ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ወልዋሎን በመርታት ወደ ድል ተመልሷል

አምስት ተከታታይ ሽንፈቶች የደረሱበት ኢትዮጵያ ቡና በአምበሉ አማኑኤል ዮሐንስ ብቸኛ ግብ ወልዋሎን በማሸነፍ የድል መንገዱን አግኝቷል።

በቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ታጅቦ በጀመረው ጨዋታ ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት ከመቐለ አቻ ከተለያየው ስብስባቸው በረከት አማረን በዓብዱልአዚዝ ኬይታ ፣ ዳንኤል አድሀኖምን በብርሃኑ ቦጋለ ፣ ቢንያም ስራጅን በደስታ ደሙ ተክተው ሲገቡ እንግዶቹ ቡናዎች በበኩላቸው በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት ከገጠመው ቡድናቸው ውስጥ ቶማስ ስምረቱ ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ ሱለይማን ሉክዋ እና እያሱ ታምሩን በአማኑኤል ዮሐንስ ፣ ሄኖክ ካሳሁን ፣ አቡበከር ናስሩ እና ሁሴን ሻባኒን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ብዙም ሳቢ እንቅስቃሴ እና በርካታ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያልታዩበት የመጀመርያው አጋማሽ በአንፃራዊነት የባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ብልጫ የታየበት ነበር። ብርሃኑ አሻሞ ከረጅም ርቀት አክርሮ መቶት ወንድወሰን አሸናፊ በጥሩ ሁኔታ ባወጣው ሙከራ የጀመረው የባለሜዳዎቹ ጥቃት በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ከብልጫም ባሻገር በሙከራዎችም የታጀበ ነበር። በሃያኛው ደቂቃ በኤፍሬም አሻሞ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት እራሱ ኤፍሬም አሻሞ መትቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ፤ ኳሱን አማካዩ መቶት አግዳሚውን ገጭቶ ከተመለሰ በኃላ ነበር ግብ ጠባቂው ማዳን የቻለው።

ፍፁም ቅጣት ምት ካመከኑ በኃላም ከተጋጣሚያቸው አንፃር በተሻለ ወደ ግብ ቶሎ ቶሎ የደረሱት ቢጫ ለባሾቹ በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች በተሻለ ተንቀሳቅሰው ሙከራዎችም አድርገው ነበር። በተለይም እንየው ካሳሁን በጥሩ ሁኔታ አሻግሮት ክሪስቶፈር ችዞባ በደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ያመከነው ኳስ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆ እና ኤፍሬም አሻሞ ከርቀት ያደረጓቸው ጥሩ ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ።

በመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱ አጥቂዎች በግላቸው ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጪ እንደቡድን የተሳካ ማጥቃት አጨዋወትን መተግበር ያልቻሉት ቡናዎች በአህመድ ረሺድ እና ሄኖክ ካሳሁን አማካይነት ጥሩ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ሄኖክ ካሳሁን በግሩም ሁኔታ መትቶት ዓብዱላዚዝ ኬይታ ያወጣው ኳስ ቡናማዎቹ ከፈጠሯቸው ዕድሎች በተሻለ ሁኔታ ለግብ የቀረበ ነበር።

ኢትዮጽያ ቡናዎች በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉበት ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የታዩበትም ጭምር ነበር። በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ አጨዋወቱ በመሃል ሜዳ የፈጠረላቸው የቁጥር ብልጫ ተጠቅመው ኳሶች ከማንሸራሸር ውጪ ንፁህ የጎል ዕድል ሳይፈጥሩ ወደ ዕረፍት ያመሩት ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ በብዙ ረገድ ተሻሽለው ሲቀርቡ መሪ የሚያደርጋቸውን ጎልም ለማግኘትም ብዙ አልቆዩም። በአርባ ዘጠነኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ነስሩ ከመስመር ያሻገራት ኳስ ሁሴን ሻባኒ በተረከዝ መትቶ የወልዋሎ ተከላካዮች ሲደረቡበት አማኑኤል ዮሐንስ የተመለሰው ኳስ ተጠቅሞ ቡድኑን መሪ ምታደርግ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ግብ ካስቆጠሩ በኃላም ጥሩ የተንቀሳቀሱት ቡናዎች ብዙም ሳይቆዩ የግብ መጠናቸውን ከፍ የሚያደርጉባቸው ሁለት ወርቃማ ዕድሎች በአስራት ቱንጆ እና ሑሴን ሻባኒ መፍጠር ችለው ነበር። አስራት ከረጅም ርቀት ያደረጋትን ሙከራ ኬይታ በጥሩ ሁኔታ ወደ ውጪ ሲያወጣት ሑሴን ሻባኒ በጥሩ ሁኔታ ገብቶ ያደረጋት ሙከራም ቋሚውን ገጭታ ተመልሳለች።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ የሰመረ እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ማድረግ ያልቻሉት ቢጫ ለባሾቹ ምንም እንኳን የአቻነት ግብ ባያስቆጥሩም ጫና በፈጠሩባቸው ደቂቃዎች በርካታ ዕድሎችን አግኝተው ነበር። ከነዚህም ውስጥ ኤፍሬም አሻሞ ከአዶንጎ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ እና ፕሪንስ ከርቀት ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ቡናዎች በእጃቸው የገባውን ነጥብ ለማስጠበቅ የመከላከል ባህሪ ያላቻው ተጫዋቾችን ቀይረው በማስገባት አፈግፍገው ሲጫወቱ ባለሜዳዎቹ ጫና በመፍጠር አቻ የሚያደርጋቸው ጎል ፍለጋ አጥቅተው በመንቀሳቀስ የጎል ዕድሎችም ፈጥረዋል ፤ ከነዚህም ፕሪንስ አሻምቶት ከጎሉ ቅርብ ርቀት የነበረው ኤፍሬም አሻሞ ሞክሮት ወደ ውጪ ያወጣው እና ሰመረ ካሕሳይ በሶስት አጋጣሚዎች የሞከራቸው ኳሶች ይጠቀሳሉ።

ጨዋታው በዚሁ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ወልዋሎ በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ስር የመጀመርያ ሽንፈቱን ሲያስመዘግብ ኢትዮጵያ ቡና ከተከታታል አምስት ሽንፈት በኃላ ወደ ድል መመለስ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *