ሪፖርት | ስድስት ጎል በተቆጠረበት ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር እና ድሬዳዋ ከተማ አቻ ተለያይተዋል

በጅማ አባ ጅፋር የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ ምክንያት በአራተኛ ሳምንት ሳይካሄድ የቆየው የጅማ አባ ጅፋር እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ዛሬ ተከናውኖ 3-3 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጅማዎች ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳቸው ከባህር ዳር ከተማ ጋር አንድ አቻ ከተለያየው ስብስባቸው ውስጥ ዘርይሁን ታደለን በሚኪያስ ጌቱ፣ ይሁን እንደሻውን በኤልያስ ማሞ በመተካት ወደ ሜዳ ሲገቡ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ወደ ሀዋሳ አቅንተው ሀዋሳ ከተማን የረቱበትን የመጀመርያ አሰላለፍ ሳይለውጡ የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል።

ሁለቱ የጅማ ተወላጆች የሆኑት ወድማማቾችን (የጅማው የመሐል ተከላካይ ወላኩ ወልዴ እና የድሬዳዋው አጥቂ ሐብታሙ ወልዴ) በተቃራኒ እርስ በእርስ ያፋጠጠው ጨዋታ ላይ የተቆጠሩት ስድስት ግቦች በሙሉ በአስገራሚ ሁኔታ መጀመርያው አጋማሽ የተቆጠሩ ነበሩ።

ባለሜዳዎቹ ባልተለመደ መልኩ በተጋጣሚያቸው የመሐል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶባቸዋል። በ4-3-3 አሰላለፍ ሁለት የማጥቃት ባህርይ ያላቸው አማካዮች መስዑድ መሐመድ እና ኤልያስ ማሞ ወደፊት በሚሄዱበት ጊዜ ሲጋለጥ የነበረው አክሊሉ ዋለልኝ ለተከላካዮች የሚሰጠው ሽፍን በቂ ካለመሆኑ በተጨማሪ ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች ኳስ በድሬዳዋዎች እግር ስር ሲገባ የመከላከል ተነሳሽነታቸው አነስተኛ ሆኖ ታይቷል። እነዚህን ክፍተቶች በሚገባ የተጠቀሙት ድሬዳዋዎችም በሚኪያስ ግርማ እና ምንያህል ጥምረት ኳሶችን በፍጥነት የማስጣል እና የሚያደርጉት ፈጣን ወደ ማጥቃት ሽግግር የመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎችን ለጅማዎች አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል፡፡ በዚህም በ7ኛው ደቂቃ ሚኪያስ ግርማ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ የጅማው ግብ ጠባቂ ሚኪያስ ጌቱ ገጭቶ ቢመልሳትም ኳሷ ከግብ ክልሉ ባለመራቋ ከጅማ ተከላካዮች ትኩረት ማነስ ጋር ተደምሮ በቅርበት የነበረው ገናናው ረጋሳ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል፡፡

የድሬዳዎች ጫና ቀጥሎ በመልሶ ማጥቃት በ13ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ ኳስን በግራ መስመር እየገፋ ወደ ጅማ ግብ ክልል የገባው ራምኬል ሎክ የድሬዳዋዎችን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ግቡ መቆጠሩን ተከትሎ በተወሰደባቸው የጨዋታ ብልጫና በተቆጠሩባቸው ሁለት ግቦች የተበሳጩ ደጋፊዎች በቡድኑ አመራሮች፣ ረዳት አሰልጣኞች እና ግብ ጠባቂው ሚኪያስ ጌቱ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ የተወሰኑ ደጋፊዎችም ወደ ሜዳ ለመግባት በመሞከራቸው ጨዋታው ለ5 ደቂቃ ተቋርጧል። ሆኖም ብዛት ያላቸው የፀጥታ ኃይሎች በቦታው በመኖራቸው ሁኔታውን በፍጥነት ለመቆጣጠር ችለዋል።

ጨዋታው ከተቋረጠበት ከቀጠለ በኋላ ጅማዎች እንደ ቡድን የተደራጀ እንቅስቃሴ ባያደርጉም በግል በሚደረጉ ጥረቶችና በተሻጋሪ ኳሶች ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል መድረስ ችለዋል። በ24ኛው ደቂቃም በቀኝ መስመር ከዲዲዬ ለብሪ የተሰጠውን ኳስ ቀጥታ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ማማዱ ሲዴቤ የጅማዎችን ተስፍ ያለመለመች ጎል ማስቆጠር ችሏል።


ከግቡ መቆጠር በኋላ በተወሰነ መልኩ ወደ ጨዋታው በመመለስ መረጋጋት የቻሉት ጅማዎች ኤልያስ ማሞን ወደኋላ በመመለስ ኳስን ለማደራጀት እና የኳስን በማንሸራሸር በተወሰነ መልኩ የተወሰደባቸውን የጨዋታ ብልጫ ለማመጣን ሞክረዋል። ሆኖም በዚህ ሁኔታ ላይ በ34ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ሚኪያስ ተጠልፎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ራሱ ሚኪያስ በረጅሙ ሲያሻግረው በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ፍሬድ ሙሸንዲ አስቆጥሮ የድሬዳዋን መሪነት ወደ 3-1 ከፍ አድርጓል። ብዙም ሳይቆይ በ38ኛው ደቂቃ በዕለቱ ከደጋፊዎች ተቃውሞ ሲደርስበት የነበረው ግብ ጠባቂ ሚኪያስ ጌቱ በዘርይሁን ታደለ ተቀይሮ ወጥቷል።

ከ40ኛው ደቂቃ በኋላ ድሬዳዋዎች የግብ ልዩነቱን አስጠብቀው ወደ እረፍት ለመውጣት በተደጋጋሚ በመውደቅ ሰዓት ለመግደል ሲሞክሩ በአንፃሩ ጅማዎች ኳስን ከማንሸራሸር ይልቅ በተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም ወደ ድሬዳዋ የግብ ቶሎ ቶሎ ደርሰዋል። በዚህም በ44ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ውስጥ መስዑድ ያሻገረውን ኳስ ማማዱ ሲድቤ የግብ ልዩነቱን ያጠበበች ጎል አስቆጥሯል። በመሐል ዳኛው የተጨመረው ስድስት ደቂቃ መገባደጃ ላይ ደግሞ በጥሩ ቅብብል የድሬዳዋ የግብ ክልል በመግባት የተከላዮች ሰህተት ተደምሮ አስቻለው ግርማ ጅማዎችን አቻ ያደረገች ግብ አስቆጥሮ በ3-3 ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከዕረፍት መልስ በኳስ ቁጥጥር ድሬዳዎች የተሻሉ ቢሆኑም ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ጅማዎች የተሻሉ ነበሩ። በ51ኛው ደቂቃ ዲዲዬ ለብሪ በቀኝ መስመር ሁለት ተከላካዮችን አታሎ አልፎ የሰጠውን ኳስ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ የነበረው መስዑድ ሞክሮ የግቡን አግዳሚ ታካ የወጣችበት፤ በ59ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል ውስጥ ገብተው አስቻለው ያመከነው ጥሩ የግብ ማግባት ዕድል በጥሩ አጋጣሚነታቸው የሚጠቀሱ ነበሩ።

ከ70ኛው ደቂቃ በኃላ ኳሱን ለጅማዎች በመልቀቅ ወደ መከላከሉ ያመዘኑት ድሬዳዎች ከመከላከሉም ባሻገር ኳስን በማዘግየትና በተደጋጋሚ በመውደቅ ሰዓት በማባከን እንዲሁም የጅማዎችን ተነሳሽነት ለማቀዝቀዝ የተጠቀሙት ታክቲክ ተሳክቶላቸዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም ከጠሩ የግብ እድሎች እና ሙከራዎች ይልቅ ተሻጋሪ ኳሶች የተበራከቱበት ነበሩ። ከመጀመርያው አጋማሽ የጎል ብዛት አንፃር ተጨማሪ ጎሎች ይቆጠራሉ ተብሎ ቢጠበቅም ጨዋታው መጀርያ አጋማሽ በተቆጠሩ ስድስት ግቦች 3-3 ተጠናቋል።

ጨዋታው ከነበረው ውጥረት አንፃር የዕለቱ ዋና ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴና ረዳቶቻቸው ጨዋታውን በጥሩ ብቃት መርተውታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *