የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 1-0 ኢትዮጵያ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር መደበኛ የመጨረሻ መርሃግብሮች ዛሬ ሲካሄዱ መከላከያ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ ከውጤት ቀውስ በኃላ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

“በሁለተኛው አጋማሽ እኛ የተሻለ ቅርፅ ይዘን ቀርበናል”- ሥዩም ከበደ (መከላከያ)

ስለ ጨዋታው

“በዛሬው ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ ጥብቅ ነበርን። በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ሜዳውን ተቆጣጥረው በመጫወት ለማግባት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ እኛ የተሻለ ቅርፅ ይዘን ቀርበናል፤ የዛሬውን ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ በማግኘታች ደስ ብሎኛል። በዚህም በተሻለ የራስ መተማመን በቀጣይ ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ላይ የተሻለ ነገር ይዘን የመጀመሪያውን ዙር ለማጠናቀቅ እንሰራለን፡፡”

ወጥ ስላልሆነው የቡድኑ አቋም

“አብዛኛው ነገሮች መበላሸት የጀመረው በሜዳችን በአዳማ ከተሸነፍንበት ጨዋታ አንስቶ ነው። ከዚያ በመቀጠል በነበሩት ጨዋታዎች ላይ የመከላከል አደረጃጀታችን ጥሩ አልነበረም። በተሸነፍንባቸው ጨዋታውች በግብጠባቂ እንዲሁም በተወሰኑ ግለሰባዊ ስህተቶች ነጥብ አጥተናል፡፡ ቡድናችን በማጥቃቱ ረገድ የተሻለ ነው፤ እንዲያውም የሊጉ ከፍተኛ አስቆጣሪ የኛ ተጫዋች ነው፡፡”


“በእንቅስቃሴ ደረጃ በተከታታይ ከተሸነፍንባቸው ጨዋታዎች የተሻለ ነበር”-ገብረኪዳን ነጋሽ(ኢትዮጵያ ቡና)

ስለጨዋታውና የአቡበከር ፍፁም ቅጣት ምት

“ፍፁም ቅጣት ምት ማንም ተጫዋች ሊስት ይችላል። በእንቅስቃሴ ደረጃ በተከታታይ ከተሸነፍንባቸው ጨዋታዎች የተሻለ ነበር ፤ ፍፁም ቅጣት ምት ስለሳትን ብቻ ተሸንፈናል ማለት አይቻልም። ፍፁም ቅጣት ምቱም ገብቶ ልንሸነፍበት የምንችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችል ነበር፡፡ እኛ በዛሬው ጨዋታ ተጫዋቾቻችንን ሊያግዝ የሚችል ተጨማሪ ሰው እንደሚያስፈልገን ተረድተናል፡፡”

ስለአጥቂ መስመር ችግር

“አሁን ባለው ሁኔታ ምንም ማድረግ አልቻልንም። በአጥቂ ስፍራ ላይ በቅርቡ ከውጪ ያስፈረምነው ተጫዋች አለ፤ በሁለተኛው ዙር እሱን ለመጠቀም አቅደናል። በተጨማሪም በመሀል ክፍሉ እንዲሁም በተከላካይ ስፍራ ላይ የተሻሉ ተጫዋቾች የምናገኝ ከሆነ ለመጨመር እንጥራለን፡፡ ቡድናችን በጉዳት የተነሳ በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኗል። በተጨማሪም ቡድናችን ልምድ ያለው ተጫዋች የለውም። በአብዛኛው እንደምታይዋቸው ልምድ የሌላቸው ወጣት ተጫዋቾች ናቸው። በዚህም ከልምድ ማነስ አንድ ግብ ስናስተናግድ የመረበሽ ሁኔታ አለ። ለዚህም በሁለተኛው ዙር ሊያግዙ የሚችሉ ተጫዋቾችን እያፈላለግን እንገኛለን። ከተስፋ ቡድንም ቢሆን ተጫዋቾችን ጨማምረን የተሻለ ነገር ለመስራት እንሞክራለን፡፡”

ስለዋንጫ ፉክክር

“አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ እንገኛለን። ከመሪዎቹ ጋር ያለን ልዩነት በጣም የሰፋ አይደለም። ከስምንት ነጥብ ያነሰ ነው ፤ በአጠቃላይ ይህን ያህል ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር የለውም፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *