ኦሊምፒክ ቡድኑ በአቋም መለኪያ ጨዋታ ሲሸልስን አሸነፈ

ከሲሸልስ ዋና ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደረገው የኢትዮጵያ ከ 23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአቡበከር ናስር ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ችሏል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ በደረሰው አስደንጋጭ አደጋ ለሞቱት ወገኖች በተደረገው የህሊና ፀሎት የጀመረው ጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ብልጫ የታየበት ነበር። በጨዋታው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበረው ቡድኑ ግብ ለማስቆጠር ብዙም ደቂቃ አልፈጀባትም ፤ በ20ኛው ደቂቃ አቡበከር ናስር ከአፈወርቅ ኃይሉ የተሻገረችነትን ኳስ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ኢትዮጵያን መሪ ማድረግ ችሏል። እንደወሰዱት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል መድረስ ያልቻሉት የኦሊምፒክ ቡድኑ ተሰላፊዎች ምንም እንኳ ወደ ራሱ ሳጥን ተጠግቶ እና በመስመሮች መካከል ያለውን ክፍተት አጥብቦ መከላከልን የመረጠውን የሲሸልስን የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ብዙ የግብ ዕድሎች ባይፈጥሩም የግቡን ልዩነት ማስፋት የሚችሉባቸው ዕድሎች ፈጥረው ነበር።

በተለይም አቡበከር ናስር ከመስመር በጥሩ ሁኔታ አሻምቶት አፈወርቅ ኃይሉ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ እና አፈወርቅ በጥሩ ሁኔታ አሻግሮት እስራኤል እሸቱ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።
ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም እስራኤል እሸቱ አቡበከር ናስር በጥሩ ሁኔታ በረጅሙ ያሻማለትን ኳስ አብርዶ ለአፈወርቅ አቀብሎት አማካዩ ወደ ጎል ያልቀየረው ኳስ ለግብ የቀረበ ነበር። በጨዋታው በእንቅስቃሴ የተሞላውን የኢትዮጵያን የማጥቃት አጨዋወት ለማቆም ከተከተሉት ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ውጭ ይህ ነው የሚባል የጥሩ ጎን ያልነበራቸው ሲሸልሶች ከቆሙ ኳሶች ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጭ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ አንድም ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በተለይም ተጋጣሚያቸው ከኳስ ውጭ የሚፈጥራቸውን ጫናዎች ( pressing) ተቋቁመው መቀባበል ያልቻሉት እንግዶቹ በጨዋታው ጥሩ የኳስ ፍሰት ማሳየት አልቻሉም። በዚህም ጎዲ ሜላኔ ከቅጣት ምት አክርሮ መቷት ምንተስኖት አሎ በጥሩ ብቃት ካወጣበት ሙከራ እና ራሱ ጎዴ ሜላኔ ከርቀት መትቶ በምንተስኖት እጅ ሾልካ ወደ ውጭ ከወጣችው ሙከራ ሌላ ግልፅ የማግባት ዕድል አልፈጠሩም።

በሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 11 ተጫዋቾች ቀይሮ ነበር ወደ ሜዳ የገባው በዚህም ተክለማርያም ሻንቆ ፣ ዳዊት ወርቁ ፣ ፈቱዲን ጀማል ፣ እንየው ካሳሁን ፣ ሸዊት ዮሃንስ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ ፣ የአብስራ ተስፋዬ ፣ ቴድሮስ ታፈሰ ፣ ሐብታሙ ገዛኸኝ ፣ ፍቃዱ ወርቁ እና በረከት ደስታ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር የተሻለ ፉክክር የታየበት እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተሻለ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የደረሰበት ሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ሙከራዎች የታዩበትም ነበር። ሀብታሙ ገዛኸኝ ባደረጋት ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ባለሜዳዎቹ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ብቻ እንኳን ሁለት ንፁህ የግብ ዕድሎች አምክነዋል። በተለይም እንየው ካሳሁን በጥሩ ሁኔታ አሻምቷት ሀብታሙ ገዛኸኝ ያልተጠቀመባት ኳስ የኢትዮጵያን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

ሲሸልሶሽ በመጀመርያው አጋማሽ የነበራቸው ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ማስጠበቅ ያልቻሉት ሲሆን በዚህም ብዙ የግብ ሙከራዎች ለማስተናገድ ተገደዋል።
ኢትዮጵያዊያኑም ከግብ ጠባቂ ጀምሮ ኳስ መስርተው ወደ ተጋጣሚ ክልል ለመግባት የተጠቀሙት አጨዋወት በተደደጋጋሚ የጎንዮሽ ኳሶች የታጀበ በመሆኑ የቡድኑ የማጥቃት ሽግግር ዘለግ ያለ ጊዜ እንዲወስድ ቢያደርገውም በርካታ ባይሆኑም ተጨማሪ የግብ ዕድሎች ከመፍጠር ግን አልቦዘነም።

በዚህም እዮብ አለማየሁ ከግቡ ቅርብ ርቀት ሆኖ መትቶ ወደ ውጭ ያወጣው እና በረከት ደስታ ከመሃል ሜዳ የተሻገረለት ኳስ ብበመጠቀም ግብ ጠባቂውን አታሎ መትቶ ተከላካዩ ዮኒክ ማሎ ከመስመር የመለሰው ኳስ በኢትዮጽያ በኩል ከታዩት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ሲሸልሶችም በአንፃራዊነት ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት አጨዋወት ቢያሳዩም እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ከቆሙ ኳሶች ብቻ ነው የግብ ዕድል የፈጠሩት ፤ በዚህም ሮዲ ሜላኔ በጥሩ ሁኔታ ከቅጣት ምት መትቶ ተክለማርያም ሻንቆ ያወጣው እና ጀርቪስ ዋያቲቬ ከቅጣት ሞክሮ በድጋሜ ተክለማርያም ሻንቆ በጥሩ ብቃት ያወጣው እንግዶቹ ከፈጠሯቸው ዕድሎች የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

በጨዋታው ተጨማሪ ግብ አለመቆጠሩን ተከትሎም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን 1-0 አሸንፎ ወጥቷል።

የአቋም መለኪያ ጨዋታው በመጪው ቅዳሜም የሚደገም ሲሆን የኢትዮጵያን ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን በድጋሜ ከሲሸልስ ዋናው ብሄራዊ ቡድን ጋር የሚጫወት ይሆናል። በዕለቱም የስታድየም መግቢያ ነፃ መሆኑ ታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *