንን ብታልፍም የባህር ዳር ተከላካዮች እንደምንም ከመስመር ላይ ያራቁበት ሙከራዎች ጥሩ አጋጣሚዎች ነበሩ። ድቻዎች ፍፁም የበላይነት ባሳዩበት በዚህ አጋማሽ 15 ደቂቃ ላይም ከግራ ጠርዝ ላይ የተገኘችውን ኳስ ኄኖክ አረፊጮ አክርሮ ቢመታም ሙከራው የግቡን አግዳሚ ታካ ወጥታበታለች። የዕለቱ የመጀመርያ ግብ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ስትቆጠርም ባዬ ገዛኸኝ በቀኝ የሜዳው ክፍል በቅብብል ከሳጥን ውጪ ያገኛትን ኳስ በአግባቡ በመቆጣጠር ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ በግሩም ሁኔታ ከሃሪሰን መረብ ላይ አሳርፏታል።


ከግቧ መቆጠር በኋላ የጣና ሞገዶቹ ከጫና ውስጥ ለመውጣት መሀል ሜዳ ላይ በደረጄ መንግስቱ እና ኤልያስ አህመድ አማካይነት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በመጀመርያ ሙከራቸውም በ26ኛው ደቂቃ ግርማ ዲሳሳ ከረቀት አክርሮ የመታው ኳስ በታሪክ ጌትነት የተመለሰ ሲሆን ወደ መረጋጋት ተመልሰውም አቻ የምታደርጋቸውን ግብ በ43ኛው ደቂቃ ላይ አግኘተዋል። ከማሀል ሜዳ ኤልያስ አህመድ ያሻገራትን ኳስ ጃኮ አራፋት በአግባቡ በመጠቀም ታሪክ ጌትነት መውጣቱን በመመልከት ከፍ አድርጎ በመምታት ነበር ማስቆጠር የቻለው። ጃኮ አራፍት ግብ ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን ባለመግለፅ ለቀድሞ ክለቡ ያለውን ክብርም አሳይቷል።


በሁለተኛው አጋማሽ ባህር ዳሮች እጅግ ተሻሽለው ወደ ሜዳ የገቡበት እና የሚያስቆጭ የግብ አጋጣሚም ያመከኑበት ነበር። በአንፃሩ ድቻዎች በመጀመርያው አጋማሽ የነበራቸው ተነሳሽነት የቀዘቀዘበት እና ግልፅ የሆነ ሙከራ ያላደረጉበት ነበር። በ48ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ ከመሀል የተሻገረለትን ኳስ ግርማ ዲሳሳ ለብቻው በማግኘት እየገፋ ግብ ጠባቂው ጋር በመድረስ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ሙከራው በማይታመን መልኩ በግቡ አናት ወጥቷል። ድቻዎች የመሀል ሜዳ ብልጫ የተወሰደባቸው በመሆኑ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር ይልቅ ከርቀት በመሞከር ግብ ለማግኘት ሲጥሩም ነበር። በ66ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወልዴ ከርቀት ካደረገው ሙከራ ውጪም ምንም ዓይነት አጋጣሚ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ኳሱን በመቆጣጠር ጥሩ የነበሩት ባህር ዳር ከነማዎች በግራ መስመር በአስናቀ ሞገስ ማራኪ እንቅስቃሴ በማድረግ 75ኛው ደቂቃ ላይ ያሻገረውን ኳስ ወሰኑ ዓሊ በቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት ወደ ጎል በመምታት አስቆጠረ ሲባል ወደ ላይ የላካት ኳስ ጥሩ ሙከራ ነበረች።


ጨዋታው ሊጠናቅቅ 10 ደቂቃዎች ሲቀሩት ድቻዎች የማሸነፊያውን ግብ ለማግኘት ወደ ማጥቃቱ ለመመለስ ቢሞክሩም የጠራ የግብ አጋጣሚ መፍጠር ተስኗቸዋል። በተቃራኒው ባህር ዳር ከነማዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ ውጤት አስጠብቀው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ከሜዳቸው ውጪ አንድ ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል። በጨዋታው በተጨመሩት አራት ደቂቃዎችም ምንም ዓይነት ግብ ሳይስተናገድ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በዕለቱ ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው በተደጋጋሚ ከባህርዳር ከነማ የአሰልጣኞች ስብስብ ቅሬታ ሲያስተናግዱም ተስተውሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *