ሪፖርት | መከላከያ የዓመቱን የመጀመሪያ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

ከ15ኛው ሳምንት ጨዋታዎች መካከል በመጨረሻ የተካሄደው የመከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በፍቃዱ ዓለሙ ብቸኛ ግብ ጦሩን የበላይ በማድረግ ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጀመር በፊት ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና በደቡብ ፖሊስ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሽንፈት ካስተናገደ በኃላ በተወሰኑ የክለቡ ደጋፊዎች ከፍተኛ ዘለፋን በማስተናገዳቸው ከቦርድ ሰብሳቢነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ወስነው የነበሩት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እና ሌላኛው የክለቡ የቦርድ አባል አቶ ይስማሸዋ ስዩም በትላንትናው ዕለት ውሳኔያቸውን በማጤን እስከቀጣዩ የውድድር ዘመን ድረስ ከክለቡ ጋር ለመቆየት መወሰናቸውን በማስመልከት የክለቡ የደጋፊዎች ማህበር “ባለውለታዎቻችንን እናከብራለን” የሚል ባነር በማሰራት እንዲሁም አበባ በማበርከት ለተፈጠረው ድርጊት ይቅርታ ጠይቋል፡፡

በአራተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ደደቢትን 3-0 በመርታት የተመለሰው መከላከያ የግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ሙሉቀን ደሳለኝን በዓለምነህ ግርማ የተካበትን ብቸኛ ለውጥ አድርጓል። በኢትዮጵያ ቡና የዛሬው ቡድን ውስጥ ደግሞ ከ14ኛው ሳምንት የደቡብ ፖሊስ ሽንፈት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ተደርጓል። በዚህም ጉዳት ላይ የሚገኘው ሳምሶን ጥላሁን ፣ የኋላሸት ፍቃዱ እና ሱለይማን ሎክዋ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በተመለሰው አስራት ቱንጆ ፣ አልሀሰን ካሉሻ እና ቃልኪዳን ዘላለም ተተክተዋል።

በመከላከያ የኳስ ቁጥጥር ወደ ኢትዮጵያ ቡና አጋማሽ አድልቶ የጀመረው ጨዋታ በቅድሚያ በታየበት መነቃቃት የቀጠለ አልነበረም ። መከላከያዎችም በነዚህ ደቂቃዎች ካገኙት የበላይነት 2ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከሳጥን ውጪ ካደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ ሌላ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ቀስ በቀስ ጫናውን ከራሳቸው ሜዳ ማስወጣት የችሉት ኢትዮጵያ ቡናዎችም ቢሆኑ ቅብብሎቻቸው ከመሀል ሜዳ እምብዛም ሲያልፉ አይታዩም ነበር። በመሆኑም ተመሳሳይ የዳይመንድ ቅርፅ በነበራቸው የቡድኖቹ አማካይ ክፍሎች ላይ በተደጋጋሚ የሚቋረጡ ቅብብሎች እና የመሀል ሜዳ ጉሽሚያዎች የአጋማሹን በርካታ ደቂቃዎች ወስደው ታይተዋል።

ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመሀል ወደ አቡበከር ናስር በሚላኩ ኳሶች የግብ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ታይቷል። 5ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ መንገድ አቡበከር ከካሉሻ አልሀሰን በተላከ ኳስ ከይድነቃቸው ኪዳኔ ጋር ተገናኝቶ ጥፋት የተሰራበት በመሆኑም ኢትዮጵያ ቡና የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኘም ራሱ አቡበከር መትቶ ይድነቃቸው ሊያድንበት ችሏል። ፍፁም ቅጣት ምቱ አቡበከር ዘንድሮ ካስቆጠራቸው አራት የፍፁም ቅጣት ምቶች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመከነው ነበር። የቡና ቀጣዩ ሙከራ የታየው 19ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ኃይሌ ገብረትንሳይ ለቃልኪዳን ዘላለም ያደረሰውን ኳስ በበርካታ አጋጣሚዎች ከኳስ ጋር ሲገናኝ መረጋጋት ሲሳነው የታየው ወጣቱ አጥቂ ወደ ውጪ ሰዶታል።

በ28ኛው ደቂቃ ዳዊት ማሞ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጪ እምብዛም ጫና ያልፈጠሩት መከላከያዎች እጅግ አጥብቦ የሚጫወተው የአማካይ ክፍላቸው ቅብብሎች ወደ አጥቂዎቻቸው ደርሰው ወደ መልካም አጋጣሚነት መቀየር አልቻሉም። ተመስገን ገብረኪዳን ወደ ግራ መስመር በመውጣት አልፎ አልፎ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በስረቀርም ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ ፊት ላይ አስፈሪነቱ ድካማ ነበር። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ካሉሻ ከተጋጣሚ የግብ ክልል ርቆ ቢንቀሳቀስም ዛሬ የተሻለ በሚባል መልኩ ተጫዋቾችን ቀንሶ ኳሶችን ወደ ፊት በማድረስ በመጀመሪያው አጋማሽ ጎልቶ መውጣት ችሎ ነበር። 36ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘው እና ኃይሌ በቀጥታ መቶት በግቡ አግዳሚ የተመለውም ቅጣት ምትም ካሉሻ ካስጀመረው ጥቃት የተሞከረ ነበር። 40ኛው ደቂቃ ላይ ቡናዎች በከፈቱት ሌላ ድንገተኛ ጥቃት ሳጥን ውስጥ በብዛት በመገኘት በካሉሻ ፣ ኃይሌ እና አቡበከር ያደረጓቸው ተከታታይ ሙከራዎች መከላከያዎች እንደምንም ማውጣት ችለዋል።

የተሻሉ የግብ ሙከራዎች የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ኢትዮጵያ ቡናዎች በተሻለ መልኩ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል የመቅረብ ዕድል ነበራቸው። 48ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ረሺድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ የነበረው አቡበከር በማብረድ ሞክሮት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ቡድኑ የፈጠረው ጥሩ የግብ አጋጣሚ ነበር። ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ለመግባት ጊዜ በፈጀባቸው መከላከያዎች በኩልም ተመስገን 54ኛው ደቂቃ ላይ ያደረገው የርቀት ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ምንይሉ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በዋቴንጋ ኢስማ ከተመለሰ በኋላ ዳዊት ማሞ እና ፍሬው ሰለሞን ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል።

63ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያዎች ተመስገንን በፍቃዱ ዓለሙ የተኩበት ቅያሪ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ፍሬ አፍርቷል። በሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታው ላይ የነበረው ተፅዕኖ ክፍ ያለው ዳዊት እስጢፋኖስ ባሳለፈለት ኳስ የመጀመሪያውን ንክኪ ያደረገው ፍቃዱ በግራ የሳጥኑ ክፍል ከገባ በኋላ በጥሩ አጨራረስ የጨዋታውን ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። መመራታቸው ከፈጠረባቸው ጫና በተነሳ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች በተለይም ከኳስ ውጪ የነበራቸው የመንጠቅ ጉጉት ለመከላከያ የአማካይ ክፍል ተጨዋቾች ቅብብሎችን ለመከወን የተመቸ ሆኖ ታይቷል። በተለይም 82ኛው ደቂቃ ላይ የሁለቱ ዳዊቶች ጥምረት ሳጥን ውስጥ ለምንይሉ የፈጠረው ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ተጠቃሽ ሲሆን ተቀዛቅዞ የዋለው የምንይሉ ሙከራ ግን ወደ ላይ የተነሳ ነበር።

አስራት ቱንጆ በቃልኪዳን ተቀይሮ የገባው ሱለይማን ሎክዋ 80ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ካሻማው ኳስ ከሳጥን ውስጥ እንዲሁም 84ኛው ደቂቃ ላይ በግል ጥረቱ ከሳጥን ውጪ ባደረጋቸው ሙከራዎች የጦሩን የኋላ ክፍል መፈተን የቻሉት ቡናዎች 86ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ለመሆን በእጅጉ ተቃርበው ነበር። ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ የተጣለውን ኳስ ይድነቃቸው በአግባቡ ሳያወጣው ቀርቶ ወንድይፍራው ጌታሁን ወደ ግብ ቢልከውም ምንተስኖት ከበደ ከመስመር ላይ በማውጣት ቡድኑን ታድጓል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ሌላ አስደንጋጭ ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው በመከላከያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎም ተከታታይ ድል ማሳካት የቻለው እና ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት መከላከያ ሦስት ደረጃዎችን በማሻሻል ወደ 10ኛነት ከፍ ሲል የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎቹን ያገባደደው ኢትዮጵያ ቡና በሰንጠረዡ አጋማሽ ለመቀመጥ ተገዷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *