የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 2-0 ስሑል ሽረ

በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የተከናወነው የባህር ዳር ከተማ እና የስሑል ሽረ ጨዋታ በባለሜዳዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች 2ለ0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን ብለዋል።

“በሁለተኛው አጋማሽ ያደረግናቸው ቅያሪዎች ውጤት ይዘን እንድንወጣ አድርጎናል።” ጳውሎስ ጌታቸው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ

“ጨዋታውን መጨረስ የነበረብን በመጀመሪያ አጋማሽ ነበር። ነገር ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻልንም። እንደተመለከታችሁት ተጋጣሚያችን ግብ ክልል ቶሎ ቶሎ እንደርስ ነበር። ነገር ግን ጨዋታውን ቶሎ መጨረስ አልቻልንም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ቅያሪዎችን አድርገን ውጤት ይዘን ወጥተናል። በዚህም ደግሞ ደስተኛ ነኝ።”

በሁለተኛው አጋማሽ ስላደረጉት ቅያሪ

“በሁለተኛው አጋማሽ ያደረኩዋቸው የተጨዋች እና የፎርሜሽን ቅያሪዎች በጣም የተሳኩ ነበሩ። ተቀይረው የገቡት ተጨዋቾች በሙሉ የአጥቂ ባህሪ የነበራቸው ተጨዋቾች ናቸው። በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሶስት ተከላካይ ነበር ስንጫወት የነበረው። ይህ ደግሞ የሆነው ግብ ለማስቆጠር ካለን ፍላጎት የተነሳ ነው እንጂ በቋሚነት የተሰለፉት ተጨዋቾች ከአቅም በታች ተጫውተው አይደለም የቀየርናቸው።”

በተከታታይ አስመዝግበውት ስለነበረው የአቻ ውጤት እና ስለቀጣይ የቡድኑ እቅድ

“ከሜዳችን ውጪ ያደረግናቸው የወላይታ ዲቻ እና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ ላይ የተመዘገበው የአቻ ውጤት አይገባንም፤ ማሸነፍ ነበረብን። የዛሬው ድል በተለይ በቀጣይ በሜዳችን ከአዳማ ከተማ ጋር እንዲሁም ከሜዳችን ውጪ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ለምናደርገው ጨዋታ መነቃቃት ይፈጥርልናል። እቅዳችን አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ መቆየት ነው። ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች አሉብን እነሱን አሸንፈን ወደ ዋንጫ ፉክክሩ እንመለሳለን።”

“በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሰራናቸው ስህተቶች ተሸንፈናል፣ ውጤቱንም በፀጋ እንቀበላለን።” ገብረኪሮስ አማረ – ስሑል ሽረ

ስለ ጨዋታው

“የዛሬው ጨዋታ ለሁለታችንም በጣም ያስፈልገን ነበር። ምክንያቱም ባህር ዳሮች ከአቻ ውጤት ነው የመጡት እኛም ደግሞ ከሽንፈት ነው የመጣነው ስለዚህ ጨዋታው ማሸነፍ ያስፈልገን ነበር። በጨዋታው ግን በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሰራናቸው ስህተቶች ሁለት ጎሎች ተቆጥሮብን ተሸንፈን ወጥተናል። ከጎሉ ጎን ለጎን ግን በመጨረሻዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች የተፈጠረው ነገር ግን የሚደገፍ አይደለም። ይህ ተግባር የሙሉ የባህር ዳር ከተማን ህዝብ እና የጨዋውን የባህር ዳር ከተማ ቡድን ደጋፊ የሚወክል እንዳልሆነ እና የአንድ ሰው ስራ እንደሆነ እናውቃለን።”

ወደ ሜዳ ይዘውት ስለገቡት እቅድ

“ወደ ሜዳ የገባነው ለማሸነፍ ነው። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ይዘነው የገባነው ፎርሜሽን ለማጥቃት የሚመች ነበር። ነገር ግን ተጨዋቾቼ ከጨዋታው በፊት አስበነው የነበረውን ነገር ሜዳ ላይ አልተገበሩትም።”

ስለቡድኑ ቀጣይ እጣ ፈንታ

“ቡድናችንን እንደ አዲስ ለማሻሻል (Reform) አስበናል። አሁን አንድ ጨዋታ ነው የሚቀረን እሱንም ለማሸነፍ እንገባለን። በቀጣይ ዙር ግን ተሻሽለን ቡድናችንን ወደ ጥሩ ደረጃ ለማምጣት እንሞክራልን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *