የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 0-0 ድሬዳዋ ከተማ

በሦስተኛው ሳምንት መካሄድ ኖሮባቸው በይደር ተይዘው ከቆዩ ጨዋታዎች መካከል የሆነው የመከላከያ እና ድሬዳዋ ከተማ ተሰተካካይ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድየም ተካሂዶ ያለምንም ግብ ከተጠናቀቀ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ይህንን ብለዋል።

” ጨዋታው ማግኘት የሚገባንን ነጥብ በራሳችን ስህተት ያጣንበት ነበር ” አሰልጣኝ ስዩም ከበደ – መከላከያ

ቡድኑ ከነበረው ብልጫ አንፃር ጨዋታው ሲታይ…

” በአጠቃላይ ጨዋታው እንዳሰብነው አልነበረም። በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ነገር መጨረስ እንችል ነበር። ቢያንስ 3-0 መምራት የምንችልበት ዕድል ፈጥረን ነበር። መሳት የማይገባቸው ኳሶች ባክነዋል ፤ የዛሬው በሽታ ደግሞ አጨራረስ ላይ ነበር። 500 ፐርሰንት ሊገቡ የሚችሉ ኳሶች ነው ያመከነው። እንዛ ኳሶች ገብተው ቢሆን ኖሮ በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ እንነቃቃ ነበር። በመሆኑም በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ሀሳባችንን ማጥቃት ላይ አድርገን ከኋላ ክፍተት እንዳንተው ስጋትም ነበረብን። አጠቃላይ ጨዋታው ማግኘት የሚገባንን ነጥብ በራሳችን ስህተት ያጣንበት ነበር። ”

ቡድኑ ከፈጠረው ጫና አንፃር በመጨረሻ ደቂቃዎች ግብ ለማስገኘት ጥድፊያ ስላለማሳየቱ…

” ምንይሉን እንዲሁም ፍፁምን በረጃጅም ኳሶች ለማግኘት ሞክረን ነበር ያ ደግሞ ውጤታማ አልሆነም። ስለሆነም አንድ ጎል ለኛ ዋሳኝነት ያለው በመሆኑም ቀስ ብለን ሳንቻኮል ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረን ነበር። ነገር ግን በግራም በቀኝም ያሰብነው ታክቲካል ዕቅድ ሳይሳካልን ቀርቷል። ነጥብ መጋራቱ ግን የሚገባን አልነበረም። ”

ለሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታ ግብ አለማስተናገዱ የመከላከል ችግሩን መቅረፉን የሚያሳይ ስለመሆኑ…

” ከመቐለው ጨዋታ መልስ በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር የመከላከል ሂደታችን ላይ ብዙ ሰርተናል። በተሰላፊዎችም በተጠባባቂዎችም በኩል ብዙ ዕርምቶችን ለማድረግ ሞክረናል። ለውጥም አይቼበታለው። ነገር ግን ዛሬ ደሞ በተቃራኒው ለማጥቃት በነበረው ጥረት ውስጥ የነበረው መጣደፍ እና ችኮላ ለግብ የምናደርገውን ውሳኔ የሰከነ እንዳይሆን አድርጎታል። ይህም ዋጋ አስከፍሎናል። ”

” በእንቅስቃሴ ጥሩ ባንሆንም ከሽንፈት መጥተን አንድ ነጥብ ማግኘታችን ለኛ ትልቅ ነገር ነው ብዬ አስባለው። ” አሰልጣኝ ስምዖን አባይ – ድሬዳዋ ከተማ

በመቐለውን ጨዋታ ቡድናቸው ያሳየውን እንቅስቃሴ ‘ከእስከዛሬው የወረደ’ ከማለታቸው አንፃር የዛሬውን ሲመዝኑት…

” እንግዲህ በእንቅስቃሴው ምንም የተለየ ነገር አላየሁም። በጨዋታ ብልጫ ተወስዶብናል። ሆኖም ግን ካለን ስብስብ አንፃር ከፍተኛ ድካም ይታያል። በጥቂት ቀናት ውስጥ ብዙ ጨዋታ እየተጫወትን ነው። ከዛ አንፃር ሳየው በውጤቱ ደስተኛ ነኝ ፤ ተጋድለው ነው ያመጡት። ነገር ግን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ብልጫ ተወስዶብናል ፤ የግብ ሙከራም አድርገዋል። በመልሶ ማጥቃት ትንሽ ጥረት ብናደርግም አልተሳካም። ያም ቢሆን በእንቅስቃሴ ጥሩ ባንሆንም ከሽንፈት መጥተን አንድ ነጥብ ማግኘታችን ለኛ ትልቅ ነገር ነው ብዬ አስባለው። ”

ስለረመዳን ናስር እና ሚኪያስ ግርማ መመለስ እንዲሁም ስለገናናው ረጋሳ የሚና ለውጥ…

” ሚኪያስ ከተመለሰ በኋላ ትናንት ታሞ ነበር። ሆስፒታልም ሄዶ ጉሉኮስም ተደርጎለት ነበር። ከዛ ህመም ተነስቶ ነው ዛሬ የገባው። ብዙ ውይይት አርገን ነው ላሰልፈውም የቻልኩት። በረመዳን በኩል ግን የታየ ነገር ነው ፤ ትንሽ የሚቀሩን ስራዎች አሉ ፤ ከጋብቻ ሥነ ስርዓቱ እንደመመለሱም ዛሬ በአካል ብቃቱም ጥሩ አልነበረም። ገናናውን ብዙ ጊዜ በማንኛውም ቦታ ላይ እንጠቀምበታለን። ዛሬም እየቀያየርን እንዲጫወት አድርገናል ፤ የተሰጠውን ሚና በተገቢው ሁኔታም ተወጥቶታል።

‘ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ስኬታማ ነበር’ ማለት ስለመቻሉ…

” ውጤቱ ሲታይ አንድ ነጥብ ይዘን በመውጣታችን ስኬታማ ነበር ሊባል ይችላል። ነገር ግን እነሱ ያገኙትን ዕድል ያለመጠቀማቸው ድክመት እንጂ ዋጋ ያስከፍለን ነበር። ከዕረፍት በኋላ ግን በተደራጀ ሁኔታ ተከላክለናል ያም ደግሞ ውጤታማ አድርጎናል አንድ ነጥብ ይዘን እንድንወጣ አስችሎናል። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *