አሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-1 ባህር ዳር ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት የዛሬ ብቸኛ መርሐ ግብር ሀዋሳ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ ካደረጉት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን በዚህ መልኩ ሰጥተዋል።

አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው

ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረን ፍላጎት ማሸነፍ ነበር። እኛ ጋር ወጣት ተጫዋቾች ስለሚበዙ እንጂ በብዛት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ቢሆኑ ይህ አይፈጠርም ነበር። ከሜዳ ውጪ አስበነው የምንመጣውን ነገር ሜዳ ውስጥ መተግበር አልቻልንም። ያንን ብንተገብር የተሻለ ይሆን ነበር። እንዲሁም የተቃራኒ ቡድን አጨዋወት ኳሱን ጠብቆ ነበር የሚወጣው እና ኋላችን ላይ የምናደርገዉ እንቅስቃሴ ስህተት እንደሚፈጥር ይታወቃል። እኛ ነፃ ሆነን ነበር ኳሱን ስናሽከረክረዉ የነበረው። የገባብንም ግብ ያንን በማድረጋችን ነው።

እኛ በቀዳዳዎች መካከል ጠብቀን ነው የምንጫወተው። ኳሱን ወደፊት የመውሰድ እንቅስቃሴ ላይ የተሻልን ነበርን። በኋላ ግን እየወረድን ከመምጣታችን በተጨማሪ የነሱ አጨዋወት ሰዓት የመግደል ነበር። አዳነን ዛሬ አይታችሁት ከሆነ በጣም ጥሩ ነበር፤ በተቃራኒው ደግሞ ሄኖክ ድልቢ ጥሩ አልነበረም። ወይ ኳሱን እንደ በፊቱ ይዞት የመጫወት ነገር የለውም ወይም ኳሱን ወደፊት የሚሞክራቸውን ሙከራዎች ሲያደርግ አይስተዋልም። የቀየርነውም ለዛ ነው። ታዳጊዎችን የተወሰነ ጊዜ ነው የምታያቸው፤ እየወረዱ በመጡ ቁጥር ቶሎ እርምጃ የማትወስድ ከሆነ የበለጠ እየወረዱ ነው የሚመጡት። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች እንኳን መቼ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ያውቃሉ ።

በተደጋጋሚ ነጥብ መጣል እና የዲሲፕሊን ችግር

እግርኳስ እስከተጫወትክ ድረስ ነጥብ የመጣሉ ነገር ይቀጥላል። ግን ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሙሉ 45 ደቂቃ ተጫወትን ማለት አይቻልም፤ ካልተጫወትን ደግሞ ውጤቱ ይኸው ነው የሚሆነው።

የደረጃ ሰንጠረዡን ስናየው ታች የሆንን ይመስላል። ነገር ግን ዛሬ አሸንፈን ቢሆን ወደ ስድስተኛ አምስተኛ ነበር የምንቀመጠው። የግድ ግን ሜዳህ ላይ ማሸነፍ አለብህ። ከሜዳ ውጪ ግን ተጋጣሚዎችህ ብዙ ደጋፊዎች ስላላቸው ያ የደጋፊ ተፅዕኖ ይኖረዋል።

ጉድለቶችን ስንመለከት የተጫዋቾች ቁጥር ማነስ ነው። ሶስት ተጫዋቾች ለቤሔራዊ ቡድን ሄደው ነበር። ቡድንህን ስትገነባ ሁልጊዜ እኩል ሆነው የማይመጡልህ ከሆነ ትቸገራለህ።

ወልዋሎ ጨዋታ ላይ እንደታየው የኛ ተጫዋቾች ብልጥ አለመሆን ነው፤ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች ከኛ የተሻለ ብልጠት አላቸው። እኛ ኳሱ ላይ ብቻ እያተኮርን ነው። የወላይታ ድቻ ጨዋታ ላይ በሁለት ቢጫ ነው የወጣው። ሲወጣ ምናልባት የተናገረው ነገር ይኖራል። እናም የዲሲፒሊን ግድፈቱንም ቢሆን እናስተካክላለን ።

ስለ ዳኝነቱ

የዳኛው እይታ ነው የሚወስነው። በእኔ እይታ አንድ ተጫዋች ከኋላ ከተጠለፈ ፍፁም ቅጣት ምት ነው። እሱ ብቻ አይደለም ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጭም ጠልፎታል። የሚታየው ነገር መጠለፉ ነው፤ ለምሳሌ ፍፁም ቅጣት ምቱ ላይ ሊመታ የተዘጋጀበትን እግሩን ነው የተጠለፈው። ለምን እንዳለፈዉ አላውቅም ። የመጨረሻዉ የማዕዘን ጉዳይ ራሱ መስመር ዳኛው የማዕዘን ምት ወሰነ፤ የመሐል ዳኛው የመልስ ምት ነው አለ። ብቻ እንደዚህ አይነት ነገሮች ይከሰታሉ፤ ያው ስህተት ተሳስቶ ሊሆን ይችላል፤ ወይ ደግሞ በውስጡ ሌላ ነገር ሊኖር ይችላል። ሌሎች ዳኞች አሁን ይሄን አያልፉትም።

ጳውሎስ ጌታቸው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው

እኔ የሀዋሳን ጨዋታ ብቻ ልጠቅስላችሁ አልፈልግም። በሜዳችን ከጊዮርጊስ ካደረግነው ጨዋታ በኋላ በቀጥታ ወደ ሽረ ነው የተጓዝነው። ከዛ መልስ ደግሞ ከሲዳማ ቡና ጋር ከባድ ጨዋታ ነው ያደረግነው። ከዛሬው ጨዋታ ቀለሎ ከመቐለ ጋር ነው… በአጠቃለይ ስድስቱ ጨዋታ ከባድ ነው ለኔ።

የዛሬዉ ጨዋታ ሀዋሳም ነጥቡን ይፈልገዋል እኛም ነጥቡን እንፈልገው ነበር። የመጀመሪያውን 15 ደቂቃ ልጆቸ የሰጠኋቸዉን ግዴታ አልተወጡልኝም። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን የመጀመሪያውን 30 ደቂቃ ስለተጫናቸው መነሳሳት ጀመሩ፤ ከዛ ማስቆጠር ቻልን። ከዕረፍት በኋላ ኳሱን በደንብ ተቆጣጥረን ይዘን ነበር መጫወት የቻልነው ። ዳኛው ላይ ትንሽ ተቃውሞ ነበር። ፍፁም ቅጣት ምት ከለከለን የሚል ነገር ነበር። እንዲያውም ራሱ ታፈሰን ቢጠይቁት ይሻላል። እንደ እኔ እምነት ቢጫ ካርድ ሁሉ ማየት ነበረበት ብዬ ነው የምገምተው። እና በአጠቃላይ የጨዋታው ይዘቱ ተፈራራቂ ነበር። ለኛ ይሄ 3 ነጥብ ቢገባንም አላሳካነውም። ያው አቻ ወጥተናል። ለሚቀጥለው ጨዋታ አሁንም ያነሳሳናል ብየ እጠብቃለሁ።

የውጤቱ ተገቢነት

እንደነገርኳችሁ ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ በልጠውናል፤ ሁለተኛውን አጋማሽ አስተካክለን ግብ ማስቆጠር ችለናል። ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር ነበረብን ግን አልተሳካም። አንደኛ በተደጋጋሚ ከሜዳ ውጭ ነጥብ ስለጣልን መተማመናችን ወርዷል፤ አንድ ነጥብ ማግኘታችን በጣም ጥሩ ነው። ዳኛው ላይ ከነበረው ተቃውሞ አንፃር አንድ ነገር ይሳሳታል ብለን ፈርታን ስለነበር ሳጥን ውስጥ እንዲገቡ አልፈቀድላቸውም። አጥቂዎች ሁሉ እየመለስን ነበር የምናጫዉተው። በመልሶ ማጥቃት ራሱ ጥሩ ኳስ አግኝተን ነበር፤ ጃኮ የሳተው ኳስ የጨዋታውን ይዘት ይቀይረው ነበር። ስለዚህ ምንም የሚደባብቅ ነገር የለውም። አንድ ነጥቡን ፈልገነዋል። ብዙ ጉዳት ነበረብን፤ ሁለት አዲስ ያስፈረምናቸው ተጫዋቾችም አልደረሱልንም።

ስለተጫዋቾቹ እና አሰልጣኞቹ የዲሲፕሊን ችግሮች

እንግዲህ የኔ ቡድን ብቻ ከሆነ እንታረማለን። ተቃራኒም ክለብ ዛሬ አይተኸው ከሆነ በደንብ አብራራልሀለሁ እና ስህተቴን አርማለሁ። ምክንያቱም ብዙ ኳሶች ከጨዋታ ውጪ የሆኑ ውሳኔዎች ተቀብለናል። ኳስ ጨዋታ ነው። እንዲህ አይነት ነገር ከሌለ አያምርም፤ ውበቱም ይሄ ነው። ይሄ ስህተት ካለ አርማለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡