ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከጨዋታ ብልጫ ጋር ድሬዳዋን በማሸነፍ አንደኛውን ዙር 2ኛ ደረጃ በመያዝ ፈፀመ

በ13ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ዛሬ በአንጋፋው የድሬደዋ ስታድየም ተካሂዶ ሲዳማ ቡና ከፍፁም የጨዋታ የበላይነት ጋር 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን በድል አጋምሷል።

ድሬዳዋ ከተማ በተስተካካይ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከመከላከያ ያለ ግብ ነጥብ ተጋርቶ ከተመለሰው ቡድኑ ውስጥ በጉዳት ሚኪያስ መኮንንን ተክቶ አማረ በቀለ ሲገባ ራምኬል ሎክ በዳኛቸው በቀለ በመቀየር አስገብተዋል። በሲዳማ ቡና በኩል በ15ኛው ሳምንት ወደ መቐለ ከተማ አቅንተው ከወልዋሎ ጋር ያለ ግብ ነጥብ ተጋርተው ከተመለሰው ስብስባቸው የተደረገው ለውጥ ተከላካዮቹ ግሩም አሰፋ እና ዳግም ንጉሴን በማሳረፍ በዮናታን ፍስሃ እና ግርማ በቀለን ወደ ኋላ በመሳብ ሲጠቀሙ በአጥቂው ተመስገን ገብረፃድቅ ምትክ ጫላ ተሺታን በመጠቀም ጨዋታውን ጀምረዋል።

ከወትሮው እጅግ ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ ተመልካች በታደመበት፣ በዚህ ወቅት ባልተለመደ ሁኔታ ድሬ ላይ መጠነኛ ዝናብ እስከ ጨዋታው ፍፃሜ በጣለበት እና ቀዝቀዝ ባለ አየር የጀመረው ጨዋታ በእንቅስቃሴ ሞቅ ብሎ ተጠናቋል። ድሬዎች ባልተረጋጋ ሁኔታ አጀማመራቸው አስከፊ ቢመስልም የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ቤሄደ ቁጥር ወደ መረጋጋት ገብተው በአንድ አጋጣሚ ከግራ መስመር ረመዳን ናስር ያሻገረውን ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል ተሸራቶ ጎል ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ቀርቷል።

ሲዳማ ቡናዎች የጨዋታውን ሚዛን ወደ ራሳቸው በማድረግ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ስኬታማ መሆን የጀመሩ ሲሆን አማካዮቹ ዳዊት ተፈራ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ እና ወንድሜነህ ዓይናለም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መሐል ሜዳው ላይ ብልጫ እንዲወስዱ አድርጓቸዋል። ይህን የሚያደርጉት አጨዋወት ያስደሰታቸው በስታዲየሙ የታደሙት የድሬዳዋ ደጋፊዎችን ሳይቀር አድናቆታቸውን ሲቸሯቸው አይተናል። ወንድሜነህ ዓይናለም ከቀኝ መስመር በአንድ ሁለት ቅብብል በድሬደዋ የቀኝ መስመር ሳጥን ውስጥ በመግባት አክርሮ የመታውን በረከት ሳሙኤል ተንሸራቶ ለማውጣት ሲሞክር ወደ ጎልነት ተቀይሮ እንግዶቹ ሲዳማ ቡናዎች ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በመያዝ ፍጥነት ባላቸው የመስመር አጥቂዎቹ አዲስ ግደይ እና ጫላ ተሺታ አማካኝነት ወደ ጎል የሚደርሱት ሲዳማ ቡናዎች በ11ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ በፍጥነት ሾልኮ በመውጣት ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁንን በማለፍ አገባው ሲባል የግብ ክልሉ ላይ በርከት ያሉ ተከላካዮች በመኖራቸው ኳሱን ወደ ኋላ በመመለስ ለዳዊት ተፈራ ቢሰጠውም ኳሱን ወደ ላይ የሰደዳት ተጠቃሽ ሙወራ ነበረች። በቀጣይ ደቂቃዎችም በመሐልም ሆነ በመስመር በኩል ለድሬዳዋዎች ለመቆጣጠር አዳጋች ሆነው የዋሉ ሲሆን ተጨማሪ ጎል አያስቆጥሩ እንጂ የተሻለ የግብ እድል በመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ተመልክተናል። 29ኛው ደቂቃ ጫላ ተሺታ ከቀኝ መስመር ወደ ጎል የመታውን ግብጠባቂው ፍሬው ጌታሁን እንደምንም ወደ ውጭ ያወጣበት አንዱ ማሳያ ነው ።

ጨዋታው በተለያዩ ምክንያቶች ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሲቋረጥ ሰብሰብ ብለው ይመካከሩ የነበሩት ድሬዎች የተሻለ የግብ ዕድል መፍጠር የቻሉት ዘግይተው ነበር። 26ኛው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ዳኛቸው በቀለ አጥብቆ ባለመምታቱ ግብጠባቂው መሳይ አያኖ በቀላሉ የያዘበት፣ 36ኛው ደቂቃ ከዳኛቸው በቀለ ሳጥን ውስጥ የተቀበለውን ኳስ አየር ላይ እያለ በአስደናቂ ሁኔታ በመቀስ ምት ሐብታሙ ወልዴ ወደ ጎል መቶት ለጥቂት በግቡ ጠርዝ የወጣው እንዲሁም የሲዳማ ቡና ተከላካዮች በራሳቸው የሜዳ ክፍል በሚያደርጉት ቅብብል የተሰራውን ስህተት ተከትሎ ዳኛቸው በቀለ ነፃ ኳስ አግኝቶ ወደ ፊት በመግፋት ጎል መሆን የሚችል ዕድል ያመከነው ድሬዎች ጎል ለማስቆጠር የተቃረቡባቸው የሚያስቆጭ አጋጣሚዎች ነበሩ። በዚህ ተደጋጋሚ በመከኑ የግብ ዕድሎች የተነሳም በስቴዲየሙ የነበረ ደጋፊ ክፉኛ ሲያበሳጭ ተጫዋቾቹ ላይ የነበረው በራስ መተማመን የበለጠ እንዲወርድ አድርጎታል።

ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል የሚገቡበት ቀሪ አምስት ደቂቃ ጨዋታው በሁለቱም በኩል ወደ ኃይል እንቅስቃሴ አምርቶ በተፈጠረው ጉሽሚያ ፌደራል ዳኛ ኃይሉሱስ ባዘዘው ጨዋታውን ለመቆጣጠር አራት የማስጠንቀቂያ ካርድ እንዲመዙ አስገድዷቸዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በተወሰነ መልኩ ተቀዛቅዘው የገቡ ቢሆንም በ47ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ገዛኸኝ ነፃ ኳስ አግኝቶ ከውሳኔ ችግር በረከት ሳሙኤል ደርሶበት በመንሸራተት ኳሱን አርቆበታል። ከዚህች ሙከራ በኋላ ድሬዎች በፍጥነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ዳኛቸው በቀለ የሚያገኘውን አጋጣሚ ባለመጠቀሙ ምክንያት በራምኬል ተቀይሮ እንዲወጣ ሆኗል። 53ኛው ደቂቃ ዘነበ ከበደ ያቀበለውን ፍሬድ ሙሸንዲ ኳሱን በደረቱ አውርዶ የመታውና ለጥቂት በግቡ አግዳሚ በኩል የወጣበት፣ ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት 54ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ራምኬል በጥሩ ሁኔታ በመምታት የግብ ዕድል ፈጥሮ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ እንደምንም ያዳነበት አጋጣሚ ድሬዎች በከፍተኛ ፍላጎት የአቻነት ጎል ፍለጋ ተነቃቅተው የተጫወቱበት መሆኑን የሚያሳዩ ነበሩ። ይህ ባለበት ሳይጠበቅ በቀኝ መስመር የሜዳ ክፍል ድሬዎችን ሲፈትን የዋለው ወጣቱ አጥቂ ጫላ ተሺታ አምልጦ በመግባት ለአዲስ ግደይ ለማቀበል አስቦ ኳሱ ቢረዝምበትም አዲስ ግደይ በፍጥነት በመድረስ ነፃ አቋቋም ለነበረው ለሐብታሙ ገዛኸኝ አቀብሎት ለሲዳማ ቡናዎች ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ከእረፍት መልስ ድሬዎች በጨዋታው ጅማሬ ተነቃቅተው ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸው ጎል ፍለጋ ተጭነው እየተጫወቱ ባለበት ሁኔታ ሁለተኛ ጎል ቢቆጠርባቸውም በድጋሚ የጎል እድል ለመፍጠር ቀጥለው 68ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ገናናው ረጋሳ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት በተመሳሳይ ሁኔታ ከቅጣት ምት ዘነበ ከበደ 70ኛው ደቂቃ ያሻገረውን በረከት ሳሙኤል በግንባሩ ገጭቶ በሚያስቆጭ ሁኔታ ግብ መሆን ሳይችል ቀርቷል።

ድሬዎች የጎል ዕድል ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት በጨዋታ እንቅስቃሴ ኳሱን አደራጅተው ከመጫወት ይልቅ በቆሙ ኳሶች በሚገኙ አጋጣሚዎች በመሆኑ ስኬታማ ሳያደርጋቸው ቀርቷል። በአንፃሩ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቆጣጠር ኳሱን በመያዝ እና ተከላካይ ቀይሮ በማስገባት በጥንቃቄ መከላከልን ምርጫ በማድረግ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች የግብ ዕድል ይፈጥሩ የነበሩት ሲዳማዎች 77ኛው ደቂቃ ላይ ከሲዳማ ቡና የሜዳ ክፍል የተጣለለትን ኳስ ከተከላካዮች ጀርባ የነበረው አዲስ ግደይ በፍጥነት ወጥቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ሦስተኛ ጎል በቀላሉ አስቆጥሯል።

ይህ ጎል የድሬዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ ዝቅ ቢያደርግም በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ በርከት ያሉ የጎል አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። በተለይ ሐብታሙ ወልዴ የመታውን እና ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ወደ ውጭ ያወጣበት እንዲሁም ምንያህል ይመር በግሩም ሁኔታ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውን መሳይ በድጋሚ በሚገርም ሁኔታ አድኖበታል። 84ኛው ደቂቃ ላይ ግን በዕለቱ በድሬ በኩል በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ገናናው እረጋሳ ብስለቱን ያሳየበት ማስተዛዘኛ ጎል አስቆጥሯል።

በመጨረሻም የሲዳማ ቡናዎችን የግብ መጠን ከፍ የሚያደርግ አጋጣሚን አዲስ ግደይ ቢፈጥርም ሊጠቀምበት ሳይችል ቀርቶ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አንድ ክስተት ሜዳ ላይ ተፈጥሯል። በረከት ሳሙኤል እና ግርማ በቀለ የፈጠሩት አለመግባባትን ተከትሎ የፊት ጥርሱ የወለቀው ግርማ በቀለ ሜዳው ላይ የወለቀ ጥርሱን በማሳየት በረከት ሳሙኤል እንደመታው በእንባ ለዕለቱ ዳኞች እና ኮሚሽነሩ ቅሬታውን ሲያቀርብ ተመልክተናል።

በሲዳማ ቡና የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተደሰቱት የድሬደዋ ከተማ ስፖርት አፍቃርያን ተጫዋቾቹን አድንቀው እና አጨብጭበው ከስቴዲየሙ ሸኝተዋቸዋል።

የውድድር ዘመኑን መክፈቻ በሜዳው ፋሲል ከነማን 2-1 በማሸነፍ በድል የጀመረው ሲዳማ ቡና የአንደኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታቸውንም ከሜዳው ውጭ ድሬዳዋ ከተማን 3-1 በመርታት ከመቐለ 70 አንድርታ ዝቅ ብለው 2ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል። ድሬደዋ ከሜዳ ውጭ በመክፈቻ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና 2-1 ሽንፈት ጀምረው የአንደኛ ዙር መዝጊያ ጨዋታቸውንም በሜዳቸው 3-1 በመሸነፍ 12ኛ ደረጃ በመያዝ ፈፅመዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *