የዳኞች እና የጨዋታ ታዛቢዎች ስልጠና እና ግምገማ ተጠናቀቀ


የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አደኛው ዙር አጋማሽ የፕሪምየር ሊግ ሴት እና ወንድ ዳኞች እንዲሁም የጨዋታ ታዛቢዎች ስልጠና እና የአፈፃፀም ግምገማ በትላንትናው ዕለት በኢትዮጵያ ሆቴል ተካሂዷል።

በሦስት ምዕራፍ ተከፍሎ ከማለዳው ጀምሮ እስከ ምሽት 11:00 በተካሄደው በዚህ መድረክ የጠዋቱ መርሐግብር ለሚዲያ ዝግ የነበረ ሲሆን የፌዴሬሽኑ አመራሮች ፣ የጨዋታ ታዛቢዎች እና የፕሪምየር ሊግ ዳኞች በተገኙበት በጋራ ሰፊ ግምገማ ተደርጓል። ከዚህ በማስከተል የኢትዮጵያውያን በሆኑ የካፍ ኢንስትራክተሮች አማካኝነት ለጨዋታ ታዛቢዎች እና ዳኞች የስነ ልቡና እና በጨዋታ ህጎች ዙርያ ጥልቅ የሆነ ስልጠና ተሰጥቷል።

በመቀጠል ለሚዲያ ክፍት በነበረው የከሰዓት ውሎ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ፣ የስራ አስፈፃሚ አባል እና የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ፣ የጽህፈት ቤት ኃላፊው ዶ/ር ኢያሱ መርሐፅድቅ እንዲሁም የጨዋታ ታዛቢዎች እና ዳኞች በተገኙበት የጥያቄ እና መልስ ውይይት ተካሂዷል።

አቶ ኢሳያስ ጅራ የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ በኋላም በቀጥታ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ጥያቄ እና አስተያየት እንዲሰጡ ዕድል ተሰጥቷል።

የካፍ ኢንስትራክተር ፍቃዱ ግርማ

በጣም ጠቃሚ የሆነ ግምገማ አድርገናል ። በግምገማችንም በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ የውጤት ማስቀየር እንዳለ ከድምዳሜ ላይ ደርሰናል። ለዚህም እንደ ምክንያት ያቀረብነው በሀገራችን የእግርኳስ ቁማር በእጅጉ እየበረከተ መምጣቱን ነው። በተለይም ሁሉ ስፖርት የሚባለው በስቴዲየም ቢልቦርድ በመስቀል እየተንቀሳቀሰ ያለው ድርጅት ምክንያት በመሆኑ እዚህ ላይ ማስተካከያ ቢደረግ።

ዳኛን ብቻን ማሰልጠን በቂ አይደለም በስፖርቱ የሚገኙትን ባለድርሻ አካላት ሁሉ ማስተማር ይገባል። ፌዴሬሽኑ በቀጣይ አስገዳጅ በሆነ መንገድ በተዋረድ ሰልጠና መሰጠት አለበት።

ኮሚሽነር ተስፋዬ ኦሜጋ

ሊግ ኮሚቴ ኮሚሽነር ሲመደብ ዳኞች ኮሚቴም የመደባቸውን የጨዋታ ዳኞች ሲመድብ ቀደም ብለን አለመነጋገራችን በስራው ላይ መንጠባጠብ ፈጥሯል ይህ ቢስተካከል።

ቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ብዙ ችግሮች እየተፈጠረበት በመሆኑ እዚህ ላይ በጣም መታሰብ አለበት።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ወይም ስራ አስፈፃሚው አመራሮች በተለያዩ ስታድየሞች በድንገት ይገኛሉ። ይህ መታረም ይገባዋል። የሚገኙ ከሆኑ ቀድመው ለጨዋታው ታዛቢ ማሳወቅ ቢችሉ ክፍተት እየፈጠረ በመሆኑ።

ኮሚሽነር ፍስሃ ገብረማርያም

በየሜዳው የምንመለከተው ነገር አስጊ ሆኗል ፤ የጨዋታ አቅጣጫ እየተቀየረ ነው። የፀጥታ አካላት ለከተማ ክለባቸው ወገንተኛ እየሆኑ ያለው። ጨዋታዎች በፖለቲካ አስተዳደር የሚቀየሩበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው እግርኳሱን በነፃነት መምራት የምንችለው ? ዳኞች ጫና ውስጥ ናቸው ፤ መስዋትነት እየከፈሉ ነው። ከዚህ በላይ እግርኳሳችን እንዳይሄድ ከመንግስት ጋር መነጋገር አለባቹሁ።

ፌደራል ዳኛ ቦጋለ ይልማ

ተመድቦ የተቀየረ ዳኛ የለም ፤ ይህ ጥሩ ስራ ነው። ለዳኞች የሚሰጠው አበል በባንክ መሆኑ ጥሩ ሆኖ ሳለ ሄድን ጨዋታዎችን መርተን ከጨረስን በኋላ ነው የሚከፈለን ይህ ቢስተካከል።

የኮከብ ዳኝነት ምርጫ ለኢንተርናሽናል ዳኞች ብቻ መሆኑ ለምድነው? ፌደራል ዳኞች ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፉትን እየሸለመ አይደለም። መስፈርቱ ፌደራል ዳኛን አያማክልም እና ቢታሰብበት።

ፌዴራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ

የዳኛ አመዳደብ ላይ ወቅቱ የወለደው የፖለቲካ ትኩሳት ተፅዕኖ አድርጎብናል ቢስተካከል። በአንደኛው ዙር ውስጥ ሦስት ጨዋታ ብቻነው ያጫወትኩት። አቅሜ እንዴት ነው ማሳደግ የምችለው ? አንድ ዳኛ የሚያድገው አቅሙ ከፍ የሚለው ብዙ ጨዋታ ባገኘ ቁጥር ልምድ እያገኘን ሲሄድ በመሆኑ በሁለተኛው ዙር ይህ ቢስተካከል።
ሌላው የሚራዘሙ ጨዋታዎች ሲኖሩ የተመደብን ዳኞች ሌላ ጨዋታ ማግኘት አለብን መተኪያ ጨዋታ እየተሰጠን አይደለም።

ዳኞች እና ኮሚሽነሮች ሲያጠፉ የሚወሰደው እርምጃ ጥሩ ነው። ሆኖም ግን ዳኞች ላይ ጥርስ እየወለቀ ፣ ጥፊ እየተሰነዘረ ፣ የውሀ መያዣ ፕላስቲክ እየተወረወረ እኛ ዳኞች በግልፅ ሪፖርት እየፃፍን የጨዋታ ታዛቢዎች በዝምታ እያለፉ ነው።

ፌደራል ዳኛ ፋሲካ የኃላሸት

ግምገማ መደረጉ ጥሩ ነው። ሆኖም ግምገማው ግልፅ አይደለም። እከሌ እከሌ እየተባለ በግል መገምገም መቻል አለበት መተራረም እንዲኖር በሁለተኛው ዙር እራሳችንን እንድናስተካክል።

ስልጠናው የተፃፉ ነገሮች ላይ ብቻ ነው እያተኮረው ያለው ለምን ? በቪዲዮ እና ሜዳ ላይ በተግባርም አንማማር።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ክንዴ ሙሴ

አሁንም ሜዳ ላይ የቴክኒክ ክስ መቆም አልቻለም ይህ መስተካከል አለበት። ኤርትራ ተልከን ከሀገር ውጭ አጫውተናል መጥተናል ሆኖም እስካሁን አልተከፈለንም ለምን ? ዳኝነት ስራ ነው። ክፍያውን የምትፈፅመው ኤርትራ ናት ወይስ ኢትዮጵያ ? ይህን ማወቅ እንፈልጋለን። የዳኘነው በእርዳታ ከሆነ አርፈን ቤት እንቀመጣለን።

ከዚህ ቀደም ለወዳጅነት ጨዋታ 300 ዶላር ነበር አሁን 900 ብር ሆናል ለምን ?

በቀረቡት ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ዙርያ የሚከተሉት ምላሾች ተሰጥተዋል። 

አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ

የዳኝነት አመዳደብን በተመለከተ ያው የምታቁት ነገር ነው። ከአቅም በላይ ችግር ነው። ወቅታዊ አቋምን መሠረት ያደረገ ምድባ እናካሂዳለን ሆኖም በፖለቲካ የመጣን ነገር ምንም ልናደርገው አንችልም። በሁለቱ ክልሎች እንዲሁም ደቡብን ጨምሮ ችግሮች አሉ ይህን በሂደት እያስተካከልን እንመጣለን። በሁለተኛው ዙር ምደባ በብቃት እንጂ በኮታ አናደርግም።

ቅድመ ጨዋታን አስመልክቶ ባለፈው ከክለቦች ጋር ባደረግነው ውይይት ትክክለኛና ተገቢ ሰው ላኩልን ብለን አስረግጠን ተናግረናል። ለዳኞች ኮሚሽነር በቂ የሆነ ከለላ ስጡ ብለናል። ሁለተኛው ዙር ይህ ተግባራዊ ካልሆነ ዳኞች ኮሚሽነሮች ሪፖርት ካቀረባችሁልን እኛ እርምጃ እንወስዳለን። ማን ይተግብረው አይተግብረው በቀጣይ እናየዋለን።

የጨዋታ መላቀቅ አስመልክቶ መንግስት እውቅና የሰጠውን አካል አያስፈልግም እርሱ ነው ምክንያቱ ማለት ለእኔ አይመጥነኝም። ቁማር ቢኖር ባይኖር እኛ ራሳችንን እንፈትሽ። በመንግስት ህጋዊ ዕውቅና ተሰጥቷቸው እየሰሩ ነው። እውነታው ይሄ አይደለም የጨዋታ መላቀቅ ዛሬ እኮ አይደለም የተጀመረው ምክንያት ከማቅረብ ወጥተን ተጋግዘን እንስራ ዳኞች ኮሚሽነሮች በታማኝነት እንዲያገለግሉ እናድርግ። ውስጣችንን እንፈትሽ።

ክለቦች በባለፈው ስብሰባ ዳኝነትን አድንቀዋል። የእኛ ችግር ነው ከዚህ በኋላ እናስተካክላለን ብለዋል። ስለዚህ ይህ አያኩራራን የበለጠ የሚቀሩንን ነገሮች አሉ እያስተካከልን እንሂድ።

ክፍያን በተመከተ ብዙ ለውጦች አሉ ከዚህ ቀደም እንዴት ይሰራ እንደነበረ ታውቁታላችሁ። አሁን ለውጥ አለ ሆኖም ተጉላልታችኋል። ወደ ትክክለኛው አሰራር እየገባን ስለሆነ ትንሽ ታገሱን።

አቶ ኢሳይያስ ጅራ

ከምስጋና ልጀምር በአንደኛው ዙር ላይ የነበረው የዳኝነት ሂደት ጥሩ ነው ግን የሚያኩራራ አይደለም ከነ ክፍተታችን ምስጋናው ይደረሳችሁ።

ኮሚሽነሮች ዳኞችን ምትመዝኑበትን መንገድ በደንብ ፈትሹ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስም በመልካምም ሆነ በክፉ የምታስጠሩት እናንተ ናችሁ። ጫና አለባችሁ ግን ይህን በአዕምሮ ተዘጋጅታችሁ በብቃት ለመወጣት ጠንክራችሁ ማንበብ መስራት አለባችሁ።

የምንዞረው በየጨዋታዎቹ ያለውን ሂደት ለመቆጣጠር ነው። እንደ ክፍት አትዩት በቀጣይ የፕሮቶኮል ጉዳይ ነው እናሳውቃለን። በበጎው እንወስደዋለን ተቀብለናል።

እግርኳሳችን በጎጠኝነት ተይዟል የአማራ ዳኛ ፣ የትግራይ ዳኛ ፣ የኦሮሞ ዳኛ እየተባ ይነገራል። ይህ ለእግርኳሳችን ምድነው የሚጠቅመው ? ይህ መስተካከል አለበት።

በሁለተኛው ዙር የተሻለ ነገር ለመስራት ለሙያችሁ ታማኞች ሁኑ ዳኝነትን አስከብሩ።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ አባል እና የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በጆሳምቢን ስፖርት ድርጅታቸው ስም 400 ሺህ ብር የሚያወጡ የዳኞች ትጥቆችን በስጦታ አበርክተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *