ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ አስረኛ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

ምዓም አናብስት በያሬድ ብርሃኑ እና ኦሴይ ማውሊ ግቦች ታግዘው ደደቢትን 4-1 በማሸነፍ በአንድ የውድድር ዘመን ተከታታይ ጨዋታ የማሸነፍ ክብረ ወሰንን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተጋርተዋል።

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ በደረሰው አስደጋጭ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች በተደረገ የህሊና ፀሎት እና የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ማኅበር ለቀድሞ ተጫዋቾቻቸው ኃይሉ ገብረእየሱስ ፣ መድሃኔ ታደሰ ፣ ቢንያም ደበሳይ እና ሙሴ ዮሃንስ ባደረጉት ምስጋና የጀመረው ጨዋታው በርካታ ግቦች የታዩበት ነበር።

ብዙም ሳቢ ባልነበረው እና እምብዛም ንፁህ የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት የመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ከሳጥን ውጪ ካደረጓቸው ሌላ አደገኛ የሚባሉ ሙከራዎችን ማድረግ አልቻሉም።

ኦሴይ ማውሊ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መትቶ ረሺድ ማታውሲ በቀላሉ ባዳነው ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት መቐለዎች በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ከተጋጣሚያቸው አንፃር የተሻሉ ሆነው ቢገኙም በሁለት አጋጣሚዎች ያሬድ ብርሃኑ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ካደጋቸው ሙከራዎች ውጭ የተቀሩት ከሳጥን ውጭ ከርቀት በመምታት ነበር የሞከሩት። በዚህም ሃይደር ሸረፋ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቷት ወደ ላይ የወጣችው እና ራሱ ሃይደር በድጋሜ አክርሮ መትቶ ግብጠባቂው የመለሳት ኳስ ይጠቀሳሉ።

የመጀመርያው አጋማሽ መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በተሻለ ጫና የፈጠሩት መቐለዎች ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጪም በያሬድ ብርሃኑ እና ዮናስ ገረመው እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር ፤ ዮናስ ገረመው ከስዩም ተስፋዬ የተሻገረችለትን ኳስ አክርሮ ሞክሮ ቋሚውን ገጭታ የተመለሰች ሲሆን ያሬድ ብርሃኑ ደግሞ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው ሙከራዎች ይነሳሉ። በተለይም ፍሊፕ ኦቮኖ በጥሩ ሁኔታ የለጋትን ኳስ ይዞ ገብቶ ሞክሮ ለጥቂት የወጣችበት ሙከራ 70 እንደርታዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

በመጀመርያው አጋማሽ ከተጋጣሚያቸው ባልተናነስ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ማሳካት የቻሉት ሰማያዊዎቹም በርካታ ሙከራዎች ያደረጉት ከሳጥን ውጭ ነበር። ከነዚህም ውስጥ አሸናፊ እንዳለ እና ኤፍሬም ጌታቸው ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ ፤ በተለይም ኤፍሬም ጌታቸው በጥሩ ሁኔታ መቷት የመረቡ የውጪ አካል ላይ ያረፈችው ኳስ ለግብ የቀረበች ነበረች።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የጨዋታ ፍሰት የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ አምስት ግቦችን ያስመለከተን ነበር። ጨዋታው ተጀምሮ ብዙም ሳይዘልቅ አለምአንተ ካሳ ከአቤል እንዳለ የተቀበለውን ኳስ በሳጥኑ በቀኝ በኩል አክርሮ በመምታት እጅግ አስደናቂ ጎል በማስቆጠር ሰማያዊዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ሆኖም የቡድኑ መሪነት የቆየው ለሦስት ያክል ደቂቃዎች ነበር ፤ ሄኖክ መርሹ በያሬድ ብርሃኑ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ኦሴይ ማውሊ በማስቆጠር መቐለን አቻ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ የደደቢትን ደካማ የመከላከል አደረጃጀት ተጠቅመው በርካታ ዕድሎች የፈጠሩት 70 እንደርታዎቹ ሁለተኛውን ግብ ለማስቆጠርም ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም። ኦሴይ ማውሊ የግብ ጠባቂው እና ተከላካዮቹን አለመናበብ ተጠቅሞ ከጠባብ አቅጣጫ ግብ በማስቆጠር ቡድኑ እንዲመራ አስችሏል።

በጨዋታው ከበርካታ ጊዜያት በኃላ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ተመልሶ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ያሬድ ብርሃኑ በሰባኛው ደቂቃ ከኦሴይ ማውሊ በጥሩ ሁኔታ የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር የመቐለን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ወርደው የታዩት ሰማያዊዎቹ በበኩላችው በሄኖክ መርሹ እና በአለምአንተ ካሳ ሁለት ጥሩ የግብ ዕድሎች ፈጥረው ነበር። በተለይም ሄኖክ መርሹ በግል ጥረቱ ተጫዋቾች አልፎ መትቶ ፍሊፕ ኦቮኖ በሚያስድንቅ ብቃት ያወጣት ኳስ በደደቢት በኩል ትጠቀሳለች። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ፍፁም ብልጫ የነበራቸው 70 እንደርታዎቹ በ90ኛው ደቂቃ በያሬድ ብርሃኑ ሌላ ግብ አክለው የጎል መጠናቸው ወደ አራት አሳድገዋል ፤ አማካዩ ኦሴይ ማወሊ ከመስመር ያሻገራት ኳስ በጥሩ ሁኔታ ነበር ወደ ጎልነት የቀየረው። ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ከጨዋታው መጠናቀቅ ቀደም ብሎ ያደረጋት ሙከራም ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች።

ውጤቱ በዚህ መልኩ መጠናቀቁን ተከትሎ መቐለ 70 እንደርታ ከተከታዩ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ስምንት ከፍ ሲያደርግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ1991 እስከ 1992 በዘለቀው የ15 ጨዋታዎች ተከታታይ ድሉ ወቅት በ1991 በአንድ የውድድር ዓመት በርካታ ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ የያዘውን ክብረ ወሰን መጋራት ችለዋል። ቀጣይ አምስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ካሸነፈም የፈረሰኞቹን ሪከርድ የሚሰብር ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *