መቐለ 70 እንደርታ የአጥቂውን ውል አራዘመ

ባለፈው ዓመት አጋማሽ የዝውውር መስኮት መቐለ 70 እንደርታን የተቀላቀለው ያሬድ ብርሃኑ ከክለቡ ጋር እስከ ቀጣይ ዓመት አጋማሽ ለመቆየት ተስማማ።

ከወልድያ ጋር በስምምነት ተለያይቶ መቐለን በአንድ ዓመት ውል ከተቀላቀለ በኋላ ያለፈውን አንድ ዓመት ከተቀያሪ ወንበር እየተነሳ ቡድኑን ያገለገለው ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ከምዓም አናብስት ጋር ያለው ውል በመጠናቀቁ ወደ ሌሎች የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ይዘዋወራል ቢባልም ተጫዋቹ ግን ለቀጣይ አንድ ዓመት በክለቡ ለመቆየት ተስማምቷል።

በ2007 በመቐለ 70 እንደርታ መለያ ብቅ ያለው የመስመር አጥቂው በቀጣዩ ዓመት የፕሪምየር ሊጉን ክለብ ደደቢት ቢቀላቀልም በቡድኑ የቋሚነት ዕድል ባለማግኘቱ በውሰት ውል ወደ ወልዲያ አቅንቶ ከቡድኑ ጋር የተሳካ አንድ ዓመት አሳልፎ ነበር ወደ አሳዳጊው ክለብ መቐለ በድጋሚ ወደ ክለቡ የተመለሰው።

አጅግ አስደናቂ የውድድር ዓመት በማሳለፍ ላይ የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ በትላንትናው ዕለት ደደቢትን 4-1 ሲያሸንፍ የመጀመርያ ተሰላፊነት እድል ያገኘው ያሬድ ብርሀኑ ኮከብ ሆኖ የዋለ ሲሆን ሁለት ግብ አስቆጥሮ ለአንድ ግብ መቆጠር ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *