የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቅጥር ጉዳይ እያነጋገረ ይገኛል

ለኦሊምፒክ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ ለመወዳደር የመጨረሻ ፈተና የደረሱት ተፈታኞች የቴክኒክ ኮሚቴው ጥሪ ተቀብለው ለመፈተን ቢመጡም ፈተናው ወደ ሌላ ቀን መራዘሙን ተነግሯቸው ተመልሰዋል።

ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ቅድመ ማጣርያ ከዩጋንዳ ጋር ጨዋታ ለሚጠብቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመቅጠር መስፈርት አውጥቶ ያወዳደረው የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ አራት አሰልጣኞችን ለመጨረሻ የቃል እና የጽሑፍ ፈተና ሰኞ ጠርቶ እንደነበረ መዘገባችን ይታወቃል። ሆኖም የሰኞው ፈተና ወደ ዛሬ ተቀይሮ ከአራቱ አሰልጣኞች መካከል ሰርካዲስ እውነቱ (ጥረት)፣ መሠረት ማኒ (አዲስ አበባ) ፣ ሠላም ዘርዓይ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ለፈተና በአዲስ አበባ ስታዲየም ቴክኒክ ኮሚቴ ቢሮ ቢገኙም ፈተናው ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል ስንጠራችሁ ትመጣላቹ ተብለው መመለሳቸውን ሰምተናል።

የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን ከዩጋንዳ ጋር በመጋቢት ከ23 እስከ መጋቢት 30 ባሉት ቀናት በደርሶ መልስ እንደሚካሄድ እየታወቀ ከወዲሁ አሰልጣኝ በመቅጠር እና ተጫዋቾችን በመምረጥ እና በቂ ሁኔታ ዝግጅት መጀመር እየተገባ የቴክኒክ ኮሚቴው የፈተናውን ቀን እንዲራዘም ማድረጉ አነጋጋሪ የሆነ ሲሆን ስለ ፈተናው መራዘም በምክንያትነት የተገለፀ ነገር ባይኖርም በቴክኒክ ኮሚቴው ላይ ጥያቄ እንዲነሳበት አድርጓል።

በተያያዘ ዜና ከአራቱ የመጨረሻ እጩዎች መካከል አሰልጣኝ ህይወት አረፋዓይኔ (መቐለ ሰባ እንድርታ) ራሷን ከውድድሩ እንዳገለለች ለማወቅ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *