የአሰልጣኞች አስተያየት | መቐለ 70 እንደርታ 4-1 ደደቢት

መሪው መቐለ 70 እንደርታ ከ ደደቢት ካደረጉት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት እንዲህ አቅርበነዋል።

“አስር ግዜ በተከታታይ ነው ያሸነፍነው፤ ይሄ ደግሞ የማይታመን ነው” ገብረመድኅን ኃይሌ

ስለ ጨዋታው

ከዕረፍት በፊት ጥሩ አልነበርንም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን አስተካክለን ጥሩ ተጫውተናል፤ በአጠቃላይ ጥሩ ነው። አሁንም ችግሮች አሉብን በቀጣይ የተወሰኑ ተጫዋቾች ይመለሳሉ። በጥቅሉ ስናየው ግን በሁለተኛው አጋማሽ ያጠቃንበት መንገድ ጎል እንድናገኝ ረድቶናል።

ስለ ተከታታይ ድል እና ስለ ያሬድ ብርሃኑ የዛሬ ብቃት

ባለፉት ጊዜያት የስነ ልቦና ችግር ገጥሞት ነበር። ያሬድ ዛሬ ጥሩ ተንቀሳቀሰ፤ በተጨማሪም ሁለት ግብ እግብቶልናል። በጣም ጥሩ ነገር ነው ይሄ። ለቡድናችን ተጨማሪ ኃይል ነው። በዚህ ከቀጠለ በማጥቃት ያለብንን ችግር ይፈታልናል ብዬ አስባለው።

አስር ግዜ በተከታታይ ነው ያሸነፍነው። ይሄ ደሞ የማይታመን ነው፤ በኢትዮጵያ ከባዱ ነገር ነው። በቀጣይነት የተሻለ ለመስራት እንሞክራለን። ዋና ነገር ማሸነፋችን፤ ትልቁ ነገር ነጥባችንን ማሳደግ ነው። ክብረ ወሰኑ ግን ያስደስተናል።

የቀጣይ ከባድ ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች እና የአጨዋወት ለውጥ

ቅድም እንዳልኳችሁ ብዙ ችግሮች አሉብን ፤ ችግሮች ተቋቁመን ለመጫወት በተወሰነ አጨዋወታችን የምንቀይርበት አጋጣሚ ይኖራል። በቀጣይ ግን ጨዋታው በሜዳችን ስለሆነ አጨዋወታችን አንቀይርም። ግን የተጫዋቾች ለውጥ ይኖራል። ዛሬ ተጫዋችም ተጎድቶብናል። ሥዩም ወሳኝ ተጫዋቻችን ነው። እሱ መጎዳቱ አንድ ችግር ሆኖብናል።

ስለ ደጋፊው

ደጋፊው አዲስ ነገር አይደለም፤ በጣም ያስደምማል። ከዚ በላይም ይቀጥላል ብዬ አምናለው። በገንዘብም በሌላም ሊያግዝህ የሚችል ደጋፊ ይዘህ ከጎናቹህ ነን ብሎ ሲደግፍህ ደስ ይላል። እሱም ነው የስኬታችን ምስጢር።

“የብስለት እና ብልጠት ችግር ነበረብን” ዳንኤል ፀሐዬ

ስለ ጨዋታው

እንቅስቃሴያችን መጥፎ አልነበረም። በሁለቱም አጋማሾች ጥሩ ነበርን። እኛ የብስለት ችግር ነበረብን አብዛኞቹ በረጅሙ የተጣሉ ኳሶች ነው የገቡብን። በጉልበትም በፍጥነትም ተበልጠናል በዛ ላይ ብልጠትም አልነበረንም። ተከላካዮቻችን መሸፈን የነበረባቸው ቁልፍ ቦታዎች አልሸፈኑም። በተለይም ሁለተኛዋ ጎል በዛ መንገድ ነው የገባችው።

የመቐለዎች እንቅስቃሴም ጥሩ ነው። በተለይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ኳስን በማንሸራሸር ሳይሆን በረጃጅም ኳሶች ነበር ያጠቁን። ለአጨዋወታቸው ተዘጋጅተን ነበር።

አምስት ተሰላፊዎቻችን አጥተናል። ሁለቱ ተጫቾች ብሄራዊ ቡድን የነበሩ ሲሆን ያብስራ ተስፋየ መጥቷል። በተከላካይ ላይ ጥሩ ተጫዋቻችን ዳዊት ወርቁ አልነበረም። ከዛ በተጨማሪ ሶስት ከውጭ ያስመጣናቸው ተጫዋቾችም በአንዳንድ የወረቀት ጉዳዮች አልተሰለፉም። በተከላካይ ክፍልም ኪሩቤል ኃይሉን ማግኘት አልቻልንም። የተዘጋጀንበት የመጀመርያ አሰላለፍን ቅዳሜ ነበር የቀየርነው። እንደማይጫወቱ ካወቅን በኃላ ነው እንደ አዲስ አዲስ ቡድን የሰራነው ይሄ ራሱ አንድ ምክንያት ነው።

ቡድኑን ከወራጅ ቀጠና ስለማውጣት

እንዳያችሁት ቡድናችን መጥፎ አይደለም። የጎል ዕድል በመፍጠርን ወደ ጎል የምንደርስበት መንገድም ጥሩ ነበር። ይሄን እያደረግን የጥንቃቄ ጨዋታ ብንጫወት ኖሮ ግን በዚ ልዩነት ባልተሸነፍን ነበር። በተከላካይ ክፍላችን እንደፈራነው ነው የሆነው። ዳዊት ወርቁን ከብሄራዊ ቡድን ለማምጣት ብዙ ጥረናል። ከዛ ውጭ ናይጄርያዊው አቡዋላም ጥሩ ተከላካይ ነበር። ባጠቃላይ ግን በተከላካይ ክፍል ላይ ያለንን ክፍተቶች ለመፍታት እንጥራለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *