ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ የደርሶ መልስ ድሉን ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ተቀዳጅቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ በሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ በሳላምላክ ተገኝ ብቸኛ ግብ አሸንፎ ደረጃውን አሻሽሏል።

21 ደቂቃ ዘግይቶ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴድሮስ ምትኩ በተመራው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች የተለያዩ መልኮችን አስመልክተውናል። በመጀመሪያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ የጣናው ሞገዶቹ ተሽለው ሲንቀሳቀሱ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ፈረሰኖቹ የተሻለ ሲጫወቱ ተስተውሏል።

የሚታወቁበትን 4-3-3 የተጨዋች አደራደር ይዘው የገቡት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በአማካይ ስፋራ ላይ በዝተው ለመጫወት አስበው የገቡት ጊዮርጊሶችን ተቆጣጥረው በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ሲደርሱ ታይቷል። በ3-4-1-2 የጨዋታ ፎርሜሽን ለጨዋታው የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሚያገኙዋቸውን ኳሶች በአግባቡ አጥቂ መስመር ላይ ለተሰለፉ ተጨዋቾቻቸው ባለማድረሳቸው ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ሲስተዋል በተለይ በሜዳ ላይ የአማካይ እና የአጥቂ መስመሩን የሚያገናኝ ተጨዋች አጥተው የግብ ሙከራ ለማድረግ ብቸኛ አማራጫቸውን ረጃጅም ኳሶች በማድረግ ተጫውተዋል።

ፍጥነት የተሞላበት አጨዋወት መርጠው የገቡት ባህር ዳሮቸ በተለይ የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ወደ ጊዮርጊሶች የግብ ክልል እየደረሱ በጊዜ መሪ ለመሆን ጥረዋል። በዚህም በ6ኛው ደቂቃ ግርማ ዲሳሳ ያገኘውን ኳስ ወደ ጊዮርጊሶች የግብ ክልል ለማድረስ ሲሞክር ተጨርፎ የተመለሰውን ኳስ ጋዲሳ ሳይቆጣጠረው በመውደቁ የባህር ዳሮች የቀኝ መስመር ተከላካይ ሳላምላክ ተገኝ በማግኘቱ የተመታው ኳስ ፓትሪክ ማታሲ ሳያድነው የመጀመሪያ ጎል ተቆጥሮ ባለሜዳዎቹ በጊዜ መሪ ሆነዋል። ግቧ ስትቆጠር ደስታቸውን ሲገልፁ የነበሩት የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው መጠነኛ ጉዳት አጋጣሟቸው በህክምና ባለሙያዎች ታግዘው ወደ ህክምና ቦታ አምርተዋል። ገና በጊዜ ግብ ያስተናገዱት ጊዮርጊሶች ለተቆጠረባቸው ግብ ምላሽ ለመስጠት በሚመስል መልኩ ከደቂቃ በኋላ በናትናኤል ዘለቀ አማካኝነት ሙከራ አድርገው መክኖባቸዋል።

ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ባለሜዳዎቹ በ15ኛው ደቂቃ ግርማ ዲሳሳ እና ወሰኑ ዓሊ አንድ ሁለት ተቀባብለው ወደ ሳጥን በመግባት በሞከሩት ሙከራ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ማታሲ አምክኖባቸዋል። የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ረጃጅም ኳሶችን ለአቤል ያለው እና ሪቻርድ አርተር ሲልኩ የነበሩት ጊዮርጊሶች በ21ኛው ደቂቃ በሪቻርድ አማካኝነት በተሞከረ ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የባህር ዳሮችን ግብ ያስቆጠረው ሳላምላክ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ አብዱልከሪም በግምባሬ ለግብጠባቂው ማታሲ አቀብላለው ብሎ እራሱ መረብ ላይ ለማስቆጠር ተቃርቦ ለጥቂት ወቷል። አብዱልከሪም ያወጣውን ኳስ ተጠቅመው የመአዘን ምት ያገኙት ባህር ዳሮች በግርማ አማካኝነት አሸምተውት ግብ ለማስቆጠር ምክረው ወቶባቸዋል። ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ አጨዋወታቸውን ለመቀየር ጥረት ያደረጉት ተጋባዦቹ በመጠኑ ተረጋግተው ለመጫወት ሞክረዋል። በ38ኛው ደቂቃም የባህር ዳር ተጨዋቾች የፈፀሙትን የቅብብል ስህተት ተጠቅመው በአቤል አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ሞክረው ሃሪሰን ሄሱ አድኖባቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናግድ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተጠናክረው እና አጨዋወታቸውን ቃኝተው የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባህር ዳሮች ሜዳ ላይ በማሳለፍ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክረዋል። በተቃራኒው ያገኙትን ሶስት ነጥብ አሳልፎ ላለመስጠት ወደ ኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ የነበሩት ባህር ዳሮች የግብ ማግባት ምንጫቸውን ከቆመ ኳስ እና ከመልሶ ማጥቃት በማድረግ ተንቀሰቅሰዋል። በ51ኛው ደቂቃ ከጥሩ ቦታ የቅጣት ምት ያገኙት ባህር ዳሮች በፍቃዱ ወርቁ አማካኝነት ወደ ግብ ሞክረው ወደ ውጪ ወቶባቸዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር መልሰው ያገኙተ ፈረሰኞቹ ብልጫቸውን በግብ ለማሳመር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ባህር ዳሮች ላይ አድርገው መክኖባቸዋል። በ54ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም መሃመድ ከቀኝ መስመር ለናትናኤል ዘለቀ አቀብሎት ናትናኤል ያመከነው እና በ60ኛው ደቂቃ ጋዲሳ ያሻገረውን የመአዘን ምት በተመሳሳይ ናትናኤል ያልተጠቀመበት አጋጣሚዎች ይበልጥ ለግብነት የቀረቡ ቢመስሉም መረብ ላይ ሳያርፉ ቀርተዋል። በተለይ በ60ኛው ደቂቃ የተሞከረችው የናትናኤል ዘለቀ የግምባር ኳስ ግብ ጠባቂውን ሃሪሰን አልፋ ከመረብ ለማረፍ የተቃረበች ብትመስልም ግዙፉ የባህር ዳሮች ተከላካይ አቤል ውዱ እንደምንም አውጥቷታል።

የአጥቂ ባህሪ ያላቸውን ተጨዋቾች በተከታታይ በመለወጥ ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ጊዮርጊሶች በ69ኛው ደቂቃ ሌላ አጋጣሚ በአብዱልከሪም አማካኝነት ፈጥረው መክኖባቸዋል። የተከላካይ ክፍላቸውን ወደ መሃል በማስጠጋት በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ሲታይባቸው የነበረውን ክፍተት ለማረም የሞከሩት ስቲዋርት ሃል ከተከላካይ እስከ አጥቂ ክፍል ያለውን ስፋት አጥበው ለመጫወት በመሞከር የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። ባህር ዳሮች በበኩላቸው ወደ ኋላ በማፈግፈግ ለጊዮርጊስ ተጨዋቾች ክፍተቶችን ለመንፈግ ሲሞክሩ ታይቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ያልተጠበቀ እድል ያገኙት ባህር ዳሮች በግርማ ዲሳሳ አማካኝነት ተጨማሪ ጎል አስቆጥረው መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉበትን አጋጣሚ ፈጥረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በሁለተኛው አጋማሽ የነበራቸውን ብልጫ በጎል ማሳመር ያልቻሉት ፈረሰኞቹ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በባህስ ዳር 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *