ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ሀዋሳ ከተማ

በሊጉ ሁለተኛ ዙር መጀመሪያ በሆነው የወልዋሎ እና ሀዋሳ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ጉዳዮች አንስተናል።

ነገ 09፡00 ላይ በትግራይ ስታድየም ወልዋሎ ዓ/ዩ ሀዋሳ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ሁለተኛው የውድድሩ አጋማሽ መጀመሪያ ይሆናል። አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን በአሰልጣኝነት የሾሙት ቢጫ ለባሾቹ ከእስካሁኑ የፕሪምየር ሊጉ ቆይታቸው የተለየ መልክ ይዘው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል። በዚህም አምስት ወይንም አራት አማካዮችን የሚጠቀም እና በጠንካራ የመከላከል መሰረት ላይ የሚገነባ ቡድን ይዘው የመምጣት ዕድል ይኖራቸዋል። ወልዋሎዎች ከአሰልጣኝ ቅጥሩ ባለፈም ከተስፋዬ ዲባባ ፣ ዮሃንስ ሽኩር እና ሮቤል አስራት ጋር ሲለያዩ ግብ ጠባቂው ሺሻይ መዝገቦን ደግሞ አሳድገዋል። በነገው ጨዋታ ደግሞ ቡድኑ በኢትዮጵያ ዋንጫ ፋሲል ከተማን ሲገጥም ለሁለተኛ ጊዜ ጉዳት ገጥሞት ሰባት የሊጉ ጨዋታዎች ያለፉት ዋለልኝ ገብሬ እንዲሁም ቀላል ጉዳት የነበረባቸው ኤፍሬም አሻሞ እና አብዱላዚዝ ኬይታ ከጉዳት እንየው ካሳሁን ደግሞ ከኦሊምፒክ ቡድኑ መቀነሱ ተከትሎ ቡድናቸውን ያገለግላሉ። አዳማ ላይ ቀጥታ የቀይ ካርድ የተመለከተው አፈወርቅ ኃይሉ በቅጣት ደስታ ደስታ ደሙ ደግሞ ለኦሊምፒክ ቡድኑ በመመረጡ ከጨዋታው ውጪ ናቸው።

ከመሪው በዘጠኝ ነጥቦች ዝቅ ብለው አምስተኛ ደረጃን በመያዝ የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቁት ሀዋሳ ከተማዎች በአመዛኙ ባለፉት ዓመታት ከታችኛው ቡድናቸው ባሳደጓቸው ተጫዋቾች ያደረጉት ጉዞ አዋጭ ሆኖ ያገኙት ይመስላል። መስፍን ታፈሰ ፣ ምንተስኖት እንድርያስ እና ምንተስኖት ጊምቦን አሳድገው ወደ ሁለተኛው ዙር መምጣታቸውም ይህን የሚያሳይ ነው። በርግጥ አምና በድሬዳዋ የምናውቀው የፊት ጋናዊው የፊት አጥቂ አትራም ኩዋሜን ለዚህ ጨዋታ ባይደርስም ወደ ቡድናቸው ያመጡ ሲሆን በሌላ በኩል ከመስመር ተከላካዩ ያኦ ኦሊቨር ጋር ተለያይተዋል። ቡድኑ በ15ቱ ጨዋታዎች እንዳታየው በቀጥተኛ አጨዋወት እና ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ያተኮረው አጨዋወቱ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ገብረመስቀል ዱባለ እና ብሩክ በየነ በጉዳት እስራኤል እሸቱ ፣ ደስታ ዮሃንስ እና ተክለማሪያም ሻንቆ ደግሞ በኦሊምፒክ ቡድኑ ምርጫ ውስጥ በመካተታቸው ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። ሁለት የመስመር ተመላላሾቹን እና ሁለት አጥቂዎቹን ያለመጠቀሙ ጉዳይ ሲታይም ከቡድኑ አጨዋወት አንፃር ጨዋታው ሊከብደው እንደሚች መገመት ይቻላል።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– የአምናው የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት አንድ ግብ ብቻ የተቆጠረበት ቢሆንም ዘንድሮ በአንደኛው ሳምንት ሲገነኙ ግን ሀዋሳ ከተማ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሎ ነበር።

– በጊዚያዊነት ጨዋታዎቻቸውን ትግራይ ስታድየም ላይ እያደረጉ የሚገኙት ወልዋሎዎች ከስምንት ጨዋታዎች ሦስቱን በድል ሲወጡ ሦስት የአቻ እና ሁለት የሽንፈት ውጤቶችን አስመዝግበዋል።

– ከሜዳው ውጪ በደካማ አቋሙ የቀጠለው ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮም ከስድስት ጨዋታዎች ድል የቀናው ነገ ጨዋታውን ወደ ሚያደርግበት መቐለ አቅንቶ ደደቢትን በገጠመበት የመጨረሻ ጨዋታው ነበር። ከዛ ውጪ ሁለቴ ሲሸነፍ ሦስቴ ነጥብ መጋራት ችሏል።

 

ዳኛ

– እግሩ ላይ በገጠመው ጉዳት ሳቢያ በመጀመሪያው ዙር ምንም ጨዋታ መዳኘት ያልቻለው ኢብራሂም አጋዥ ይህን ጨዋታው በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-2-3-1)

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን – በረከት ተሰማ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

ብርሀኑ አሻሞ – አስራት መገርሳ

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ዋለልኝ ገብሬ – ኤፍሬም አሻሞ

ሪችሞንድ ኦዶንጎ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – መሣይ ጳውሎስ

ዳንኤል ደርቤ – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን –ኄኖክ ድልቢ – ጌትነት ቶማስ

ታፈሰ ሰለሞን

ቸርነት አወሽ – አዳነ ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *