የኢትዮጵያ ዋንጫ ቀጣይ ጨዋታዎች ይፋ ሆኑ

የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) የ2011 የውድድር ዘመን በተቆራረጠ መልኩ መካሄዱን በመቀጠል ቀጣይ አምስት ጨዋታዎች የሚደረጉበት ቀን በፌዴሬሽኑ ይፋ ተደርጓል።

ከውድድሩ የመጀመርያ ዙር ጨዋታዎች መካከል ሦስቱ ተካሂደው ስሑል ሽረ፣ ፋሲል ከነማ እና መከላከያ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ ሲያልፉ በደደቢት አለመሳተፍ ምክንያት ኢትዮጵያ ቡና ወደ ሩብ ፍፃሜው የተሸጋገረ ሌላው ቡድን ነው።

ፌዴሬሽኑ ባወጣው መርሐ ግብር መሠረት በቅድሚያ በኢትዮጵያ ቡና እና ስሑል ሽረ መካከል የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ የሚያደርጉ ሲሆን ቅዳሜ መጋቢት 7 ቀን 2011 በአዲስ አበባ ስታድየም ይካሄዳል።

ቀሪ የአንደኛ ዙር ጨዋታዎች በተለያዩ ጊዜያት ቡድኖቹ በሊጉ በሚገናኙበት ወቅቶች ይካሄዳሉ። ወላይታ ድቻ ከ ጅማ አባ ጅፋር ረቡዕ ግንቦት 14፣ መቐለ 70 እንደርታ ከደቡብ ፖሊስ ሐሙስ ግንቦት 22፣ ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ ረቡዕ ግንቦት 28፣ አዳማ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ ረቡዕ ሠኔ 5 ይደረጋሉ።

ሌሎች ጨዋታዎች (ቀሪ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች፣ የግማሽ ፍፃሜ እና ፍፃሜ ) መቼ እንደሚደረጉ ወደፊት እንደሚገለፅ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *