ሀዋሳ ከተማ ሶስት ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን አሳደገ

ሀዋሳ ከተማ በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውጤታማ ቆይታ የነበራቸው መስፍን ታፈሰ እና ምንተስኖት እንድሪያስን እንዲሁም ግብ ጠባቂውን ምንተስኖት ጊንቦን ከ20 ዓመት ቡድኑ ወደ ዋናው አሳድጓል፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ወጣቶችን በማሳደግ አውራ የሆነው ሀዋሳ ከተማ ያለፉትን አምስት ዓመታት ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ያደጉ ያሳደጋቸው 17 የሚደርሱ ተጫዋቾችን ልምድ ካላቸው ጋር በማዋሀድ በመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመሪዎቹ ተርታ መሰለፍ የቻለው ክለቡ አሁን ደግሞ በተለያየ ጊዜ በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጠርተው ሲጫወቱ ከነበሩት በተመሳሳይ ዕድሜያቸው 18 የሆኑ   ሶስት ተጫዋቾችን ከሁለተኛው ዙር ጀምሮ ለመጠቀም በማሰብ ወደ ዋናው ቡድን አሳድጓል፡፡

ካደጉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ አጥቂው መስፍን ታፈሰ ነው። በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የእግር ኳስ አካዳሚ (ዛማ) የተገኘውና ባሳለፍነው አመት ብሩንዲ በተዘጋጀው ከ17 ዓመት በታች የዞን የሴካፋ ሀገራት ውድድር ላይ  ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ኢትዮጵያ ሶማሊያን 4-1 ስትረታ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ተስፋ ከተጣለባቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር። ተጫዋቹ ምንም እንኳን በሶማሊያው ጨዋታ ላይ ተሰልፎ መጫወት ቢችልም በፓስፖርት ስህተት ምክንያት ከውድድሩ ውጪ መሆኑ ቢታወስም በ2010 የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ላይ 16 ግቦችን በማስቆጠር በኮከብ ግብ አግቢነት እና ተጫዋችነት ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ዘጠኝ ግቦችንም ማስቆጠር ችሏል።

ሌላኛው ወደ ዋናው ቡድን ያደገው ምንተስኖት እንድሪያስ ሆኗል፡፡ አምና የክለብ ህይወትን በሀዋሳ ከ17 ዓመት በታች ቡድን በመጫወት የጀመረው ምንተስኖት በቅርቡ ለኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተመርጦ በሴካፋ ሀገራት ውድድር ታንዛኒያ ላይ እስከ ፍፃሜው በተጓዘው ቡድን ውስጥ ውጤታማ እንቅስቃሴ በማድረግ 8 ግቦችን አስቆጥሮ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ያጠናቀቀ ሲሆን ዘንድሮ በሀዋሳ 20 ዓመት በታች ቡድን ሲጫወት ቆይቷል፡፡

ሶስተኛው ያደገው ተጫዋች ግብ ጠባቂው ምንተስኖት ጊምቦ ነው። ይህ ግብ ጠባቂ ከመስፍን ታፈሰ ጋር በብሩንዲው የሴካፋ ዋንጫ ላይ ለሀገሩ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን በሀዋሳ ከተማም በ2009 ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ተካቶ የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመሆን ያጠናቀቀ ተጫዋች ነበር፡፡

በቅርቡ ከፀጋዓብ ዮሴፍ እና ያኦ ኦሊቨር ጋር የተለያየው ክለቡ ከቀናት በፊት የፊት አጥቂው ጋናዊው አትራም ኩዋሜን ወደ ስብስቡ በማካተት እና በመጀመሪያው ዙር ያልተጠቀሙት ጌትነት ቶማስን ዳግም ወደ ቡድን መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *