ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር ከፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተዋል

በጅማ አባ ጅፋር የአፍሪካ ውድድር ተሳትፎ ምክንያት በ10ኛ ሳምንት ሳይካሄድ የቀረው የጅማ አባ ጅፋር እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጅማ አባ ጅፋሮች መከላከያን ካሸነፉበት ስብስብ ውስጥ በተከላካይ ስፍራ ላይ መላኩ ወልዴን በማሳረፍ በምትኩ ከድር ኸይረዲንን፤ በአማካይ ስፍራ መስዑድ መሐመድን በሄኖክ ገምቴሳ በመተካት በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በፍየፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ በ15ኛ ሳምንት ስሑል ሽረን ካሸነፈው ስብስብ ውስጥ በርከት ያሉ ለውጦችን በማድረግ ጀማል ጣሰውን በሚኬል ሳማኬ፣ ሰለሞን ሀብቴን በፍፁም ከበደ፣ ዓለምብርሃን ይግዛውን በኤፍሬም ዓለሙ፣ አብዱረህማን ሙባረክን በበዛብ መለዮ እንዲሁም ቤንጃሚን ኤዲን በኢዙ አዙካ በመተካት በ4-3-3 አሰላለፍ ወደሜዳ ገብተዋል፡፡

የዛሬውን ጨዋታ ለመታደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በጅማ ስቴድየም የተገኙ ሲሆን ከጅማ አባ ጅፋር ፕሬዝዳንትና የጅማ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አጃይብ አባመጫ ስጦታዎች ተበርክቶላቸዋል፡፡

የዛሬው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ማሸነፍ ከቻሉ የደረጃ ለውጥ ስለሚያስከትል እንዲሁም ባለፉት ጊዜያት ፋሲል ከነማ ወደ ጅማ አቅንቶ በጅማ ቡድኖች ላይ ከወሰደው የበላይነት አንፃር የዛሬው ጨዋታ ተጠባባቂ አድርጎታል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጫወታ ክፍለግዜ በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች ፈጣን እቅስቃሴዎችን የተመለከትንበት በሁለቱም ቡድኖች በኩልም ለግብ የቀረቡ የግብ እድሎችን የፈጠሩበትና ተመጣጣኝ ፉክክርን ታይቶበታል። በ2ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ከድር ኩሊባሊ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ አግዳሚ ብረት ገጭቶ የወጣበት አጋጣሚ በፋሲል በኩል፤ በ5ኛው ደቂቃ ዲዲዬ ለብሪ ከቀኝ መስመር በነፃ አቋቋም ከግብጠባቂው ፊትለፊት ለሚገኘው ሲድቤ ያቀበለውን ሲዲቤ መቆጣጣር አቅቶት በተከላካዮች ርብርብ የወጣው አጋጣሚ በጅማዎች በኩል የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር፡፡

ከአስረኛው ደቂቃ በኋላ ጅማዎች የአጨዋወት ለውጥ በማድረግ ወደ 4-5-1 አሰላለፋቸውን በመቀየር በአምስት አማካዮች በመጠቀም በተሻጋሪ ኳሶችና በመልሶ ማጥቃትን ምርጫቸው አድርገዋል። በዚህም ከዐወት እና ዲዲየ ለብሪ ወደ ማማዱ ሲዲቤ የሚላኩ ተሻጋሪ ኳሶች በፋሲል ተከላካዮችን በቀላሉ ሲመለሱ እንዲሁም ተደጋጋሚ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችን ሲየመደርጉ ተስተውሏል። በ23ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ የነበረው አክሊሉ ዋለልኝ በቀጥታ ወደ ግብ አክርሮ መቶት ኳሷ የግቡን አግዳሚ ብረት ለትማ የወጣችው አሰደንጋጭ ሙከራ ነበረች።

በኳስ ቁጥጥር ረገድ ከጅማዎች በአንፃራዊነት የተሻሉ የነበሩት ፋሲሎች እድሎችን በመፍጠር ረገድ ተቀዛቅዘው ታይተዋል። ተጨማሪ ሙከራዎችን ያልተመለከትንበት የመጀመርያ አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡

የሁለተኛውን አጋማሽ ከሌላው ጊዜ በተለየ በጥሩ መነሳሳት ላይ የነበሩት ጅማዎች እስከ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድረስ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችለው ነበር። በ59ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ዲዲዬ ለብሪ ያሻገረውን ኳስ ማማዱ ሲድቤ በግንባሩ ሲገጨው ሚኬል ሲማኬ በጥሩ ብቃት ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ በድጋሚ ሞክሮ ፍጹም ከበደ መልሶበታል፡፡

ፋሲሎች በሁለተኛው አጋማሽ አንድም ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ አላደረጉም። እድሎችን ለመፍጠር የነበራቸው ተነሳሽነትም አነስተኛ ነበር። ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥርም ወደ ኃላ አፈግፍገው ለመጫወት መርጠዋል፡፡ ጅማዎች በአንፃሩ መስዑድን ቀይረው ካስገቡ በኃላ ከቀጥተኛ ኳሶች ይልቅ ኳስን መስርተው ተደጋጋሚ እድሎችን ለመፍጠር ቢችሉም ግብ ግን ማስቆጠር አልቻሉም።

በጅማ በኩል ከሚጠቀሱ እድሎች መካከል በ75ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ማማዱ ሲዲቤ በግንባሩ ገጭቶት በእለቱ ጥሩ የነበረው ሚኬል ሳማኬ እንደምንም ሲያወጣበት በ83ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን መስዑድ በደረቱ አብርዶ ለቢስማክ ቢሰጠውም የቢስማክ ሙከራ የግቡን ቋሚ ታኮ የወጣበት ይጠቀሳሉ።
ጨዋታው ያለጎል መጠናቀቁን ተከትሎ ፋሲል አንድ ደረጃ አሻሽሎ ወደ አራተኛ ከፍ ሲል የዙሩን የመጨረሻ ጨዋታ ወደ መቐለ ተጉዞ ሀሙስ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የሚያከናውነው ጅማ አባ ጅፋር የደረጃ ለውጥ ሳያደርግ ዘጠነኛ ላይ ተቀምጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *