ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከነገ ጨዋታዎች መካከል በዛሬ ቅድመ ዳሰሳችን የምንመለከተው ጨዋታ ድቻ እና ጊዮርጊስ የሚገናኙበትን ይሆናል።

ከአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ጋር የተለያየው ወላይታ ድቻ ነገ በሶዶ ስታድየም 09፡00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናግዳል። አዲስ አባባ ላይ በተስተካካይ ጨዋታ በሲዳማ ቡና የተረታው ወላይታ ድቻ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የመጀመሪያውን ዙር በወራጅ ቀጠና ውስጥ ላለመጨረስም ወሳኝ በሆነው በዚህ ጨዋታ የዋና አሰልጣኙን ስንብት ተከትሎ በምክትል አሰልጣኙ ደለለኝ ደቻሳ እየተመራ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። አምስት ድሎችን በመደዳ አስመዝግቦ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ የጀመረውን ግስጋሴ ጋብ የሚያደርጉ ሁለት የአቻ ውጤቶች ገጥመውታል። ተስተካካይ ጨዋታዎቹን በመጨረሱም በተከታዮቹ መቐለ እና ሲዳማ መሪነቱን ላለመነጠቅ ማድረግ የሚችለው ነገር ከሶዶ በድል ተመልሶ የነሱን ጨዋታዎች መጠበቅ ብቻ ይሆናል።

ወላይታ ድቻ የበረከት ወልዴን አገልግሎት ከ5 ቢጫ ካርድ ቅጣት በኋላ የሚያገኝ ሲሆን ፍፁም ተፈሪ ፣ አንዱዓለም ንጉሴ ፣ እዮብ አለማየሁ ፣ ውብሸት ክፍሌ እና ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ግን ከጉዳታቸው አላገገሙም። አብዱልከሪም መሀመድ ከጉዳት በተመለሰለት ቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ መሀሪ መና ፣ ሳላዲን በርጌቾ  እና ጌታነህ ከበደ ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን መጠነኛ ጉዳት ያለባቸው ምንተስኖት አዳነ እና አቡበከር ሳኒ ግን ከቡድኑ ጋር ተጉዘዋል። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ እስካሁን 10 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ግማሹን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ወላይታ ድቻ የአምናውን ድሉን ጨምሮ ሁለት ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ፈረሰኞቹ 17 ሲያስቆጥሩ የጦና ንቦቹ ደግሞ 6 ግቦች አሏቸው።

– በወላይታ ድቻ ሜዳ በተደረጉ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ሦስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሁለቱም አንድ አንድ ጊዜ ድል አድርገዋል።

– ወላይታ ድቻ በአዲስ አበባ ስታድየም ከሲዳማ ያደረገውን ጨዋታ ሳይጨምር ሽንፈት ባላስተናገደበት የሶዶ ስታድየም አምስት ጨዋታዎችን ሲያከናውን ሁለቱን በማሸነፍ ቢጀምርም ከመጨረሻዎቹ ሦስት ተጋጣሚዎቹ ጋር 1-1 ነበር የተለያየው።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ ስድስት ጨዋታዎችን ሲያደርግ ሦስት የ1-0 ድሎች አስመዝግቦ ሁለት ጊዜ ደግሞ ያለግብ በተጠናቀቁ ጨዋታዎች ሲመለስ አንድ ሽንፈት አስተናግዷል።                 

ዳኛ

– እስካሁን ከመራቸው ሦስት ጨዋታዎች መካከል በሁለቱ እነዚህን ተጋጣሚዎች የመዳኘት አጋጣሚ የነበረው ዮናስ ካሳሁን እርስ በርስ የሚገናኙበትን ይህን ጨዋታዎች ይመራል። ዮናስ በሦስቱ ጨዋታዎች ዘጠኝ የማስጠንቂያ ካርዶችን መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)

መኳንንት አሸናፊ

እሸቱ መና – ተክሉ ታፈሰ – ውብሸት ዓለማየሁ –  ኄኖክ አርፌጮ

በረከት ወልዴ – ኃይማኖት ወርቁ

ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ  – ሳምሶን ቆልቻ

ባዬ ገዛኸኝ          

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)

ፓትሪክ ማታሲ

አስቻለው ታመነ  – ፍሬዘር ካሳ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ 

በኃይሉ አሰፋ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ – ኄኖክ አዱኛ

ታደለ መንገሻ

ሳላሀዲን ሰዒድ – አቤል ያለው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *