ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደቡብ ፖሊስ ከ ጅማ አባ ጅፋር

የደቡብ ፖሊስ እና አባ ጅፋር ጨዋታን የተመለከቱ ጉዳዮችን በቅድመ ዳሰሳችን እናስቃኛችኋለን።

ደቡብ ፖሊስ በሀዋሳው ሰው ሰራሽ ሜዳ 09፡00 ላይ ጅማ አባ ጅፋርን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ከዛሬ የሊጉ መርሐ ግብር ውስጥ አንዱ ነው። ደቡብ ፖሊስ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ከሾመ በኋላ ነው በውድድር ዓመቱን አጋማሽ የመጨረሻ ጨዋታው ከቻምፒዮኖቹ ጋር የሚገናኘው። ቡድኑ አሁንም 15ኛ  ደረጃ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም ከሜዳው ውጪ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ያስመዘገበው ያልተጠበቀ ድል ትልቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥርለት ይታመናል። የዛሬው ጨዋታም ከአደጋው ዞን የሚያወጣው ባይሆን እንኳን ከበላዩ ወዳሉ ክለቦች ለመቅረብ የሚያስችለው በመሆኑ በሁለተኛው ዙር  ለሚጠብቀው ላለመውረድ የሚደረግ ፍልሚያ የሚጨምርለት ነገር ይኖራል።

ባሳለፍነው ሳምንት ከተደረጉ ተስተካካይ ጨዋታዎች መካከል ሜዳው ላይ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ አስገራሚ በነበረ 3-3 ውጤት ጨዋታውን የፈፀመው ጅማ አባ ጅፋር የሊጉን ወገብ ለመሻገር ጊዜ የፈጀበት ይመስላል። በሜዳው ባደረጋቸው ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ባለመቻሉም ከተስተካካይ ጨዋታዎች በሚያገኛቸው ነጥቦች ሊጉን የመምራት ዕድሉን እየቀነሰው ይገኛል። የአምናው ቻምፒዮን አባ ጅፋር ዛሬ ከደቡብ ፖሊስ ሙሉ ነጥብ ቢያገኝ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ይሆናል። 

                                                   
ደቡብ ፖሊስ ከጉዳት መልስ የመስመር አጥቂው ብሩክ ኤልያስን ግልጋሎት እንደሚያገኝ ሲጠበቅ ብርሀኑ በቀለ እና መስፍን ኪዳኔ ግን አሁንም ባለማገገማቸው ጨዋታው ያልፋቸዋል። በጅማ በኩል ደግሞ ፍቃድ ላይ የሚገኘው ዳንኤል አጄዬን ጨምሮ ከድር ኸይረዲን ፣ ይሁን እንደሻው እና ዐወት ገብረሙካኤል በጉዳት ወደ ሀዋሳ አልተጓዙም። ባለፉት አራት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ያስቆጠረው ማማዱ ሲዲቤ ምርጥ አቋም ላይ መገኘት ግን ሳይነሳ የማይታለፍ ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ደቡብ ፖሊስ አራተኛ እንዲሁም ጅማ አባ ጅፋር ሁለተኛ የፕሪምየር ሊግ የውድድር ዓመታቸውን ተሳትፎ እያደረጉ ቢገኝም እርስ በርስ ሲገናኙ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።

– ደቡብ ፖሊስ ሀዋሳ ላይ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች በስድስቱ ግብ እያስቆጠረ ቢወጣም ድል የቀናው ግን በአንዱ ብቻ ሲሆን ሰባት ጊዜ ሽንፈትን አስተናግዷል።

–  ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን ከሜዳው ውጪ ስድስት ጨዋታዎችን ሲያደርግ በሁለቱ ሽንፈት በሁለቱ ደግሞ የአቻ ውጤቶች ሲገጥሙት በመጀመሪያው እና በመጨረሻው ጨዋታዎቹ ግን በድል መመለስ ችሏል።

ዳኛ

– ኃይለየሱስ ባዘዘው ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷታል። አርቢትሩ በዳኘባቸው አራት ጨዋታዎች ሰባት የማስጠንቀቂያ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ የጅማ አባ ጅፋር ጨዋታዎች ነበሩ።

                    
ግምታዊ አሰላለፍ

ደቡብ ፖሊስ (4-4-2)

ሀብቴ ከድር

ዘሪሀን አንሼቦ – ደስታ ጊቻሞ  – አዳሙ መሀመድ – አናጋው ባደግ

 በረከት ይስሀቅ – ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – የተሻ ግዛው

 በኃይሉ ወገኔ – ኄኖክ አየለ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)                       

ሚኪያስ ጌቱ

ተስፋዬ መላኩ – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ                                                     

                               
ኤልያስ ማሞ – አክሊሉ ዋለልኝ – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *