ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ አራት – ክፍል አንድ)

በእንግሊዛዊው የእግርኳስ ጸኃፊ ጆናታን ዊልሰን ደራሲነት በ2008 ለንባብ የበቃው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics ን በሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ክፍሎች እያቀረብንላችሁ እንገኛለን፡፡ በዛሬው መሠናዶም የአራት የመጀመርያ ክፍልን እነሆ ብለናል፡፡

|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ LINK

 

የማዕከላዊ አውሮፓን እግርኳስ የቀየሩ ቡና መጠጫ ቤቶች

ኸርበርት ቻፕማን በጥንቱ ዘመን እግርኳስ አጨዋወት ላይ ከታዩ ቀደምት ችግሮች መካከል ለአንደኛው ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የጣረና የተወሰነ ለውጥም የፈጠረ አሰልጣኝ ነው፡፡  በጊዜው የቻፕማን የጨዋታ ዘዴ ውጤታማ በመሆኑ የእንግሊዝ እግርኳስም የእርሱን ፈለግ እንዲከተል ተገዷል፡፡ ይሁን እንጂ ሶስተኛውን ተከላካይ የሚያካትተው አዲሱ የቻፕማን የጨዋታ ስልት ሌሎች እንግሊዛውያን የታክቲክ ባለሟሎች የያዘ ትውልድ እንዲፈራ አላበረታታም፡፡ ዊሊ ሜይዝል ሲጽፍም “ያለመታደል ሆኖ የተሰራው የጀሶ ልስን ባለበት ቆየ፤ አንድም የእግርኳስ ምትሃተኛ ወይም ምሁር ይህን የግንባታ ስሪት የተለየ መልክ አልሰጠውም፡፡ የትኛውም አካል በሌላ ቅርጽ መልሶ ሊያንጸውም አልሞከረም፡፡” አለ፡፡ እንዲያውም ታክቲካዊ ለውጥ ያልተፈጠረ ለማስመሰል የሚደረገው ሙከራ የበለጠ ተመራጭ ሆነ፡፡ ቀኖናዊው የፒራሚድ ፎርሜሽንም ምንም አይነት ማሻሻያ ሳይደረግበት እንዳለ ስለመቆየቱ ማሳየት ቅድሚያ ተሰጠው፡፡

በ1939 የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር አመራሮች  በተጫዋቾች መለያ ላይ ቁጥሮች እንዲጻፉ አስገዳጅ ውሳኔ ሲያሳልፉ ወደፊት በእግርኳሱ  ሊከሰቱ የሚችሉ መጻኢ እድገቶችን በመገንዘብ ረገድ ቸልተኛነት አሳዩ፡፡ ተጫዋቾች ጀርባቸው ላይ የሚሰፍረው የመለያ ቁጥር በሜዳ ላይ ከሚኖራቸው ቦታ አያያዝና ከሚወጡት ኃላፊነት ጋር ታስቦ በሚከተለው አኳኋን እንዲሆን ሃሳብ ቀረበ፡፡ በዚህም መሰረት የቀኝ መስመር ተከላካይ-2፣ የግራ መስመር ተከላካይ-3፣ የቀኝ መስመር የመሃል አማካይ-4፣ የመሃል ተከላካይ አማካይ-5፣ የግራ መስመር የመሃል አማካይ-6፣ የቀኝ መስመር አማካይ-7፣ የቀኝ መስመር የውስጥ አጥቂ-8፣ የመሃል አጥቂ-9፣ የግራ መስመር የውስጥ አጥቂ-10 እና የግራ መስመር አማካይ-11 ቁጥሮች ያሉባቸውን መለያዎች እንዲለብሱ ተደረገ፡፡ በወቅቱ 2-3-5 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ዓለም አቀፋዊ ቅቡልነቱ ከፍተኛ ስለነበርና ፎርሜሽኑ በመነሻነት ተወስዶ የሚፈጠሩ ሌሎች ግትር የተጫዋቾች ቦታ አጠባበቅን የሚያሳዩ መዋቅሮች እንዲሁ ለይስሙላ የሚሞከሩ በመሆናቸው የእግርኳስ ማኅበሩ ኃላፊዎች የቁጥር አሰጣጡ የ2-3-5 ፎርሜሽን ላይ እንዲመሰረት አጥብቀው ወተወቱ፡፡ ከዚያም W-M ፎርሜሽንን የሚጠቀሙ ቡድኖች ከታች በተመለከተው ዘመናዊ ምስል እንደሚታየው የተጫዋቾቻቸውን የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ዝርዝር 2-5-3፣ 4-6፣ 8-10፣ 7-9-11 አድርገው ያቀርቡ ጀመር፡፡ ይህም በብሪታንያ እግርኳስ ወስጥ የመሃል-ተከላካይ አማካይ (Centre-Half) እና የመሃል ተከላካይ (Centre-Back) ሚናን ተመሳሳይ አድርጎ የማየት ስር የሰደደ ግራ መጋባት ፈጠረ፡፡

በተመሳሳይ ጋዜጦችም እውነታውን ስተው የቡድኖችን ተሰላፊዎች በሚያሳዩ ህትመቶቻቸው ላይ እስከ 1960ዎቹ ድረስ ሁሉም ክለቦች 2-3-5 ፎርሜሽን እንደሚተገብሩ የሚያሳብቅ መረጃዎች ማቅረባቸውን ገፉበት፡፡  ቼልሲዎች በ1954 የቡዳፔስቱን ቬሮስ ሎቦጎ ሲገጥሙ ከአንድ ዓመት በፊት በዌምብሌይ ስታዲየም እንግሊዝ በሃንጋሪ በደረሰባት ከፍተኛ ሽንፈት ምክንያት ታክቲካዊ ለውጦች ያላቸው ዋጋ በቀላሉ የማይታይ እንዳልሆነ መጠነኛ ንቃት ያደረባቸው የክለቡ ሰዎች ጨዋታው በሚደረግበት ዕለት ባወጡት የመርሃ-ግብር ማሳያ መጽሄት ላይ የሃንጋሪውን ክለብ ፎርሜሽን በትክክል የማተም ጥረት አደረጉ፡፡ ይሁን እንጂ በከንቱ ስሜት ተመርተው የእነርሱ W-M ፎርሜሽን ራሱ 2-3-5 ስለመሆኑ መግለፃቸውን ተያያዙት፡፡ በዘመኑ የእንግሊዞች እግርኳሳዊ አመለካከት እጅግ ወግ አጥባቂነት የተንሰራፋበት እንዲሁም ተጫዋቾች ቀጥተኛ ባላጋራዎቻቸው ጀርባ ላይ ያሉትን ቁጥሮች በማየት የቅርብ ክትትል ያደርጉ ነበር፡፡ ስለዚህም በ1950ዎቹ የዶንካስተር ሮቨርሱ አሰልጣኝ ፒተር ዶኸርቲ አንድ መላ ዘየደ፡፡ የቡድኑ ተጫዋቾች አልፎ አልፎ መለያዎቻቸውን እንዲቀያየሩ በማዘዝ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን ትኩረት በማወሳሰብ እና እንዲደነጋገሩ በማድረግ ስኬታማ መሆን ቻለ፡፡

የእግርኳስ ታክቲክ አስፈላጊነትና ፋይዳ ሙሉ በሙሉ እውቅና እንዲያገኝ በፍጥነት መላምቶችን በሚያፈልቁና መልሰው በሚያሻሽሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ጨዋታው ተወዳጅ መሆን ነበረበት፡፡ የረቂቁን እና ጥልቁን ጽንሰ-ሐሳባዊ ውጥን ሜዳ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ መጣር ምቾት የሚሰጣቸው እነዚህ አካላት የእግርኳስ ሁለንተናዊ አቀራረብ ላይ አዎንታዊ አሻራቸውን ለማሳረፍ ወደ ኋላ ብለው አያውቁም፡፡ ያም ሆኖ ይህ ተመክሮ አንዳንዴ በብሪታንያ የሚታየውን በጠራ አመክንዮ ላይ ጥርጣሬ የማሳደር ልማድን ሊቀይር አልቻለም፡፡ 

በአንጻሩ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች መሃል በነበረው ጊዜ ” የንድፈ-ሐሳብ ጥንስስም ሆነ የአመለካከት አቋም በደመነፍሳዊ እምነት ሳይሆን በምክንያታዊነት ላይ መመስረት አለበት፡፡” የሚለው እውነታ በመካከለኛው የአውሮፓ ክፍል በሚዘወተረው እግርኳስ ላይ ታየ፡፡ የካፒታሊስት ስርዓትን የሚመሩ በቁጥር በርከት ያሉ አይሁዳውያን የኦስትሪያና ሃንጋሪ ከበርቴዎች ቀደም ብሎ በዩራጓውያኑና አርጀንቲናውያኑ እግርኳስ ውስጥ በሰረጸው የአጨዋወት ፍልስፍና ዙሪያ ማብራሪያዎችን ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ በዚህም መነሻነት ስለጨዋታው በቂ ግንዛቤ የሚያስገኙ ውይይቶችን የማድረግ ዘመናዊ ልምዶች ቪየና በሚገኙ ቡና መጠጫ ቤቶች (Coffe Houses) ተጀመረ፡፡

በ1924 በተዋረድ ሁለት እርከኖች ያሉት ፕሮፌሽናል ሊጎች በመጀመሩ ምክንያት በኦስትሪያ የእግርኳስ ተደራሽነት በሒደት እየሰፋ ሄደ፡፡ በአስራ ዘጠኝ ሃያዎቹ መባቻ አካባቢ ደግሞ የጨዋታው ተፈላጊነት እና ዝና በሃገሪቱ ውስጥ ናኘ፡፡ በዚሁ ዓመት ህዳር ወር <ኔውስ ዌርነር> የተሰኘው መጽሔት ” ከሁሉም የስፖርት አይነቶች ውስጥ ዘወትር ከእሁድ-እሁድ በትንሹ በአማካኝ ከአርባ እስከ ሃምሳ ሺህ የሚደርሱ ደማቅ ህብረ ቀለም ያላቸው ተመልካቾች በስታዲየም ተገኝተው የሚታደሙት በየትኛው የጨዋታ አይነት ነው? አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በእግርኳስ የሚማረከውስ የት ሃገር ይሆን? የሊግ ግጥሚያዎች በተደረጉበት ምሽት ስለተመዘገቡ ውጤቶች እና የሚደግፈው ቡድን በቀጣይ ጨዋታዎች ሊገጥመው ስለሚችል ስኬት ሲያወራ ልትሰሙ የምትችሉት በየትኛው ቦታ ነው፡?” ሲል ጠየቀ፡፡ መልሱ ቀላል ነበር፦ ከብሪታኒያ ውጪ በሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ሊሆን አይችልምና፡፡

ይሁን እንጂ በብሪታኒያ የእግርኳስ ጨዋታን የሚንተራሱ ውይይቶች የሚካሄዱት በመጠጥ ቤቶች ሲሆን በኦስትሪያ ግን በሻይ-ቡና መገባበዣ ካፌዎች ውስጥ ነበር፡፡ በእንግሊዝ እግርኳስ በህዝብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደ ጊዜ ማሳለፊያ ቢጀመርም በ1930ዎቹ በዋናነት የሰራተኛው መደብ ስፖርት ሆነ፡፡ በማዕከላዊው የአውሮፓ ክፍል የታየው የእግርኳስ አጀማመር ግን በመጠኑ ወሰብሰብ ያለ መልክ ነበረው፡፡ በአካባቢው ጨዋታውን ያስተዋወቁት እንግሊዛውያኑ በመሃከለኛ መደብ የሚገኙ የህብረተሰቡ አካላት ቢሆኑም እግርኳስ በሰራተኛው መደብ ተቀባይነት ለማግኘት ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ በእርግጥ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከዚሁ የማኅበረሰብ ክፍል ቢወጡም በሒደት ልሂቃኑም ተሳታፊ እየሆኑበት መጡ፡፡

በማዕከላዊው የአውሮፓ ክፍል የታየው እግርኳስ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መጠን በከተሞች ብቻ የተገደበ ተደራሽነት አሳየ፡፡ ጨዋታው ቪየና፣ ቡዳፔስት፣ ፕራግ እና ሌሎች ከተሞችን ማዕከል ከማድረግም አልፎ በእነዚህ ቦታዎች የእግርኳስ ውይይቶች የሚካሄዱባቸው የቡና መጠጫ ቤቶች ባህልም ይበልጡን ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ የሃብስበርግ አገዛዝ ዘመን (ከአስራ አራተኛው እስከ አስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የዘለቀ የጀርመናውያኑ ዘውዳዊ ስርዓት ሲሆን የተለያዩ መሪዎችን ወደ አውሮፓ ሃገራት ይልክ የነበረ ንጉሳዊ መንግስት ነው፡፡) ወደ ማብቂው በተቃረበበት ወቅት በከተሞች ውስጥ ቡና መጠጫ ቤቶች ተስፋፉ፡፡ እነዚህ ቤቶች ሰዎች በብዛት የሚሰባሰቡባቸው ስፍራዎችም ሆኑ፤ ከሁሉም ማህበረሰባዊ መደቦች የተውጣጡ ወይዛዝርትና ወጣቱ በአንድ ላይ የሚገናኙባቸው የመናኸሪያ ድባብ ተላበሱ፡፡ በስብሰባዎቹ ያልተለመዱና አዳዲስ አሰራሮችም እየተዘወተሩ ስነ-ጥበባዊና ኪነ-ጥበባዊ ህብር ፈጠሩ፡፡ እነዚያ ቤቶች ውስጥ ሰዎች ሻይ-ቡና እየተባባሉ ጋዜጦችን ያነባሉ፤ ደብዳቤዎች ይጻጻፋሉ፤ ቼዝና ካርታም ይጫወታሉ፡፡ ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ተሳታፊ የሆኑ እጩዎችም ቡና ቤቶቹን እንደ ውይይት ማድረጊያ እና መከራከሪያ መድረኮች ተጠቀሙባቸው፡፡ ምሁራኑና ተከታዮቻቸው ደግሞ የየዕለቱ መሰረታዊ አርእስቶች ላይ ምክክር ያደርጉ ጀመር፡፡ ኪነጥበብ፣ ስነ-ጽሁፍ፣ ድራማ ቆየት ብሎ ደግሞ በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መነሻ ላይ እግርኳስ የጭውውቶቻቸው ዋነኛ አጀንዳዎች ሆኑ፡፡

ሁሉም የእግርኳስ ክለቦች፣ ተጫዋቾች፣ ደጋፊዎች፣ የቡድን አመራሮች እንዲሁም ጸኃፊዎች የሚገናኙባቸው የየራሳቸው ካፌዎች ነበሯቸው፡፡ ለምሳሌ የኦስትሪያ ቪየና ደጋፊዎች በፓርሲፋል ካፌ ይታደማሉ፤ የራፒድ ቪየናዎቹ ደግሞ ወደ ካፌ ሆለብ ይተማሉ፡፡ ይሁን እንጂ በሁለቱ የአለም ጦርነቶች መካከል በነበረው ጊዜ የእግርኳስ ትዕይንቶች እምብርት የነበረችው ሪንግ ካፌ ናት፡፡ ካፌዋ ቀደም ሲል የእንግሊዛውያን ክሪኬት ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ማዘወተሪያ ስፍራ በመሆን አገልግላለች፡፡ ከ1930ዎቹ ዓመታት በኋላ ግን የሰፊው እግርኳስ ወዳድ ማህበረሰብ መገናኛ ማዕከል ሆነች፡፡ <ዌልት አም ሞንቴዥ> የተሰኘ ጋዜጣ ላይ እንደተጻፈው ከሆነ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ” ቡና መጠጫ ቤቶቹ ለእግርኳስ ደጋፊዎችና ጽንፈኞች አብዮታዊ ፓርላማ ነበሩ፡፡  በቪየና መሰረቱን ያደረገ እያንዳንዱ ክለብ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ ዘወትር የሚቆረቆርለት ወገኑ ስለሚገኝ ለአንድ ክለብ ብቻ የሚያደላ ሃሳብ ፍጹም አይሰነብትም፡፡”

የራፒድ ክለብ የመሃል አጥቂ በነበረው ጆሴፍ ኦሪድሊ ታሪክ አማካኝነት ሰፊ የሆነ ባህል ባለበት አካባቢ ላይ እንኳ እግርኳስ ያለው ተጽዕኖ ይበልጡን ግልጽ እየሆነ ሄደ፡፡ ኦሪድሊ የተወለደው ከቪየና ወጣ ብላ በምትገኘውና በሰራተኛው መደብ ማህበረሰብ አማካኝነት ከፍተኛ ውጥረት ከነገሰባት የገጠር መንደሮች ውስጥ በአንዷ ነው። ጠንካራ የሆነው የተጫዋቹ አጨዋወት ስልት ክለቡ በዝቅተኛው መደብ አባላት ዘንድ ስር የሰደደ ድጋፍ እንዳለው አመላካች ነበር፡፡ ኦሪድሊ ለቡና-መጠጫ ቤቶች የመጀመሪያው የእግርኳስ ጀግናቸው ሆነ፡፡ በ1922 ደግሞ በዝነኛው የምሽት ክበቦች ሙዚቀኛ ሄርማን ሊኦፖልዲ የተቀነቀነው <ሂውቴ ስፒየል ደር ኡንዲሊ> ዘፈን ርዕሰ ጉዳዩ በተጫዋቹ ዙሪያ አጠነጠነ፤ እጅግም ስኬታማነት ተጎናጸፈ፤ ለእግርኳስ እምብዛም ፍላጎት በማያሳድሩ ሰዎች ዘንድ እንኳ ተወዳጅነት አግኝቶ ተቀባይነቱ ናረ፤ በዚህም ምክንያት የተጫዋቹ ዝና በሃገሪቱ በሰፊው ናኘ፡፡ ከዚያም ከሳሙና አንስቶ እስከ ፍራፍሬ ጁስ ድረስ ያሉ በርካታ ምርቶችን ማስተዋወቅ  ጀመረ፡፡ ቀጠለና በየካቲት 1924 የሙዚቃ ድግስ መድረኮች ላይ ፕሮግራም አስተዋዋቂ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም የራሱን ህይወት በሚተርክ <ፍሊች ኧንድ ኤህር> የተሰኘ ፊልም ላይ ዋና ገጸባህሪውን ወክሎ ተጫወተ፡፡ ፊልሙ በሲኒማ ቤቶች እንደጉድ ይታይለት ነበር፡፡

እንግዲህ በእነዚያ ከባቢያዊ ሁኔታዎች ውስጥ ነው የሑጎ ሜይዝል <ዉንደር ቲም> ማበብ የጀመረው፡፡ በአስራ ዘጠኝ ሃያዎቹ መባቻ ላይ የታየው የእግርኳስ አጨዋወት ስልት ሰፊ ተቀባይነት በማግኘት ሒደት ውስጥ ነበር፡፡ ከመካከለኛው አውሮፓ ተውጣጥተው በሚሳተፉ ሃገራት የሚደረገው የእግርኳስ ዋንጫ ሲጀመር በዶ/ር ጊሮ አማካኝነት በተዘጋጀው የመክፈቻ ውድድር ኦስትሪያ በወረደ ብቃት እጅግ መጥፎ ጅማሮ ብታደርግም ከቶርናመንቱ ሳትሰናበት በእንጥፍጣፊ ዕድል ተረፈች፡፡ ለሰላሳ ወራት በሚዘልቀው፥ ቼኮስሎቫኪያ፣ ሃንጋሪ፣ ሲውዘርላንድና ጣልያን በሚሳተፉበት የሊግ-ፎርማት ያለው ውድድርም ቀሪ ጉዞዋን ተያያዘችው፡፡ ከመክፈቻዎቹ ተከታታይ አራት ጨዋታዎች ሶስቱን ብትሸነፍም በቀጣይ ሃንጋሪን 5-1 ረምርማና በውድድሩ መጨረሻ የዋንጫው ባለድል የሆነችው ጣልያንን 3-0 በማሸነፍ በአንድ ነጥብ ተቀድማ ሁለተኛ ሆና አጠናቀቀች፡፡ ኦስትሪያኖቹ በሪንግ ብቃት ደስተኞች አልሆኑም፡፡ በዚህም ሳቢያ ማቲያስ ሲንድለርን ለመምረጥ ተነሳሱ፡፡ ከአይሁድ ከበርቴዎች ጋር ጥብቅ ቁርኝት መስርቶ ትልቅ ድጋፍ ከሚደረግለት ኦስትሪያ ቪየና ክለብ የተገኘው ይህ ተጫዋች ከስሜታዊነት ይልቅ ሰከን ባለ ባህሪው የሚታወቅ ፣ ብልህና ባለተሰጥዖ የመሃል አጥቂ ነበር፡፡

ሲንድለር ባልተለመደ የመሃል አጥቂዎች  ዘይቤና ሚና ብቅ ያለ ተጫዋች ነው፡፡ ከግዙፍ ስብዕናው በተጻራሪ አጠር ባለው ቁመቱ እና በደቃቃ ተክለ ሰውነቱ የተነሳ <ደር-ፐፒሬኔ> ወይም <ልስልሱ> እያሉ በቅጽል ስሙ ይጠሩታል፡፡ አያሌ ፀሃፍት ስለፈጠራ ክህሎቱ ሲያነሱ “ከሲታ፣ ባለ ምጡቅ አዕምሮ እንዲሁም ከደራሲዎች ያልተናነሰ የመፍጠር ብቃት ባለቤት ነበር፡፡” ይሉለታል፡፡ ሲንድለር ተገቢውን ጊዜ ጠብቆ ለሚከወን ማንኛውም ነገር ክብር ይሰጣል፡፡ ሳይታሰብ በድንገት ለሚፈጠሩትም ሆነ በጥበብ ለሚታነጹ ድራማዊ ክስተቶች ጥልቅ ስሜት ያሳያል፡፡ ከቀደምት የቡና መጠጫ ቤቶች ከወጡ ጸሃፊያን አንዱ የሆነው ፍሪየድሪክ ቶበርግ <ዳይ ኧርበን ደር ታንት ቶሌች> በተሰኘ የ1978 መጽሃፉ ላይ እንደገለጸው ” ሲንድለር እጅግ በማይታመን መልኩ የብዙ ሃሳቦች ባለቤት ከመሆኑም በላይ ከሌሎች ተጫዋቾች አንጻር ሲታይ ከመደበኛ ደረጃ ላቅ ያሉ ብልጫዎችን የታደለ ነበር፡፡ በጨዋታዎች ወቅት ተጋጣሚ ቡድኖች እርሱ የትኛውን የአጨዋወት ስልት እንደሚተግብር እርግጠኛ እንዳይሆኑ የማድረግ አቅም ነበረው፡፡ የሚገርመው የጨዋታ አቀራረብ መዋቅር አልዘረጋም፤ ማሸነፊያ ቀመር የመንደፍ ፍልስፍናንም አልተከተለም፡፡ በቃ እንዲሁ የተለየ አዕምሯዊ ብቃት ነበረው፡፡” ሲል አወድሶታል፡፡

ለሲንድለር ይህ ሁሉ ሙገሳ ቢቸረውም ሑጎ ሜይዝል ግን ተጠራጣሪው ነበር፡፡ በእርግጥ በ1926 ተጫዋቹ የሃያ ሶስት ዓመት ወጣት ሳለ ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሄራዊ ቡድኑ እንዲጫወት ጥሪ አቀረቦለታል፡፡ ይሁን እንጂ ሲንድለር ለአዲሱ የእግርኳስ አጨዋወት ጽንሰ ሐሳብ ግንባር ቀደም የድጋፍ ተሟጋች ሆኖ በመቅረቡ ከአሰልጣኙ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ለመመስረት ሳይቸገር አልቀረም፡፡ ሜይዝል ከፍተኛ ወግ አጥባቂነት የተጸናወተው እና ሙሉ ታክቲካዊ ስራዎቹ በትዝታ ወደኋላ የሚጎትቱ ስለነበሩ ቀዳሚውን የእግርኳስ አጨዋወት ስርዓት ናፋቂ አድርገውታል፡፡ በወጣትነቱ በ1905 ከሃገር-ሃገር እየተዟዟሩ ግጥሚያዎችን በማድረግ ይታወቁ በነበሩት ሬንጀርሶች የጨዋታ አቀራረብ ስለተማረከም የእነርሱን ስልት በድጋሚ ለመፍጠር የመጣር አዝማሚያ ታየበት፡፡ እነዚያ ጥልፍልፍ (Weaving Pattern Passes) ያሉት የስኮትላንዳውያኑ አጫጭር ቅብብሎች ላይ ችግር በማለት ሶስተኛ ተከላካይ የሚያካትተውን አዲስ አቀራረብ ችላ አለ፡፡ “አንድ የፊት አጥቂ እንደ ኡርዲሊ ተክለሰውነቱ የገዘፈ መሆን አለበት፡፡” የሚለውን ሐሳብም የሙጥኝ ብሎ ቆየ፡፡

ኡርዲሊና ሲንድለር ከሞራቪያን ስደተኞች የተገኙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ሁለቱም ከከተማ ወጣ ብለው በሚገኙ ትናንሽ የገጠር መንደሮች ያደጉ እና በጥረታቸው ደግሞ የዝናን ጣሪያ የነኩ ሆነዋል፡፡ (ሲንድለር በእግርኳስ ከሚያገኘው ገቢ ጎን ለጎን በፊልሞች ላይ በመተወን እንዲሁም የእጅ ሰዓትና የወተት ምርቶችን በማስተዋወቅ ተጨማሪ ገንዘብ ይሰራ ነበር፡፡)  እንዲህም ሆኖ ሁለቱን ተጫዋቾች የሚያመሳስላቸው የጋራ ነገር አነስ ይላል፡፡ ቶርበርግ በጽሁፉ እንደገለጸውም  ” እነርሱ (ኡርዲሊና ሲንድለር) በእውቅና ሊነጻጸሩ ይችሉ ይሆናል፡፡ በቴክኒካዊ ክህሎት፣ ፈጠራ፣ ጥበብና ተሰጥዖን በመሳሰሉ ዝርዝር ጉዳዮች ያወዳደርናቸው ከሆነ ግን የሰማይና የምድር ያህል ይራራቃሉ፡፡ እንዲያውም እነርሱን በአንድ ሚዛን ላይ ለማስቀመጥ መሞከር ትልቅ የጭነት ቦቴን ከትንሽ ጠፍጣፋ የብረት ዘንግ ጋር እንደ ማነጻጸር ነው፡፡” አለ፡፡

በመጨረሻ ማለትም በ1931 ሜይዝል በሲንድለር ምክንያት በሚደርሱበት ጫናዎች ተረታና ፊቱን ወደ ተጫዋቹ አዞረ፡፡ የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊም አደረገው፡፡ ውሳኔውም ወዲያውኑ ፍሬ አፈራለትና አስገራሚ ውጤቶች ማሳየት ቻለ፡፡ በግንቦት 16-1931 ኦስትሪያ ስኮትላንድን 5-0 ረመረመች፡፡ <የዌምብሌይ ምትሃተኞች> እንግሊዝን በሜዳዋ የ5-1 ድል ከተቀዳጁ ከሁለት ዓመት ተኩል ጊዜያት በኋላ ስኮትላንዳውያኑም  በተመሳሳይ የአጨዋወት ዘይቤና እጅጉን በላቀ የተጋጣሚ ብቃት ሲቸገሩ ዋሉ፡፡ በጨዋታው በአስትሪያ የበለጠ ስኬታማ እንቅስቃሴ ተደርጎባቸው እና ብልጫ ተወስዶባቸው ተገኙ፡፡ በእርግጥ ከሴልቲክም ሆነ ከሬንጀርስ ክለቦች ምንም ተጫዋቾችን ሳያካትቱና ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሄራዊ ቡድን የተጠሩ ሰባት ተጫዋቾችን ያሰለፉት ስኮትላንዶች ጨዋታው እንደተጀመረ የቡድኑን ወሳኝ ተጫዋች ዳንኤል ሊድልን በጉዳት አጡ፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት የጭንቅላት ግጭት የደረሰበት ኮሊን ማክናብም የሚጠበቀውን ያህል ሳይንቀሳቀስ ዋለ፡፡ <ዴይሊ ሪከርድ> የተባለው ጋዜጣ በጨዋታው ዙሪያ ሃቀኛ ምስክርነቱን ሰጠ፡፡ ስኮትላንዳውያኑ “ከፍተኛ ብልጫ ተወሰደባቸው፡፡ ” ሲል ሽንፈቱን አራገበው፡፡ ” ምንም አይነት ሰበብ አያሻውም! የበረኛው ጆን ጃክሰን ጥሩ ብቃት ባይታከልበት ኖሮ ቡድኑ ላይ ከዚህም የከፋ ውርደት ይደርስበት ነበር፡፡” ሲልም አከለ፡፡

ኦስትሪያውያኑ ስኮትላንድን ከማሸነፋቸው ከሁለት ቀናት በፊት በፓሪስ ከተማ እንግሊዝ በፈረንሳይ 5-2 መረታቷን ተከትሎ ሳምንቱ ለቀደምቶቹ የእግርኳስ ጀማሪ ሃገራት ያልተለመዱ ችግሮች መነሻ ወቅት መሰለ፡፡ ይሁን እንጂ የተቀረው ዓለም ሳይወድ በግድ ከብሪታኒያ እግርኳሳዊ ባህል ጋር ማበሩን እና ጥብቅ ቁርኝት መመስረቱን ለመካድ አይቻልም፡፡ የብሪታኒያ ጋዜጦችና የእግርኳስ ባለስልጣናቱም የተጋረጠባቸውን ውጤት የማጣት ተግዳሮት ለመጋፈጥ ተከታታይ ሙከራቸውን ሊገቱ አልፈለጉም፡፡ <ዘ አርቢትር-ዜይቱንግ> የጊዜውን ሁኔታ በአግባቡ አስቀምጦታል፡፡ ” ስኮትላንዳውያኑ ያወረሱን የእግርኳስ አጨዋወት ስልት ኮስምኗል፡፡ ይህን ውድቀት የሚያስቃኝ የሙሾ ስንኝ ቢገኝ በዚያ ዘመን ቱባውን ጥበባዊ የጨዋታ አቀራረብ ከያዘው እግርኳስ ይልቅ በሌሎች ነባር የአጨዋወት ስርዓቶች የሚከወነው ጨዋታ ይበልጡን የሚበረታታ እና ምስጋና የሚቸረው እንደነበር የሚያወሳ ነው፡፡” ሲል ዘገባው የስኮትላንዳውያኑ ቅብብሎች ላይ የሚያተኩር አቀራረብ እየከሰመ ስለመምጣቱ አስረዳ፡፡ የጋዜጣው ጽሁፍ ቀጠለና ” አስራ አንዱ ተጫዋቾች – ጨዋታውን ቀዳሚ ስራቸው ያደረጉ አስራ አንድ እግርኳሰኞች ናቸው፡፡ እውነት ነው፥ በህይወት ውስጥ ከእግርኳስም በላይ አስፈላጊ የሆኑ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ቪየናውያኑ በእግርኳስ ውስጥ ውበትን በሚመለከት ለሚያሳድሩት ጥልቅ ስሜት፣ ለምናባዊ ፈጠራቸው እና ትጋታቸው ሊቸር የሚገባ ከፍተኛው የአድናቆት መግለጫ ድርጊት ነው፡፡” ብሎ አከለ፡፡

ይህ አንጻራዊ ውጤታማነት <ዉንደርቲም> ተብሎ ለሚጠራው ቡድን ጅማሮው ነበር፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ጥሩ የማጥቃት ባህሪ ባለው የመሃል-ተከላካይ አማካዩ ጆሴፍ ሲሚስቲክ ላይ  ተመስርቶ ተለምዷዊውን 2-3-5 ፎርሜሽን   ይተገብራል፡፡ በጊዜው ቀጥተኛ ያልሆነ የመሃል አጥቂ በመጠቀም ማራኪና ፍሰት ያለው አጨዋወት ማሳየት የቻለው ይህ ቡድን <የዳኑቢያን ምትሃተኞ> የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡  ለሁለተኛ ጊዜ በተዘጋጀው የዶ/ር ኼሮ ዋንጫ ላይም ኦስትሪያውያኑ ከአስራ አንድ ጨዋታዎች ውስጥ ዘጠኙን አሸንፈው በሁለቱ አቻ ወጡ፡፡ በውድድሩም አርባ አራት ግቦች በማስቆጠር ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ፡፡ በሃገሪቱ የተስፋፉት ቡና መጠጫ ቤቶች የደስታ ስሜት የሰፈነባቸው ሆኑ፤ ቤቶቹ ነገሮችን የሚከውኑባቸው ሁኔታዎች በሌሎች ስፍራዎች ተደራሽነታቸው ከፍ አለ፡፡ የአይን ብሌናቸውን ያህል በሚሳሱለት ሲንድላር ምክንያት ደግሞ ቡና ቤቶቹ ጥብቅ ጉርብትና መሰረቱ፡፡ ” አንድ በክህሎቱ ከፍተኛው ደረጃ ላይ እንደደረሰ አለምአቀፋዊ ቼዝ ተጫዋች ሲንድለርም እግርኳስን በዚያ ልህቀት ይጫወተዋል፡፡ ሰፋ ባለ እግርኳሳዊ አዕምሮና አረዳድ ሜዳ ላይ እያንዳንዱን የመከላከል እና የማጥቃት እንቅስቃሴ እያጤነ፣ በጨዋታው ሒደት ቀጥሎ የሚመጣውን ሁኔታም እየቀመረ ሁሌም እጅግ የሚያዋጣውን መንገድ ይመርጥ ነበር፡፡” ሲል በወቅቱ ትያትሮች ላይ ጠለቅ ያለ ሂስ በመስጠት የሚታወቀው ታዋቂው ሐያሲ አልፍሬድ ፖልጋር <ፓሪዚዬ ታገስዜይቱንግ> በተባለው ጋዜጣ ላይ የሲንድላር የቀብር ስነ ስርዓት በተካሄደበት ዕለት የተጫዋቹን አስገራሚ ጭብጥ እውነታዎች ጽፏል፡፡

ጋሊያኖ በአስራ ዘጠኝ ሃያዎቹ ዩሯጓውያኖችን ለመግለጽ የቼዝን ምሳሌ እንዳነሳው ሁሉ በተመሳሳዩ አናቶሊ ዜሌንሶቭም ለቫለሪ ሌቫኖቭስኪው ዳይናሞ ኬይቭ ተጠቅሞበታል፡፡ የጂሚ ሆጋን ተጽዕኖ እንዲሁም በፍጥነት ኳስን የመቆጣጠር አባዜው ግልጽ ቢሆንም ፖግላር ግን ተጨማሪ ሐሳብ ይሰጣል፡፡ ” ሲንድላር ተወዳዳሪ የሌለው ኳስ አዳኝ ፣ አስገራሚ የመልሶ ማጥቃት ባለሟል፣ በትክክለኛ የማጥቃት አጨዋወት ዑደት ወቅት ለቁጥር የሚታክቱ ታክቲካዊ ፊንታዎችን በመፍጠር የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን ሲያልፍ ለቁጥጥር አዳጋች ነበር፡፡ ባላንጦቹም ብዙውን ጊዜ በእርሱ ቴክኒካዊ ተሰጥዖ አማካኝነት በቀላሉ ሲታለፉ የሚያስደስት ድባብ ይፈጠር ነበር፡፡” ሲል የተጫዋቹን ድንቅ ስብዕና ያወሳል፡፡

ምናልባትም ከሁሉ የበለጠ በሚያስገርም ሁኔታ ሲንድለር በስነ ህይወት ዘርፍ የተፈጥሮን ዝግመታዊ ለውጦች በሚያጠናው ታዋቂው ተመራማሪ ስቴፋን ጄይ ጉልድ የመነጨውን <የልህቀት አለምዓቀፋዊ ተደራሽነት> አስተሳሰብ ቦታ ያስለቀቀ መሆኑ ነው፡፡ ጉልድ እንደጻፈው ” በተለመደ ምሁራዊ ግንዛቤ በታገዘ አቀራረብ እንዲሁም አካላዊ ብቃት ላይ ባመዘነ አጨዋወት መካከል ልዩነቶች መኖራቸውን አልክድም፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ጭካኔያዊ ድርጊቶችና ስሜቶች የሚንጸባረቁባቸው መድረኮች አድርገን በመመልከት ለስህተት እንጋለጣለን፡፡ ታላላቆቹ ስፖርተኞች በሰውነት ብቁነት ብቻ ስኬታማ አልሆኑም፤ ዋናው ቁምነገርእጅጉን ከሚያስደስቱትና ሊካዱ ከማይችሉት የስፖርት ትልልቅ አቋሞች ማሳያ ባህሪያት መካከል የተወሰኑትን ማዕከላዊ ብቃቶች ግልጽ በሆነ ምሁራዊ የውይይት እምነት አልያም ተግባር ለመቆጣጠር የማይቻል መሆኑ ላይ ያርፋል፡፡ ተፈላጊው አካላዊ እንቅስቃሴ ተራ በተራ ለሚደረግ አዕምሮዓዊ የውሳኔ ሒደት በቀላሉ በቂ የሚባል ጊዜ አይሰጥም፡፡” ይላል ተመራማሪው ጉልድ፡፡ ፓልጋር ደግሞ ” የሲንድለር አዕምሮውና እግሮቹ አስገራሚ መስተጋብር ፈጥረዋል፤ አስደናቂና የማይጠበቁ ክስተቶችን የሚከውነውም የሁለቱን ፍጥነቶች በማዋደድ ነው፡፡ የእርሱ ሃይል የቀላቀሉ ጠንካራ ምቶች መረቡን ሲወዘውዙ አስደሳች ስሜት ይፈጥራሉ፡፡ ግሩም የሆነውን የታሪክ ውህደትና ከፍታ ለመረዳትና ለማድነቅ እንድንችል የእርሱ ልዩ ክህሎት መሰረታዊ ነበር፡፡” በማለት በተዋበ አገላለጽ ስለ ሲንድለር እንድናውቅ ያግዘናል፡፡

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

Sunderland: A Club Transformed (2007)

Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

The Anatomy of England (2010)

Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

The Anatomy of Liverpool (2013)

Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)


ቀደምት ምዕራፎች
መቅድም LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አራት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል አራት LINK
ምዕራፍ 3 – ክፍል አንድ
LINK
ምዕራፍ 3 – ክፍል ሁለት
LINK
ምዕራፍ 3 – ክፍል ሦስት LINK
ምዕራፍ 3 – ክፍል አራት LINK

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *