ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ሲዳማ ቡና

የመጨረሻው የዛሬ ቅድመ ዳሰሳችን ትኩረት በገለልተኛ ሜዳ የሚደረገው የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ይሆናል።

በአካባቢው የነበረውን አለመረጋጋት ወደነበረበት ለመመለስ የሚደረገው ዕርቅ ሂደት ላይ መሆኑን ተከትሎ በብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታ ምክንያት ተላልፎ የቆየው የሁለተኛው ሳምንት የድቻ እና ሲዳማ ጨዋታ በሲዳማ ጥያቄ መሰረት ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም 11፡00 ላይ ይደረጋል። ከስድስተኛው ሳምንት በኋላ ከድል የራቀው ወላይታ ድቻ የመጨረሻዎቹን ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ቢያጠናቅቅም አሁንም 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ለማለትም በፕሪምየር ሊግ ታሪኩ አንድ ጊዜ ብቻ ካሸነፈው ሲዳማ ቡና ሙሉ ነጥብ የመውሰድ ፈተና ይጠብቀዋል። በተቃራኒው በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ደግሞ ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎችን ሀዋሳ ላይ አድርጎ ሙሉ ዘጠኝ ነጥብ በመሰብሰብ በሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በመቐለ ከተረታበት የመጨረሻ የሜዳ ውጪ ጨዋታ አንድ ወር በኋላም ከሀዋሳ በመውጣት ከሚያደርገው የነገው ጨዋታም መሪ ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ። 

ወላይታ ድቻ በመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ ሲያካትታቸው ከሚታዩ ተጫዋቾቹ መካከል አምስቱ ነገ ቡድኑን ማገልገል አይችሉም። በዚህም የአምስተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት ያለበት ወጣቱ አማካይ በረከት ወልዴን ጨምሮ ጉዳት ላይ የሚገኙት ፍፁም ተፈሪ ፣ ዓንዱአለም ንጉሴ ፣ እዮብ አለማየሁ እና ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት በጉዳት ጨዋታው ያልፋቸዋል። ሲዳማ ቡና ግን ያለ ቅጣት እና ጉዳት ዜና ሙሉ ስብስቡን ይዞ ለጨዋታው ይቀርባል።

ወላይታ ድቻዎች በጨዋታው ኳስ ይዘው መጫወት የዕቅዳቸው አካል እንደሚሆን ሲጠበቅ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱ በሲዳማ የኋላ እና የአማካይ ክፍል መሀል ክፍተቶችን የመፍጠር ጉልበት እንዲኖረው ያስፈልጋል። ይህ የማይሆን ከሆነ እና የቅብብል ስህተቶችን በሲዳማ የሜዳ አጋማሽ ላይ የሚያበዙ ከሆነ ግን ለመልሶ ማጥቃት መጋለጣቸው የማይቀር ነው። በመሆኑም የአማካዮቻቸው ንቃት እና በቶሎ ወደ መከላከል የመሸጋገር ብቃት እጅግ አስፈላጊያቸው ነው። ከአዲስ ግደይ በተጨማሪ የመሀመድ ናስር እና ሀብታሙ ገዛኸኝ ወደ ጥሩ አቋም እና ግብ ማስቆጠሩ መምጣት ሲዳማን የአስፈሪ የአጥቂ ክፍል ባለቤት አድርጎታል። ነገም በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ግብነት ለመቀየር የአጥቂዎቹ በራስ መተማመን መዳበር ሊረዳው እንደሚችል ይታመናል። ከዚህ ውጪ በደደቢቱ ጨዋታ ምርጥ አቋሙን ያሳየው ሚሊዮን ሰለሞን የግራ መስመር የማጥቃት ተሳትፎ ለሲዳማ ቡና ተጨማሪ የጥቃት ምንጭ እንደሚሆንም ይጠበቃል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 10 ጊዜ ተገናኝተው ድቻ አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ ፣ በአራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ ቡና ደግሞ 5 ጊዜ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ድቻ 4  ሲዳማ ደግሞ 10 ጎሎች አስቆጥረዋል።

– ወላይታ ድቻ ሲዳማ ቡና ላይ ካስመዘገበው ብቸኛው የ2007ቱ የ2-1 ድል በኋላ ማሸነፍ አልቻለም።

– አምና በተገናኙባቸው ጨዋታዎች በመጀመሪያው ዙር ሲዳማ ቡና 3-1 ሲያሸንፍ በሁለተኛው ዙር 2-0 ሲመራ የቆየው ወላይታ ድቻ ወደ ፋሲል በተዘዋወረው የቀድሞው አማካዩ በዛብህ መለዮ የመጨረሻ ደቂቃ ግቤች ነጥብ ተጋርቷል።

ዳኛ

– ጨዋታው ለኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ አምስተኛ የሊጉ ጨዋታው ይሆናል። በእስካሁኖቹ አራት ጨዋታዎችም አርቢትሩ 14 የቢጫ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)

መኳንንት አሸናፊ

እሸቱ መና – ዐወል አብደላ – ውብሸት ዓለማየሁ –  ኄኖክ አርፊጮ

ኄኖክ ኢሳይያስ – ኃይማኖት ወርቁ

ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ  – ዘላለም እያሱ

ባዬ ገዛኸኝ                                  

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ግሩም አሰፋ – ፈቱዲን ጀማል – ግርማ በቀለ – ሚሊዮን ሰለሞን

ወንድሜነህ ዓይናለም – ዮሴፍ ዮሃንስ – ዳዊት ተፈራ 

ሐብታሙ ገዛኸኝ – መሀመድ ናስር –  አዲስ ግደይ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *