አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በጅማ የሚገኙ የታዳጊ ማሰልጠኛዎችን ጎበኙ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የታዳጊዎች ማሰልጠኛዎች ላይ የሚያደርጉትን ጉብኝት በመቀጠል በጅማ ከተማ የእግርኳስ ፌዴሬሽን ጋባዥነት በከተማው የሚገኙ ታዳጊ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

ከ13፣ 15 እና ከ17 ዓመት በታች ታዳጊዎችን አቅፈው በመቀንሳቀስ ላይ ከሚገኙ ማሰልጠኛዎች መካከል በከተማው ለረጅም ዓመታት በታዳጊዎች ላይ ሲሰራ የቆየው ቁልቢ ተስፋ ፕሮጀክት፣ የተስፋ ስፖርት አካዳሚ አካል የሆነውና በኮሪያውያን እርዳታ የተደረግለት ጅማ ተስፋ፣ ጋሻው መኮንን ፕሮጀክት እንዲሁም ሶልጌት ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል። ከአሰልጣኙ ጋርም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ኮሚቴ አባል ከሆኑት ኢንስትራክተር አንተነህ እሸቱ በተጨማሪ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ደያስ አዱኛ እና የሙገር ሲሚንቶና የታዳጊ ቡድን አምበል የነበረው ሙሉጌታ ሽፈራው፣ የቡድን አጋሩ አበባው ጋሻው እንዲሁም የፋሲህ ከነመመው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በጉብኝቱ ላይ ተሳትፈዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ለታዳጊዎቹ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉበትን እድል ለማመቻቸት እንደሚሞክሩ የተናገሩት አሰልጣኝ አብርሀም በከተማ ደረጃም የከተማው እግርኳስ ፌዴሬሽን ለታዳጊዎቹ ውድድር እንዲያዘጋጅላቸው ምክረ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን ከታዳጊዎቹ በተጨማሪ ለአሰልጣኞቻቸው ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበትን መድረክ እንደሚያመቻቹ ገልፀዋል። እነዚህ ታዳጊዎች በእንደዚህ ዓይነት ደረጃ መገኘታቸው በከተማው ላሉ ክለቦች እንዲሁም ለሀገር ትልቅ ግብዓት እና አቅም እንደሚሆን ገልፀው ከእግርኳሱ ጎን ለጎን ለትምህርታቸውም ትኩረት እንዲሰጡ እና ደረጃ ውስጥ ገብተው ለሚያጠናቅቁ ተማሪዎች በዓመቱ መጨረሻ በግላቸው ሽልማት እንደሚያበረክቱላቸው ቃል ገብተውላቸዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *