ለኢትዮጵያ ቡና ችግሮች የመፍትሔ ሀሳቦች ለማቅረብ የተቋቋመው ኮሚቴ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ

ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ያሉበትን ችግሮች ለመለየት እና የመፍትሔ ሀሳቦችን በጥናት በተደገፈ መልኩ እንዲያቀርብ የተቋቋመው ኮሚቴ ትናንት የሚዲያ አካላት በተገኙበት በሂልተን ሆቴል ከ09:00 ጀምሮ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰቷል።

ሰብሳቢው አቶ መንግስቱ ታደሰን ጨምሮ ተዋናይ ደበሽ ተመስገን አቶ የሱፍ ከድር፣ ዶ/ር ዳንኤል እና አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው በተገኙበት በዚህ መግለጫ የመክፈቻ ንግግር ያደረገው ደበሽ ተመስገን ይህ ኮሚቴ በ2010 በክለቡ የቦርድ አመራሮች እውቅና ተሰጥቶት አስር አባላት ያሉበት ኮሚቴ ከክለቡ በደረሰ ደብዳቤ እንደተመረጡ ገልጿል። ጥናቱ ብዙ አድካሚ ብዙ ጊዜ የወሰደ ለክለቡ ችግር በመሰረታዊነት መፍትሄ ያመጣል ተብሎ እንደተጠና እና አሁን ጥናቱ ተሰርቶ ሲያልቅ ብዙ ውስብስብ ችግሮች እንዳጋጠሙት አብራርቶ የጥናቱ አጠቃላየይ ዝርዝር ነገሮች ሌሎች አባላት እንዲያቀርቡ በመጋበዝ ሀሳቡን አጠቃሏል።

በመቀጠል የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መንግስቱ ታደሰ ንግራቸውን አስከትለው ኮሚቴው በአጭር እና ረጅም ጊዜ የክለቡ ውስብስብ ችግሮችን በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ለማምጣት መመረጣቸውን ገልፀው፤ ይህ ኮሚቴ በተዋቀረበት ወቅት ዓምና በቡድኑ ውስጥ ከተጫዋች ቅጣት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮችን አጣርቶ መፍትሔ በመስጠት ስራውን እንደጀመረ ተናግረዋል። ” የኋላ ኋላ ግን ጥናቱን እያጠናቀቀ ሲመጣ እና ወደ ትግበራ መገባት እንዳለበት እያሳወቅን ስንመጣ ችግሮች እያጋጠሙን በመምጣታቸው ይህን ጥናት የደረሰበትን ድምዳሜ ለማቅረብ የተለያዩ መድረኮች እንዲመቻቹልን ብንጠይቅም የክለቡ ቦርድም ሆነ የደጋፊ ማኅበሩ ሊያመቻችልን ባለመቻሉ ይህን ጋዜጣዊ መግለጫ ለመጥራት ተገደናል” በማለት ንግራቸውን ቋጭተው ጥናቱ ያተኮረባቸውን ዝርዝር ሁኔታዎችን አቶ ቴዎድሮስ በስፋት እንዲያቀርቡ መድረከ ለቀዋል።

በጥናቱ በመጀመርያ የክለቡ የመዋቅር አደረጃጀት ችግሮች ላይ ያተኩራል በማለት ጥናት አቅራቢው ለክለቡ ችግሮች መፍትሄ ይሆናል ያሉትን ሀሳብ እንዲህ አቅርበዋል።

-ክለቡ እየተመራበት ያለው አደረጃጀት ከዓለም አቀፍ እግርኳስ መርህ አንፃር ብዙ ክፍተቶች አሉበት። የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ዋንኛ ሀብቱ ደጋፊው ነው። ክለቡ በዓመት ከተለያዩ መንገዶች ከማልያና ቁሳቁስ ሽያጭ፣ ከስታዲየም ገቢ ፣ ከቴሌቭዥን ማስታወቂያ ስፖንሰር እና ከቡና ላኪዎች ማኅበር ከሚገኘው ጠቅላላ ገቢ 58 በመቶው የሚሆነው የሚገኘው ከደጋፊዎች ነው። ሆኖም በክለቡ የውሳኔ ሰጪነት ሚናው እና በቦርዱ ያለው ውክልና በድምፅ 3 ሰዎች ብቻ ናቸው። በመቶኛ ሲሳላ ውሳኔ የመሰጠት አቅሙ 10% አይሞላም። ይህ ተገቢ አይደለም፤ የክለቡ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ደጋፊው ሆኖ ሳለ ደጋፊው ስራው ክለቡን መደገፍ ብቻ ነው ሊባል አይገባም። የውሳኔ ሰጪነት ሚናው በቦርዱ ድምፁ ሊጨምር ይገባል። ይህ በሌሎች ሀገሮች ባርሴሎና ፣ ሪያል ማድሪድ ፣ ማንችስተር ዮናይትድ ደጋፊዎች የክለቦቹ ትልቁ ገቢ ናቸው። ስለሆነም የውሳኔ ሰጪነታቸውም ከፍተኛ በመሆኑ ክለቡን ያስተዳድራሉ ስለዚህ በኢትዮጵያ ቡናም ባቀረብነው ጥናት መሰረት ደጋፊው በቦርድ ውስጥ የውሳኔ ሰጪነቱ አሁን ካለው በተሻለለ ወደ 6 ድምፅ ከፍብሎ በመቶኛ ሲሰላ 55% ማደግ አለበት የሚል መፍትሔ አቅርበናል።

-አሁን ያለው የጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊ ብዛት 46 ሲሆን ደጋፊው በሦስት ሰዎች ብቻ ነው የሚወከለው። አሁን ባደረግነው ጥናት እንደ መፍትሄ ያስቀመጥነው የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ቁጥር ከ40 ወደ 60 እንዲያድግ እና ከጠቅላላው ጉባኤው 60 ወንበሮች ውስጥ 24ቱን ደጋፊው እንዲይዝ በጥናቱ ላይ አቅርበናል።

-በጠቅላላ ጉባዔው ላይ አንድ ድምፅ ያለው ከፍተኛ ስፖንሰር አድራጊው ድርጅት የጥቅም ግጭት የሚፈጥር በመሆኑ ድምፅ ከመስጠት ወጥቶ በክብር አባልነት በጉባዔዎች ላይ ብቻ እንዲሳተፍ ሀሳብ አቅርበናል። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ቡና የአመራር ችግሮች ያሉበት ክለብ ነው። ከገቢ የማመንጨት አቅም ፣ የደጋፊው አስተዳደ ልማት ፣ የህዝብ ግኑኝነት የመሳሰሉት መስተካከል እንደሚገባቸው ጠቁመናል።

-በሌላ በኩል ትልቁ ሙግት እና ፍጭት በጠቅላላ ጉባዔ እና በቦርዱ መዋቅሮች ከቡና አልፎ የሀገሪቱን ስፖርት ሊለውጡ የሚችሉ ሀሳቦች ሊነሱባቸው ይቅርና ምልዓተ ጉባዔ መሟላታቸው አለመሞላታቸው በቅጡ የማይታወቅባቸው ጉባዔዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። በተጨማሪ በቦርዱም ሆነ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ከተለያዩ የቡና ላኪዎች ተወክለው የሚመጡት ግለሰቦች ምንም የእግርኳስ እውቀት የሌላቸው፣ በብዛት በቦታው የማይገኙ በመሆናቸው ሀሳቦች ሳይንሸራሸሩ እና የሀሳብ ፍጭት ሳይደረግባቸው በአንድ እና ሁለት ሰዎች ሀሳብ ብቻ ውሳኔ እየተሰጠባቸው ያለፉ ጠቅላላ ጉባዔዎች መቅረት ይገባቸዋል። ለክለቡ ዕድገት መፍትሄ አመንጪ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት የሚታደሙበት አደረጀጀት ሊኖረው ያስፈልጋል።

-ከሁሉም በላይ ህዝብ የስፖርቱ መሰረት ነው ካልን በተለይ በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ያለውን እውቀት ፣ ገንዘብ ፣ የአመራር አቅም መጠቀም ከቻልን አፍሪካ ውስጥ ካሉ አምስት ትልልቅ ክለቦች መካከል አንዱ መሆን ይችላል። በማለት ይህን ደጋፊ በቅድሚያ በክለቡ ላይ ያለውን የባለቤትነት ስሜት ከፍ በማድረግ በሙሉ አቅሙ ሊሳተፍ ካልቻለ ወደፊት በክለቡ ጉዞ ላይ ከባድ ፈተና እንደሚሆን አቶ ቴዎድሮስ በጥናታቸው አቅርበዋል።

በመቀጠል ከጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው የኮሚቴው አባላት የሰጡትን ምላሽ እንዲህ አቅርበነዋል።

ደጋፊው በከፍተኛ ሁኔታ በተለያዩ መንገዶች ተቋውሞዎችን በማድረግ በክለቡ ላይ እጁን እያስገባ ባለበት ወቅት ተጨማሪ ይህ ከፍተኛ ድምፅ እንዲያገኝ ማድረግ የበለጠ ተፅእኖ እንዲፈጥር አያደርገውም?

-ውጤት ሲጠፋ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞ የሚነሳው በአግባቡ የተደራጀ የደጋፊ ማኅበር ባለመኖሩ ነው። የደጋፊውን ድምፅ የሚያሰማለት የወከለው ሰው ቢኖር አሁን በስቴዲየም የምንመለከተው ተቋውሞ አይኖርም። ደጋፊው በግሉ ቅሬታውን የሚያሰማው በደንብ ከተደራጀ ጥያቄውን የሚያቀርብለት መሪ ስላጣ ነው። ድምፁን የሚያሰማበት መድረክ ከተመቻቸለት በተደራጀ ሁኔታ ክለቡ ከተመራ ይህን ወደ መልካምነት መቀየር ይቻላል። ደጋፊ ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ከጠራ እንኳን ዓመታት አልፎታል። ይህ ደግሞ ደጋፊው ድምፁን ለማሰማት እድል ካለማግኘቱ የመጣ እንጂ በቦርዱም ሆነ በጠቅላላ ጉባኤው ድምፁ እንዲጨምር መደረጉ እና የውሳኔ ሰጪነት ሚናው ከፍ ማለቱ አቅሙን ከመጨመር ውጭ ችግር አይኖረውም ።

ጥናቱን አጠናቆ ለማቅረብ ለምን ዘገያቹ ?

አዎ ዘግይተናል። ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ከክለቡ በኩል የምንፈልጋቸውን መረጃዎች በፍጥነት አናገኝም ነበር። የቦርዱን እና የደጋፊ ማኅበሩን አመራሮች ለማግኘት የነበረን ጥረት በእነርሱ በኩል ፍቃደኝነት ስላልነበረ ለመዘግየቱ ምክንያት ሆኗል እንጂ እኛ ጥናቱ ካጠናቀቅን ቆይተናል። በመጨረሻም የደረስንበትን ድምዳሜ ለደጋፊው ማሳወቅ ስለሚገባን ነበር ወደ እናንተ (ሚዲያ) መምጣት ያስፈለገን።

ከክለቡ የቦርድ አመራር እና የደጋፊ ማኅበሩ ጋር ተቀራርባችሁ ሰርታችኋል ?

እንደሚታወቀው በክለቡ እውቅና ተሰጥቶት የተቋቋመ ኮሚቴ ነው። ስራውን የጀመርን አካባቢ ተቀራርቦ የመስራት ነገሮች ነበሩ። በኋላ ላይ ግን ጥናቱን ወደ ማጠናቀቂ ላይ ስንደርስ የምናቀርባቸውን ጥያቄዎች እና ሰነዶችን የማዘግየት ነገሮች ተከስተዋል። ይህንን ጥናት አወያይተን በሀሳብ አዳብረን ለመምጣት ፈልገን ደጋፊውን ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ለማግኘት በምንሞክርበት ወቅት የማዘግየት ችግሮች አጋጥመውናል።

ጥናቱ የክለቡ አደረጃጀት ብቻ ላይ ለምን አተኮረ? በክለቡ ዙርያ ሌሎች ችግሮችን የሉም ማለት ነው?

በጥናታችን ብዙዎቹን የክለቡን ችግሮች ላይ በጥልቀት ሄደንበታል ለምሳሌ የማርኬቲንግ ክፍሉ ፣ የደጋፊ አየያዝ ፣ የአሰልጣኝ የተጫዋች አመጣጥ ሌሎች ዝርዝር ችግሮችን ተመልክተናል። ሆኖም የእነዚህ የክለቡ ችግሮች መነሻው አስተዳደራዊ እና የአደረጃጀት ችግሮች እንደሆኑ ለማወቅ ችለናል። የክለቡን አወቃቀር ማስተካከል ከተቻለ ሌሎች በጥናታችን ያካተትናቸው ችግሮች ይፈታሉ የሚል እምነት አለን። ለዚህም ነው ጥናታችን በዋናነት የክለቡ የአወቃቀር አደረጃጀት መስተካከል አለበት ብለን የመፍትሄ ሀሳብ ያቀረብነው።

የክለቡ የቦርድ እና የደጋፊ ማኅበሩ ይህን ጋዜጣዊ መግለጫ ያውቁታል?

አዎ ያውቁታል። እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ የደጋፊ ማኅበሩ ፕሬዝደንት እንደሚገኙ ነግረውናል። ይህም ጋዜጣዊ መግለጫ በእነርሱ እንደሚጠራ እና ኃላፊነቱን ፕሬዝደንት ክፍሌ አማረ እንደሚወስድ አሳውቆን የነበረ ቢሆንም ሊገኙ አልቻሉም። ይህ እነርሱ ሊመልሱት የሚገባ ጥያቄ ነው። ክለቡ እንደሚያውቀው የሚያሳየው ደግሞ ከሁላችሁም ሚዲያ ቀድሞ በሰዓቱ የተገኘው የኢትዮጵያ ቡና የሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ባለሙያዎች ናቸው።

ይህ የመፍትሄ ሀሳባቹ ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነ በቀጣይ ምን የማድረግ ሀሳብ አላቹ?

ይህ ለእኛ የመጨረሻ ነው። ከዚህ በኋላ ብዙ የመቀጠል ሀሳብ የለንም ። ለክለቡ ይጠቅማል ያልነውን የመፍትሄ ሀሳብ ብዙ ጊዜ ወስዶብን አቅርበናል። ይህ ተግባራዊ እንዲሆን የሚፈልግ አመራር እና ደጋፊ ካለ የእነርሱ ፈንታ ነው። እኛም እንደ ማንኛውም ደጋፊ ባለን ጊዜ ክለቡን ወደ ተሻለ ቦታለ ማድረስ አብረን እንሰራለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *