ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከሜዳው ውጪ ከወልዋሎ ነጥብ ተጋርቶ የሊጉ መሪ ሆኗል

ዛሬ ከተካሄዱ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ትግራይ ስታድየም ላይ በወልዋሎ እና ሲዳማ ቡና መካከል የተከናወነው ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ወልዋሎዎች በ14ኛው ሳምንት ስሑል ሽረን ካሸነፈው ቡድናቸው አብዱራህማን ፋሴይኒን በኤፍሬም አሻሞ ሲቀይሩ ሲዳማዎች በበኩላቸው በፍቅሩ ወዴሳ፣ መሐመድ ናስር (ቀይ) እና ዳዊት ተፈራን ምትክ መሳይ አያኖ፣ ተመስገን ገ/ፃዲቅ እና ዳግም ንጉሴ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ወልዋሎዎች ተሽለው በታዩበት፤ ሲዳማዎች በመልሶ ማጥቃት ከመስመር በሚሻሙ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር በሞከሩበት የመጀመርያ አጋማሽ ሳቢ ጨዋታ ሳይታይ ቀርቷል። ወልዋሎዎች በፕሪንስ ሰርቪንሆ፣ አማኑኤል ጎበና እና እንየው ካሳሁን አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለይ እንየው ከቀኝ መስመር ያሻማው ፕሪንስ ሰርቪንሆ መሬት ለመሬት መትቶ ከግቡ ጎን የወጣው የተሻለ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር። ሲዳማዎች በበኩላቸው በሁለቱም መስመር በኩል ለማጥቃት ቢሞኩረም ይህ ነው የሚባል ንፁህ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ወልዋሎዎች የአሸናፊነትን ግብ ለማግኘት፤ ሲዳማዎች አንድ ነጥባቸውን ለማስጠበቅ ከመጀመርያው 45 የተሻለ ፋክክርን አሳይተዋል። ቀኝ መስመር ላይ ትኩረቱን ያደረገው የወልዋሎ ፈጣን የማጥቃት አጨዋወት በሁለተኛው አጋማሽ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሲሆን እንየው ካሳሁን ከቀኝ መስመር ያሻማውን ፕሪንስ በግምባሩ ገጭቶት መሳይ አያኖ የያዘበት እንዲሁም እንየው ካሳሁን ከርቀት ሞክሮት ወደ ውጪ የወጣው የዚህ ማሳያ ናቸው። መከላከል ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉት ሲዳማዎች በሐብታሙ ገዛኸኝ እና ግርማ በቀለ አማካኝነት መከራዎችን ቢያደርጉም ያን ያህል አብዱላዚዝ ኬይታን የሚፈትኑ አልነበሩም።

ሲዳማ ቡና ከዚህ ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘታቸውን ተከትሎ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀራቸው የሰንጠረዡ አናት ላይ መቀመጥ ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *