አሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 3-0 ስሑል ሽረ

በጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታዲየም የተከናወነው የፋሲል ከነማ እና የስሑል ሽረ ጨዋታ በባለሜዳዎቹ ፋሲል ከተማዎች 3ለ0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን ብለዋል።

“የመጨረሻው ግብ የገባበት መንገድ ከመጀመሪያውቹ ግቦች በላይ ያስደስተኛል” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታዉ ጥሩ ነበር። እኛ 3 ነጥብ ካገኝን ቆየን። በሜዳችንም ከሜዳችን ውጭም ተከታታይ ጨዋታዎችን አቻ ነው የወጣነው። የመቐለን ጨዋታ ደግሞ ተሸንፈን ነው የመጣነው። በየጨዋታው ጥሩ ብንሆንም 3 ነጥቦችን ማግኘት አልቻልንም ነበር። ዛሬ ጥሩ ተጫውተን ወደ አሸናፊነት መመለስ ችለናል።

በሦስት ተከላካዮች ስለመጫወት

ከሌሎች ጨዋታዎች በተሻለ ዛሬ በተደጋጋሚ እድሎችን አግኝተናል። ከአሰላለፉም በላይ የመጨረሻው የማጥቃት እንቅስቃሴ መስመር ላይ ስንደርስ ትንሽ መረጋጋት ይጎድለናል። በዛሬዉ ጨዋታ ላይ ራሱ በመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ኢዙ ለኤፍሬም የሰጠዉ ኳስ የሚያሳየዉ የመረጋጋት ክፍተቶች እንዳሉብን ነበር። እንዳያችሁት 3-4-3 አሰላለፍ የሚረዳ ነገር ይኖራል። ስለዚህ ይበልጥ አጥቅተን መጫወታቸውን ጠቅሞናል። አሰላለፍ ብቻ ትርጉም የለውም፤ ዋናው ነገር የተጫዋቾቹ ትግበራ ነው። ከሱራፌል ግቦች ውጪ እንዳያችሁት ተደጋጋሚ ኳሶችን መፍጠር ችለናል። አሁንም በዛ ቦታ ላይ ያለብንን ክፍተት ማስተካከል እንዳለብን አምናሁ። የመጨረሻው ግብ የገባበት መንገድ ከመጀመሪያዎቹ ግቦች በላይ ያስደስተኛል። እንደዛ አይነት አጋጣሚዎች እየፈጠርን የምንስተውን ማስተካከል አለብን። የሱራፌል ግቦች ለኔ ቦነስ ነው። ተጫውተን የሄድነው ቢሆንም ከውጪ እየመታህ ማግባት ላይሳካልህ ይችላል። አስተማማኝ በሆነ መንገድ ማሸነፍ ካለብን የመጨረሻው የማጥቃት ክፍል ላይ ያለብንን ያለመረጋጋት መቅረፍ አለብን ብዬ አምናለሁ።

የስብስብ ጥራት

በየቦታዉ ተፎካካሪ ናቸው። በተጫዋቾች መካከል ጥሩ ፉክክር ነው ያለው። ይሄ ደግሞ ልምምድ ላይም ሜዳ ላይም የሚታይ ነገር ነው። እናም ለቀጣይ ጨዋታ ማንን እጠቀማለሁ ብለህ እንዳትጨነቅ ያደርግሀል። ከጉዳት ነፃ ከሆነ ደግሞ በጣም ጥሩ ነው። በአጥቂ ደረጃ ለሚነሳ ነገር አለ። እኔም ቢሆን የማየዉ ክፍተት አለ። ግን ያም ቢሆን የመጨረሻ ኳሶች ላይ አለመረጋጋታችን ብዬ ነው ማምነዉ ክፍተቱ። ለምሳሌ ኢዙ ያገባዉ ኳስ ትክክለኛ ጨራሽ እንደሆነ ያስታዉቃል። ግን ትክክል ያልነበረዉ የምንመጣበት ኳስ ነው ብየ ነው የማስበው። በየ ቦታው ግን አማራጭ ልጆች መኖራቸዉ ቡድኑ በጥንካሬ እንዲቀጥል ያደርገዋል።

”በቀላሉ ነበር ግብ የሚያስቆጥሩብን” ገብረኪሮስ አማረ – ስሑል ሽረ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። እኛም እነሱም ተሸንፈን ነው የተገናኝንው። እና ሁለታችንም 3 ነጥቡን እንፈልገዋለን። ቢሆንም ግን ይሄን ሦስት ነጥብ ፋሲሎች መውሰድ ችለዋል። የኛ ችግር የነበረው የግብ ማግባት ነበር። እኛ በፈጠርናቸዉ አንዳንድ ስህተቶችም ግብ ተቆጥሮብን ልንሸነፍ ችለናል ።

የተከላካዮች ስህተት

ተካላካዮች አልቀየርኩም፤ በባህርዳር ጨዋታ ላይ የነበሩ ናቸው። ፋሲሎች ብልጫ ወስደዉ እኛ ክፍተቶችን እንድንፈጥር አድርገውናል። እናም በእነርሱ ስህተቶች ግብ ተቆጥረዋል እና ይሄ የራሳችን ስህተት ነው። ያገኘነውንም እድል አልተጠቀምንም፤ መከላከልም አልቻልንም። በቀላሉ ነበር ኳስ መትተው ግብ የሚያስቆጥሩት።

ስለ አሰላለፋቸው

አሰላለፋችን 4-2-3-1 ነበር። ይሄ የአጠቃቀም ጉዳይ ነው እንጂ አምስት አማካይ አላደረግንም፤ ለመከላከልም አልገባንም። ሁለታችንም ነጥቡን እንፈልገዋለን። ግን ነፃ ኳስም አግኝተን ነበር ፤ የጭንቀት ኳስ አግኝተን እሱንም አልተጠቀምነውም። እናም ስህተት በመስራታችን ብቻ ዋጋ አስከፍሎናል።

ለሁለተኛው ዙር…

ለሁለተኛው ዙር በጣም ብዙ የሚሰሩ ስራዎች አሉ። እናም በደረጃ ሰንጠረዡ ከእኛ በላይ ያሉ ቡድኖች 15 እና 16 ነጥቦች ላይ ነው ያሉት። እኛ ደግሞ 11 ነጥብ ላይ ነው የመለነው። ስለዚህ ብዙ የተለያየ ነገር ላይ አይደለም ያለነው። ለሁለተኛው ዙር ጥሩ ተፎካካሪ እና ተወዳዳሪዎች በመሆን ከመውረድ ስጋት ነፃ የምንሆንበት ነገር እንሰራለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *