ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደደቢት ከ መከላከያ

ደደቢት እና መከላከያን የሚያገናኘውን የ4ኛ ሳምንትተስተካካይ መርሐግብር እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ነገ 09፡00 ላይ በትግራይ ስታድየም የሚደረገው የደደቢት እና የመከላከያ ጨዋታ በኦሊምፒክ ቡድኑ የማጣሪያ ውድድር ምክንያት የተዘዋወረ ነበር። ቡድኖቹ እስከ 14ኛው ሳምንት ያደረጉት ጉዞ በወራጅ ቀጠና ውስጥ አስቀምጧቸው የሚገናኙ በመሆኑም ካሉበት ስጋት እፎይ ለማለት ከጨዋታው የሚገኙ ነጥቦችን አጥብቀው ይፈልጋሉ። በተለይም መከላከያ ከ7ኛው ሳምንት ጀምሮ ድል ያላስመዘገበ በመሆኑ ከዚያ በፊት የነበረው ደህና የሚባል ውጤት የተረሳ ይመስላል። በርግጥ ከነገው ጨዋታ ውጤት ይዞ ከተመለሰ ሁለት ደረጃዎችን የማሻሻል ዕድል መያዙ እና ሌሎች ተስተካካይ ጨዋታዎች ያሉት መሆኑ ከተጋጣሚው ደደቢት የተሻለ ያደርገዋል። ደደቢትም የነገው ጨዋታ ምንም ተስተካካይ ጨዋታ ወደሌለው ደቡብ ፖሊስ ሊያቀርበው የሚችል በመሆኑ የመጀመሪያውን ዙር ከመውረድ ስጋት ነፃ ባይሆን እንኳ ለሁለተኛው ተስፋ ለመሰነቅ ነገ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

አዲስ የጉዳት ዜና የሌለበት ደደቢት በጨዋታው አማካዩ አቤል እንዳለን በቀይ ካርድ ቅጣት የማይጠቀም ሲሆን ዓለምአንተ ካሳ ከጉዳት ኩማ ደምሴ ደግሞ ከቅጣት ተመልሰውለታል። የመጨረሻ ጨዋታውን እዛው ትግራይ ስታድየም ላይ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ያደረገው መከላከያም በተመሳሳይ የተጎዳበት ተጨዋች የሌለ ሲሆን መቐለን የገጠመበትን ስብስብ ይጠቀማል።

ጨዋታው የሊጉ ደካማ የአጥቂ ክፍል ከደካማው የተከላካይ መስመር የሚገናኝበት ነው። እስካሁን ሦስት ግቦች ብቻ ማስቆጠር የቻሉት ደደቢቶች ተጋጣሚያቸው 26 ግቦችን ማስተናገዱ የሚጨምርላቸው በራስ መተማመን ቢኖርም የቡድኑ አጠቃላይ የማጥቃት ሂደት ከተጋጣሚ ግብ ክልል እጅግ ርቀው በሚከውኑ ቅብብሎች ላይ መመስረቱ በቂ የግብ አጋጣሚዎችን እንዳይፈጥሩ እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችላል። ሆኖም ከመከላከያ የኋላ ክፍል ጀርባ በየጨዋታው የሚታየው ሰፊ ክፍተትን ያለሙ ረጅም ኳሶችን ሊጠቀሙ የሚችሉበት አግባብ አለ። ከ11 ጨዋታዎች በሁለቱ ላይ ብቻ ግብ ማስቆጠር ላቃታቸው መከላከያዎች አሁንም ጥያቄው የተከላካዮቻቸው እና የግብ ጠባቂያቸው ጉዳይ ነው። ቡድኑ አሁንም ወደ መከላከል በሚሸጋገርበት ጊዜ ያለው ደካማ የጊዜ እና ቦታ አሸፋፈን እንዲሁም ከአማካዮቹ የሚያገኘው ስስ የመከላከል ሽፋን ከሚታይበት አለመረጋጋት ከሚመነጩ የግለሰብ ስህተቶች ጋር ተደምሮ በነገው ጨዋታ ፈተና ሊሆንበት መቻሉ ዕሙን ነው። በማጥቃቱ በኩል ግን ቡድኑ ከኳስ ቁጥጥር ላይ በተመሰረተ አጨዋወት ለፊትት አጥቂዎቹ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚያቅድ ይገመታል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በአዲስ አበባ ስታድየም 18 ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች አራት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ ደደቢት ዘጠኝ መከላከያ ደግሞ አራት ድል አሳክተዋል። ደደቢት 32 ግቦችን ሲያስቆጥር መከላከያም 20 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

– በትግራይ ስታድየም ስድስት ጨዋታዎችን ያደረገው ደደቢት አራት ሽንፈቶች የገጠመው ሲሆን በሁለቱ ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን አሳክቷል።

– አምስት ነጥቦችን ከሜዳው ውጪ ያገኘው መከላከያ ከአዲስ አበባ ስታድየም ወጥቶ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈቶች ገጥመውታል።

ዳኛ

– በ5ኛ እና 13ኛ ሳምንታት ሁለት ጨዋታዎችን ዳኝቶ ስድስት የቢጫ ካርዶች የመዘዘው በፀጋው ሽብሩ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ – አዲሱ ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ሙሉቀን ደሳለኝ

ቴዎድሮስ ታፈሰ

ሳሙኤል ታዬ – ፍሬው ሰለሞን

ዳዊት እስጢፋኖስ

ተመስገን ገብረኪዳን – ምንይሉ ወንድሙ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውሲ

መድሀኔ ብርሀኔ – ዳዊት ወርቁ – ክዌኪ አንዶህ – ኄኖክ መርሹ

ኩማ ደምሴ – የዓብስራ ተስፋዬ

ዳግማዊ ዓባይ – ዓለምአንተ ካሳ – እንዳለ ከበደ

አሌክሳንደር ዐወት


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *