ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ነገ ከሚደረጉ ተስተካካይ ጨዋታዎች መካከል አንዱ በሆነው የአዳማ እና የጊዮርጊስ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ምክንያት በይደር ተይዘው ከቆዩት የ2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ነገ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም 09፡00 ላይ የሚከናወነው የአዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ አንዱ ነው። በመጨረሻ ሰዓት በተቆጠረባቸው ግብ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ለመጋራት የተገደዱት አዳማዎች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የጣሏቸው ነጥቦች ወደ አራተኛነት ከፍ የሚሉበትን ዕድል አስመልጧቸው 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በተመሳሳይ ከፋሲል ጋር አቻ የተለያየው ቅዱስ ጊዮርጊስም ሦስት ተስተካካይ ጨዋታ ካለው ተከታዩ መቐለ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ብሏል። በመሆኑም የመጀመሪያውን ዙር በመሪነት ለማጠናቀቅ በተለይም በቅርብ ዓመታት እጅግ ወደሚቸገርበት ስታድየም አቅንቶ በሙሉ ነጥብ መመለስ ግድ ይለዋል። አዳማ ከተማም እስካሁን ሄድ መለስ እያለ ወደ ኋላ እየቀረበት ካለው የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመገኘት ነጥቦቹ ያስፈልጉታል።

አዳማ ከተማ በወልዋሎው ጨዋታ በቀይ ካርድ የወጣው ቡልቻ ሹራን በቅጣት የሚያጣ ሲሆን አንዳርጋቸው ይላቅም በጉዳት ምክንያት ጨዋታው ያልፈዋል። በሌላ በኩል ከነበረበት ጉዳት ያገገመው ሱራፌል ጌታቸው ለዚህ ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን በወላይታ ድቻው ጨዋታ ላይ በህመም ያልተሰለፈው ዳዋ ሆቴሳም መመለስ አጠራጣሪ ነው። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አዲስ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኘው መሀሪ መናን እንዲሁም ሳልሀዲን በርጌቾ እና ጌታነህ ከበደም ወደ አዳማ በተጓዘው ስብስብ ውስጥ አልተካተቱም።

ባለሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች የአጥቂያቸው ዳዋ ሆቴሳ አለመኖር በድቻው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ እንዳያገኙ ያደረጋቸው ይመስላል። ነገም ቡድኑ የሚያገኛቸው የግብ ዕድሎችን ለመጨረስ ዳዋ ሆቴሳን ወደ ሜዳ ሊመልስ የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው። ከዛ ውጪ ከተጋጣሚው የመስመር ተመላላሾች እንቅስቃሴ አንፃር የመስመር ተከላካዮቸን በማጥቃት ላይ ለማሳተፍ ሊቸገር ስለሚችል መሀል ላይ የከንዓን ማርክነህን ልዩ ብቃት ይጠብቃል። በከንዓን ከሌሎቹ አማካዮች በተለይም ከበረከት ደስታ ጋር የሚፈጥረው የቅብብል ግንኙነቶችም ከጊዮርጊስ የመሀል ተከላካዮች ግራ እና ቀኝ ባሉ ቦታዎች ወደ ውስጥ ለመግባት ወሳኝነታቸው የጎላ ነው። በተሻጋሪ ኳሶቻቸው ጥራት ደስተኛ የሆኑ የማይመስሉት ጊዮርጊሶች ነገም ተመሳሳይ አካሄድን የሚመርጡ ይመስላሉ። ሆኖም በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ከሁለቱ አጥቂዎቻቸው በተጨማሪ የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎቻቸው ተሳትፎ ካልታከለበት በቀር በአዳማ የመሀል ተከላካዮች እና በነኢስማኤል ሳንጋሪ መካከል ያለው ቦታ ላይ ልዩነት ለመፍጠር ከባድ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 34 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ 17 ድል በማስመዝገብ የበላይ ሲሆን አዳማ ከተማ 7 አሸንፏል፡፡ 10 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ 2005 7-0 ያሸነፈበትን ጨዋታ ጨምሮ እስካሁን 44 ግቦች ሲያስቆጥር አዳማ ከተማ ደግሞ 24 ጎሎች አሉት፡፡

– አዳማ ላይ በተደረጉ 17 ጨዋታዎች አዳማ ከተማ 7 ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 ድሎችን ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ 6 ጊዜ አቻ ሲለያዩ አዳማ 17 ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ 11 ጎሎች አስቆጥረዋል፡፡

– አዳማ ከተማ በአጠቃላይ ላለፉት ስድስት ጨዋታዎች በሜዳው ደግሞ ወደ ሊጉ ከተመለሰበት የ2007 የውድድር ዓመት ጀምሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ አልተሸነፈም። ጊዮርጊስ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ያሳካው የ2005ቱ የመጨረሻ የ2-1 ድል ስድስት ዓመታትን አስቆጥሯል።

– ዘንድሮ አምስት ጊዜ ከአዲስ አበባ የወጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አንድ የሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት ሲገጥማቸው በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግን በተመሳሳይ የ 1-0 ድሎች ተመልሰዋል።

– አዳማ ከተማ በሜዳው ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤትን ሲያስመዘግብ አራት ጨዋታዎችን በድል መወጣት ችሏል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ከኦርላንዶ ፓይሬትስ እና ኤስፕራንስ ደ ቱኒዝ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ መልስ ይህን ጨዋታ ይዳኛል። አርቢትሩ ዘንድሮ በመራው ብቸኛው የአባ ጅፋር እና ድቻ የ12ኛው ሳምንት ጨዋታ ምንም ካርድ ሳይመዝ ጨርሷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱለይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ

አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ

ሱራፌል ዳንኤል – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሆቴሳ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)

ፓትሪክ ማታሲ

አስቻለው ታመነ – ምንተስኖት አዳነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ

በኃይሉ አሰፋ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ – ኄኖክ አዱኛ

ታደለ መንገሻ

ሳላሀዲን ሰዒድ – አቤል ያለው


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *